ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2016 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር…አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች››፡፡ ራዕ. 12፡1-2፣5
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር ፍቅርና የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችሁ ጋር በማለት የከበረ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡
የዘንድሮ ዓመት የፍልሰታን ጾም በምንጾምበት ጊዜ ሁሌም ስንጾም እንደምናደርገው ሁሉ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መቆየት የተቸገሩትን በምንችለው አቅም መርዳትና የታመሙትንና የታሰሩትን መጎብኘት የጾማችን ዋናው ተግባራት ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እናታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም ‹‹ከአዳም ኃጢአት ሁሉ ተጠብቃ የምድራዊ ሕይወቷ ጉዞ ሲያበቃ በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማያዊ ክብር›› እንደተወሰደች ስናስብ ስናሰላስል የቅዱስ ፍራንቺስኮስ የሰላም ጸሎትን የአስተንትኖአችንና የጾማችን ርእስ እንድናደርገው እጋብዛችኋለሁ፡፡
የሰላም መሳሪያ ለመሆን እንጸልይ
በሰላም እንድንኖር የጠራን አምላክ (1ቆሮ. 7፡15) ‹‹ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።›› ይለናል (ሮም 12፡18)፡፡ እኛም ምክሩን በመስማት በአንድ ልብ በመሆን በሰላም ከኖርን እርሱ የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር እንደሚሆን በቅዱስ ቃሉ አማካይነት ይነግረናል (2ቆሮ.13፡11)፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም›› የሚለን (ዮሐ. 14፡27)፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ስለ ሰላም እንዲህ ይለናል፣ ‹‹የሰብአዊ ሕይወት ክብርና እድገት ሰላምን ይሻል፡፡ ጦርነት ባለመኖሩ ወይም የባለጋራዎች ኃይል በመመጣጠኑ ሰላም አለ ማለት አይደለም፡፡ እንዲሁም ‹‹የሰዎች ጥቅምና በሰዎች መካከል የሚካሄዱ ነጻ ግንኙነቶች በሚገባ ካልተጠበቁ፡ ለሰዎች ሰብአዊ ክብርና ለሕዝቦች ከበሬታ ካልተሰጠ፣ በሰዎች መካከል የጋለ ወንድማማችነት ካልተመሰረተ በምድር ላይ ሰላም ሊገኝ አይችልም፡፡ ሰላም ሲባል ‹‹የስርዓት ርጋታ›› ማለት ነው፤ ሰላም የጽድቅ ስራ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬና የፍቅር ውጤት ነው፡፡›› (ካ.ቤ.ት.ክ 2304)፡፡
ሰላም ስለተመኘነው ብቻ የሚመጣ ነገር አይደለም የሰላም እንቅፋቶች አሉና ስለዚህ መጸለይና የሰላም መሳሪያ መሆንን ይጠይቃልና፤ የሰላም ጠንቆች የሚባሉት፡ ‹‹በሰዎችና በመንግስታት መካከል የሰፈነው ግፍ፡ ከመጠን ያለፈ የኢኮኖሚና የማኀበራዊ ፍትህ መዛባት፡ ቅናት፣ አለመተማመንና ትእቢት ሲሆኑ፡ ጦርነቶችንም ያስከትላሉ፡፡ ሰላምን ለማስፈን፡ እነዚህን ህውከቶች የሚያነሳሱ ሁኔታዎችን ለማስወገድ የሚደረግ ማንኛውም ነገር ሰላምን ለማስፈንና ጦርነትን ለማስቀረት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታል (ካቤትክ. 2317)፡፡ ስለዚህ እኛም በሚቻለን ሁሉ ከሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት እንድናደርግና ‹‹የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና›› እንደሚለው (ማቴ. 5፡ 9 ) የሰላም መሳሪያ የሚሆኑ ሰዎችን እንዲያበዛልን እንለምን፡፡
ጥል ባለበት ፍቅር ይሆን ዘንድ እንጸልይ
ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በተለያዩ ምክንያቶች ልንጣላ እንችላለን፣ ዋናው ነገር ወደቀድሞው ፍቅራችን ለመመለስ መታረቅን መሻት ግድ ይላል፡፡ በዚህ የፍልሰታ ጾም ወቅት ጥል ባለበት ሁሉ ፍቅር ይመጣ ዘንድ እንጸልይ፡፡ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችን አጥብቀን እንድንዋደድ (1ጴጥ. 4፡8)፣ በመዋደድ ውስጥ ተፈላጊው ዋናው ነገር ማእረግ ወይም እውቀት ሳይሆን ስለ ፍቅር ሲባል የሚደረግ ነገር ነው ይለናል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ‹‹በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።›› ፍቅር ታጋሽ ነውና እንድንታገስ ቸርነትን እንድናደርግ ቅናትን እንድናስወግድ እንዳንመካ እንዳንታበይ የማይገባ ነገር እንዳናደርግ የራሳችንን እንኳ እንዳንፈልግ እንዳንበሳጭ የተበደልነውን እንዳንቆጥር ከእውነት ጋር እንድንደሰት እንጹም እንጸልይ፡፡ ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል›› (1ቆሮ. 13፡1-7)
በደል ባለበት ይቅርታ እንዲሰፍን እንጸልይ
መስዋእተ ቅዳሴን ለመካፈል ከመሄዳችን በፊት ካስቀየሙን ሰዎች ጋር እርቅን መፍጠር እንድንችል እንጸልይ፡፡ ‹‹እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።›› (ማቴ 5፡23-24) የበደሉንን ይቅር በማለት የአምላካችንን ይቅርታ ማግኘት እንድንችል እንጸልይ፡፡ ‹‹ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።›› (ማቴ 6፡14-15)
ጳውሎስም እንዲህ ይላል፣ እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥›› (2ቆሮ 2፡10)፡፡ ስለዚህ እርስበርሳችን ትእግስትን እንድናደርግና በባልንጀራችን ላይ የምንነቅፈው ነገር ካለን ክርስቶስ ይቅር እንዳለን እኛም ይቅር እንድንባባል (ቆላ. 3፡13) እንጸልይ፡፡
ኃጢአተኛ መሆናችንን በመረዳት ንስሐ የምንገባበትን ትህትና እንዲሰጠን እንለምን፡፡ ‹‹ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም›› (1ዮሐ. 1፡8-10)፡፡
ጥርጣሬ ባለበት እምነት እንዲገኝ እንጸልይ
‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።›› (ዕብ 11፡1) በመሆኑም እግዚአብሔር በእርሱ ለሚታመኑ ሳይቸኩል ሳይዘገይ በእርሱ ጊዜ መልስ ይሰጣል፤ ለዚህም ነው ‹‹ እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? (ማቴ 6፡30) ዝም ይላችኋል የሚለን፡፡ ስንፈራ ደግሞ ‹‹ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? በማለት ነፋሱንና ባሕሩን ይገስጻል፥ ሰዎች ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ እስኪደነቁ ድረስ ታላቅ ጸጥታም ይሆናል። ›› (ማቴ. 8፡26-27) ‹‹ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም።›› (ዕብ. 10፡38) የሚል አምላክ ‹‹እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ…›› ይለናል›› (ማቴ. 9፡29)፡፡ ምክንያቱም እርሱ ‹‹ ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራን እግዚአብሔር የታመነ ነው›› (1ቆሮ. 1፡9)፤ እኛ ግን እንደ ሐዋርያት ጌታን እምነት ጨምርልን (ሉቃ. 17፡5) እንበለው ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ይቻላል..እናምናለን አለማመናችንን እርዳው ብለን እንጸልይ (ማር. 9፡23-24)፡፡
ተስፋ መቁረጥ ባለበት መጽናናት እንዲመጣ እንጸልይ
በኑሮ ውስጥ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ያጋጥሙናል፣ አሁንስ ተስፋዬ ማነው የምንልበት ወቅት ይኖራል፤ ይሄኔ ነው አጽናኝ የምንፈልገው፣ የተስፋ ጭላንጭል መኖሩን የሚያመላክተን አምላካችሁ ‹‹ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት›› (1ጴጥ 5፡7) የሚለንን ሰው ነው የምንሻው፡፡ የመጽናናት አምላክ ሲያጽናናን እኛም ተስፋ የቆረጡትንና ያዘኑትን እንድናጽናና አቅም እንዲጠን እንጸልይ፡፡ ‹‹የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና›› (2ቆሮ. 1፡3-5)። እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም እንደሚያውቅ እንገነዘብ ዘንድ (ናሆም 1፡7) እንጸልይ፡፡
ስለዚህ ‹‹ ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ›› በማለት (መዝ 43፡5) ደካማነታችንን በመቀበል ወደሚያሳርፈን አምላክ እንድንመጣና ልዝብ የሆነው ቀንበሩንና ቀላል የሆነው ሸክሙን ለመሸከም እሺ ማለት እንድንችል በተስፋ እንድንጓዝ እንጹም እንጸልይ (ማቴ. 11፡28-30)፡፡ ልባችን ሳይታወክ በእግዚአብሔርና በልጁ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማመን (ዮሐ. 14፡1) እናት ልጅዋን እንደምታጽናና የሚያጽናናንና (ኢሳ. 66፡13) ለዘላለም በማይጥለን አምላክ (ሰቆቃወ ኤርሚያስ 3፡31) እንድንበረታና ልባችን እንዲጠና (መዝ. 31፡24) እንጸልይ እንጹም፡፡ ‹‹አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው›› (መዝ. 39፡7)፡፡ ‹‹ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን›› (መዝ. 130፡7)፣ ምክንያቱም ‹‹በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው›› (ኤር 17፡7)፡፡
ሐዘን ባለበት ደስታ እንዲሰፍን እንጸልይ
የሰው ልጅ ሕይወት በትግል የታጀበ ለመሆኑ ሲናገር ኢዮብ እንዲህ ይላል ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን? አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ›› (ኢዮብ 7፡1-3)፡፡ በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ደስታን መፈለግ ሰውኛ ነው፡፡ ነገር ግን ደስታን ያለቦታው መፈለግ ትርፉ ድካም ነው፡፡ ስልጣንና ገንዘብ ኃብትና እውቀት የውስጥ ደስታን አይሰጡምና እውነተኛውን ደስታ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነውን ደስታ ለማግኘት እንጹም፡፡ ሰዎች ይህንን ደስታ ይቀምሱት ዘንድ እንጸልይ፣ ቃሉ የሚለው ‹‹ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ›› (ፊል. 4፡4) ስለሆነ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ እንደሚል (ነህምያ 8፡10) ዛሬን መደሰት እንድንችል እንጸልይ፡፡
ነገሮች እንዳሰብነው ባይሆኑም ልፋታችን የጠበቅነውን ያህል ባይከፍለንም በአምላካችን መደሰት እንድንችል እንጹም እንጸልይ ‹‹ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ 18 ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። 19 ፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል›› (ዕንባቆም 3፡17-19)፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን እና ጾማችንን በእናታችን በማርያም አማላጅነት ይቀበልልን!
የእግዚአብሔር መንግስት ይስፋ! አሜን!
† ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት