ፓትርያርክ ፒዛባላ እርቅና ሰላም እንዲወርድ በአስቸኳይ መጸለይ አለብን አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ነሐሴ 9 (በኢትዮጵያ ነሐሴ 16) ቀን የሚከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ ክብረ በዓልን በማስመልከት በቅድስት ሀገር ለሚገኙ ክርስቲያኖች ልባዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልእክት “አሰቃቂው ጦርነት” ከፍተኛ ስቃይና መከራን በማስከተሉ ከልብ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ፥ ይህ በመካከለኛው ምስራቅ ለወራት የዘለቀ ጦርነት ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ አከባቢው ላይ ያለው ሁኔታ በጥላቻ፣ ምሬትና ብጥብጥ የተሞላ በመሆኑ በመካከለኛው ምሥራቅ ለተፈጠረው ግጭት መፍትሔ ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን በቁጭት ተናግረዋል።
ፓትሪያርክ ፒዛባላ “በህዝባችን የየዕለት ህይወት ላይ ያለው ተጽእኖ ከበፊቱ በበለጠ እና በከፋ ሁኔታ ህዝቡን እያሰቃየ የሚገኘው የዚህን ግጭት መደምደሚያ ለመገመት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ሲሉ ጽፈዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ይላሉ ፓትሪያርኩ፥ “ብዙ ሁከት እና ንዴት በአከባቢው በጉልህ በሚታይበት ሁኔታ ስለወደፊቱ እና ስለሰላማዊ ግንኙነቶች ውይይት የሚያደርጉ ሰዎችን እና ተቋማትን ማግኘት ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ብለዋል።
ጸሎት ለድንግል ማርያም
ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ወደፊት ያሉት ቀናት በግጭቱ ላይ ያለውን ማዕበል ለመቀየር እድሎችን እንደሚሰጡ፣ በተለይም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል በምናከብርበት ወቅት በጸሎት ከተጋን ብዙ ተስፋ ይኖረናል በማለት ፓትርያርክ ፒዛባላ ጠቁመዋል።
የእርገት በዓሉን በምናከብርበት ወቅት ከቅዱስ ቁርባን ሥነ ስርዓት በኋላ ወይም በፊት ባሉ አመቺ ጊዜያት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአማላጅነት ጸሎትን እንድንጸልይ አደራ በማለት ሁሉም ሰው ስለ እርቅና ሰላም አጥብቆ እንዲጸልይ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንንም በማስመልከት “አብያተ ክርስቲያናት፣ ምዕመናን እና ሐዋርያዊት የሃይማኖት ማኅበረሰቦች እንዲሁም በመካከላችን ያሉት ጥቂት መንፈሳዊ ነጋዲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ በሰጠነው የሰላም ጥያቄ ላይ አንድ እንዲሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
ለሰላም የሚቀርቡ ጸሎቶች እየተሰቃዩ ያሉትን ለመርዳት እና አብሮነታችንን ለማሳየት ከምናደርገው ጥረት ጎን ለጎን አብሮ መሆን አለበት ሲሉ ፓትርያርክ ፒዛባላ አስታውሰው፥ ብዙ ጊዜ ሲነገር ከምንሰማቸው የጥላቻ ቃላት ፊት ሆነን “የእርቅና የሰላም ቃላትን የያዘ ጸሎታችንን ልናቀርብ እንፈልጋለን” ብለዋል።
ጸሎት ለእመቤታችን
ፓትሪያርክ ፒዛባላ በማጠቃለያቸውም “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በአማላጅነቷ ለሁላችንም እንዲሁም ለዓለም በሙሉ የብርሃን ፍንጣቂን ትከፍታለች” በማለት ለእመቤታችን የፍልሰታ በዓል የሚቀርብ የሚከተለውን ጸሎት አቅርበዋል፦
የተከበሽ የእግዚአብሔር እናት ሆይ!
ከመላዕክት ዝማሬ በላይ ከፍ ከፍ ያልሽ ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ጋር ጸልይልን
ከሰማይም መላዕክትና ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ጸልይልን።
ለቅዱስና ለተወደደው ልጅሽ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማልጂን፣ ለዚህች ቅድስት ሀገር፣ ለልጆቿ በሙሉ እና ለሰው ልጆች ሁሉ የእርቅ እና የሰላም ስጦታ እንዲወርድ ጸልይልን።
ትንቢትህ ይፈጸም ዘንድ እንጸልያለን፡-
ትዕቢተኞች በልባቸው አሳብ ተበታተኑ፣
ኃያላን ከዙፋናቸው ተገለበጡ።
እናም በመጨረሻም ትሑታን ይነሳሉ፣
የተራበ በመልካም ነገር ይጠግባል።
ሰላማውያን እንደ እግዚአብሔር ልጆች ይታወቁ፣
የዋሆችም ምድርን በስጦታ ይቀበሉ።
አንችን ከመላዕክት ዝማሬ በላይ ከፍ ከፍ ያደረገው
ልጅሽ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ይስጠን
የመንግሥቱን ዘውድ ያጎናጸፈሽ
በዘላለማዊ የክብር ዙፋን ላይ አስቀምጦሻል።
ክብርና ምስጋና ለዘላለም ለእርሱ ይሁን፡ አሜን።