ፈልግ

የኢየሩሳሌም ከተማ የኢየሩሳሌም ከተማ 

በኢየሩሳሌም የሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጦርነት የተጎዱ ክርስቲያኖችን እየደገፈ እንደሚገኝ ተነገረ

በእየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት አምልኮን የምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቅድስት ሃገር መስከረም 26 በተጀመረው ጦርነት ለተጎዱ የፍልስጤም ክርስቲያን ቤተሰቦች ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ድጋፍ ጋር በመሆን ያከናወናቸውን በርካታ ተግባራት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አሳትሞ ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ተነግሯል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከ11 ወራት በኋላ አሁንም በመካሄድ ላይ ባለበት ወቅት፣ የኢየሩሳሌም የላቲን ቤተክርስቲያ ሃገረስብከት፣ ለጋሾች በግጭቱ የተጎዱትን በአካባቢው የሚገኙትን የክርስቲያን ማህበረሰብ ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከኮቪድ ቀውስ በኋላ የክርስቲያን ቤተሰቦች አዲስ ችግር ገጥሟቸዋል
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ አብዛኛው የፍልስጤም ክርስቲያን ቤተሰቦች ሁሉንም የገቢ ምንጫቸውን በማጣታቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የገቡ ሲሆን፥ በዓለም አቀፉ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ሃገረ ስብከቱ ለእነዚህ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በመንበረ ፓትርያርኩ ድረ-ገጽ ላይ በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ጦርነቱ በተለይ በጋዛ፣ በዌስት ባንክ እና በእየሩሳሌም ውስጥ በሚገኙ ህዝቦች ላይ ታይቶ የማይታወቅ ችግር እያስከተለ መሆኑን አስታውሰው፥ “ምንም እንኳን ግጭቶች ለእኛ አዲስ ባይሆኑም፥ እንደዚህ አይነት ረጅም ጊዜ የወሰደ እና በህዝቡ ህይወት ላይ እንደዚህ ያለ ከባድ ተጽእኖ የፈጠረ ግጭት አጋጥሞን አያውቅም” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ልገሳ ለሃገረ ስብከቱ
የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ተከታይ የሆነች የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብጹእ ካርዲናል ፒየር ባቲስታ በቪዲዮው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በሃገረ ስብከታቸው እየተደረጉ ያሉ የእርዳታ ጥረቶችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያግዝ ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ያደረጉትን ጥሪ ተቀብለው ምላሽ ለሰጡ ግለሰቦች እና በጎ አድራጊ ተቋማት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ አሁን እየተደረጉ ያሉት ድጋፎች ለተጎዱት ሰዎች ምግብ ማከፋፈልን እና በጦርነቱ ምክንያት ሥራ ላጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርን እንደሚያካትት አብራርተዋል።

የምግብ ካርዶች ስርጭት እና የስራ እድሎችን መፍጠር                                                                                                     አዲስ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል “ወንዶችን እና ሴቶችን ያካተተ 279 ሰዎች በዌስት ባንክ እና በምስራቅ እየሩሳሌም ውስጥ የተረጋጋ እና የረጅም ጊዜ የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን” ከገለጸ በኋላ፥ “12 ሺህ የሚሆኑ ቤተሰቦች የምግብ ካርዶችን፣ የቤት የኪራይ ክፍያ ድጋፍ፣ የሕክምና እንክብካቤ እና የህጻናት ትምህርት ቤት አግኝተዋል” በማለት ዘግቧል።

ሃገረ ስብከቱ በጋዛ ውስጥ በሚገኘው የላቲን ሥርዓት የምትከተል የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ደብር ውስጥ ጊዜያዊ መጠለያ ላገኙ ከ1,000 በላይ የክርስትና እምነት ተከታዮች በገንዘብ፣ በምግብ እና በነዳጅ አቅርቦት ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በጦርነቱ የተፈናቀሉ 123 ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው አስተማማኝ ማረፊያ እና መደበኛ ምግብ ማግኘት እንደቻሉም አመላክቷል።

ከዚህም ሌላ ቪዲዮው ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሆኑ የሶስት ሰዎችን ምስክርነት ያቀረበ ሲሆን፥ ከነዚህም መካከል በተደረገለት ድጋፍ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መቀጠል የቻለ ተማሪ፣ ለታመመ ባለቤቷ ምግብና መድሃኒት እየተሰጣት የምትገኝ ሴት እና የቤት ኪራይ ወጪውን እንዲከፍል የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት አባት ይገኙበታል።

ክርስቲያኖች በቅድስት ሀገር እንዲቆዩ መርዳት
በሃገረስብከቱ የተሰራው ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ “ለጋሾች የሚያደርጉት ድጋፍ፥ የዕለት ተዕለት ተግባራችን የሆነውን በምድራችን ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን የምናደርገውን ጥረት ያግዛል” ካሉ በኋላ፥ “ከዚህም በተጨማሪ ድጋፉ ክርስቲያን ቤተሰቦች አከባቢያቸውን እንዳይለቁ እና በጋዛ እና በዌስት ባንክ ባለው ቀጣይነት ያለው ጦርነት ምክንያት መሰደድ እንዳይኖር ያግዛል” በማለት በተናገሩት መልዕክት በቅድስት ሀገር ለሚሰቃዩ ክርስቲያኖች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ ተጠቃሏል።

ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ የፀረ-ፖሊዮ ክትባቶችን ለመስጠት ዝግጅት ላይ ነው
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጋዛ ውስጥ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦትን የሚያደናቅፉ አደጋዎች እና በርካታ መሰናክሎች ቢኖሩም፥ ካሪታስ እየሩሳሌም በፍልስጤም ግዛት ውስጥ ላሉ ህዝቦች የጤና እንክብካቤን ለማረጋገጥ የተቻለውን ሁሉ ማድረጉን እንደቀጠለ ተቋሙ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።

በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሁለት ብሄራዊ ግብረሰናይ ሰራተኞቹን በአሳዛኝ ሁኔታ ያጣው የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የዕርዳታ ሥራ የሚሰራበትን ግዛቱን ለቆ እንደማያውቅ እና የህክምና ሰራተኞቹን በጋዛ ሰርጥ ለሚገኙ ህፃናት አስቸኳይ የፀረ-ፖሊዮ ክትባቶችን እንዲሰጡ እያዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።

በጋዜጣዊ መግለጫው መሰረት ከዘጠኙ የጤና ተቋማት ሁለቱ ለደህንነት ሲባል አገልግሎት መስጠት ስላቆሙ 14 የህክምና ቡድኖችን በማስተባበር ሰባቱ ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በጋዛ ከተማ በሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ቤተክርስቲያን ቁምስና እንደሚገኝ እና ሌሎቹ ከዋዲ ጋዛ ወንዝ በስተደቡብ፣ በኑሴይራት፣ ካንዮኒስ እና ዴር አል ባላህ ውስጥ እንደሚገኙ እና በእነዚህ አከባቢዎች አገልግሎቱን መስጠት ከባድ እና ለሰራተኞቹ እጅግ በጣም አደገኛ እንደሆነ ተገልጿል።
 

30 August 2024, 13:38