ብጹዕ አቡነ ሮቤርቶ ጋአ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ብጹዕ አቡነ ሮቤርቶ ጋአ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ  

“የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ተጽዕኖ የእግዚአብሔርን ምሕረት መጋራት እንጂ ተወዳጅነትን መፈለግ አይደለም

በተሳሳተ መረጃ እና በውሸት ዜና በተሞላው ዓለማችን ውስጥ የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ተጽዕኖ የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ርኅራኄ እና ደግነት መጋራት እንደሆነ አቡነ ጆሴ ራፓዳስ ከካቶሊክ መገናኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አቡነ ጆሴ ራፓዳስ በቃለ ምልልሳቸው እንደተናገሩት፥ እነዚህን በጎ ምግባሮች በአገልግሎታቸው ውስጥ በማካተት የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለም ውስጥ እንዲታይ እና እንዲወደስ ማድረጋቸውን አስረድተው፥ “የቤተ ክርስቲያን ውጤታማ እና ትክክለኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን…የእግዚአብሔርን ምህረት እና ርህራሄ መመስከር አለብን” ብለው፥ “በደግነት ለዚህ ዓላማ ስንመሰክር መላው ዓለም የእግዚአብሔርን መንግሥት ያደንቃል፤ ይህም የማኅበራዊ ግንኙነታችን አስፈላጊ ተግባር ነው” በማለት አፅንዖት ሰጥተዋል።

ብጹዕ አቡነ ጆሴ ራፓዳስ ይህንን የተናገሩት በፊሊፒ ሊፓ ከተማ በተካሄደው ብሔራዊ የካቶሊክ ማኅበራዊ መገናኛዎች ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ሐምሌ 30/2016 ዓ. ም. በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት ነው። እስከ ነሐሴ 8/2016 ዓ. ም. በቆየው ዝግጅት ላይ ከ300 በላይ የማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎት ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የማኅበራዊ መገናኛ አገልግሎት በርካታ ወዳጆችን እና ተከታዮችን ለማግኘት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያንፀባርቁ እውነቶችን እና እሴቶችን ለሌሎች ማካፈል መሆኑን ብጹዕ አቡነ ጆሴ አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው በማከልም፥ “ከኢየሱስ ጋር ያለንን ግንኙነት በድፍረት ለሌሎች እንድናካፍል እና በሕይወታችን ያለውን የለውጥ ሃይል እንድንመሰክር ተጠርተናል” ብለው፥ ምሥክርነት መስጠት ማራኪ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በፊሊፒን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የሚገኝ የማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ ባዘጋጀው የአራት ቀናት ስብሰባ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” በሚቀርብ ዲጂታል የወንጌል ስርጭት ሚና ላይ ውይይቶችን ተካሂዷል።

ለስብሰባው መክፈቻነት የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥር ዓት
ለስብሰባው መክፈቻነት የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥር ዓት

ማክሰኞ ሐምሌ 30/2016 ዓ. ም. የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት ብጹዕ አቡነ ሮቤርቶ ጋአ፥ ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ AI” ኃይለኛ መሣሪያ ሆኖ ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚያመቻች ቢሆንም፣ የጋራ ጥቅምን ለማስተዋወቅ የሚያስፈልገው ሰብዓዊ ጥበብ እንደጎደለው ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮው ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ፥ ሠራሽ አስተውሎት “AI” የሰውን ልብ ጥበብ በፍፁም ሊተካ እንደማይችል አስረድተዋል።

“ከሌላ ልብ ጋር ከሚያስተጋባ ልብ የሚመጣ ሳይሆን እኛ ራሳችን ነን” ሲሉ አቡነ ሮቤርቶ ተናግረው፥ ሌሎችን የሚያዳምጥ እና የሚለማመድ፣ ለሌሎችም የሚያካፍል ልብ እንደያዝን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

 

08 August 2024, 13:31