ፈልግ

የር.ሊ.ጳጳሳት የ2024 የሲንጋፖር ጉብኝት የማስታወሻ ቁሳቁሶች የር.ሊ.ጳጳሳት የ2024 የሲንጋፖር ጉብኝት የማስታወሻ ቁሳቁሶች  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ሲንጋፖር ለሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ሲንጋፖር ለሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት 40 ቀናት ብቻ የቀሩ ሲሆን፥ በእነዚህ አጭር ቀናት ውስጥ ከተለያዩ ኮሚቴዎች የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች በከተማዋ ከዚህን በፊት ታይቶ የማይታወቅ ትልቅ ሃይማኖታዊ ዝግጅት ለማዘጋጀት ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከነሃሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በእስያን እና ኦሺኒያ አህጉራት ሃዋሪያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይታወቃል፥ ከነዚህም ሃገራት ውስጥ ከመስከረም 1 እስከ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ሲንጋፖርን እንደሚጎበኙ የጉብኝት መርሃግብራቸው ያሳያል። 

የካቶሊክ ፋውንዴሽን ይፋዊ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን የ2024 የሲንጋፖር ጉብኝት የመታሰቢያ ቁሳቁሶችን ለህዝብ ይፋ አድርጓል ሲል የዘገበው ‘ካቶሊክ ኒውስ ኤስጂ’ የተባለው የሲንጋፖር ሃገረስብከት የዜና ጣቢያ ነው።

እነዚህ የማስታወሻ ቁሳቁሶች ቲሸርቶችን፣ ጃንጥላዎችን፣ ኮፍያዎችን፣ የውሃ ጠርሙሶችን፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አየር ማቀዝቀዣዎችን እና የጸሎት ቁሳቁሶችን እንደሚያካትት የተገለጸ ሲሆን፥ እነዚህን እቃዎች በቀጥታ የድህረ-ገጽ ሽያጮች ላይ እና ‘በስሪ ፖፕ አፕ’ በተባሉ መደብሮች ማግኘት እንደሚቻል ተጠቁሟል።

1,600 የሚሆኑ ከተለያዩ ደብሮች እና ከካቶሊክ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ዘማሪያንን ያቀፈው የጳጳሳዊ ሥርዓተ ቅዳሴ መዘምራን ከሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ልምምድ እንደጀመረ እና የተለያዩ ወረዳዎችን የሚወክሉ ስድስት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ልምምዶቹን እንዳካሄደ ተነግሯል።

በመስከረም ወር ውስጥ የሚካሄደው የመጨረሻው ልምምድ የመዘምራን ቡድን እና ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተዋቀሩ ቡድኑችን አንድ ላይ በማምጣት 1,800 አባላት ያሉት ስብስብ እንደሚሆንም ተገልጿል።

‘የስታዲየም ንኡስ ኮሚቴ’ ሀምሌ 14 ላይ ተሰባስቦ ጳጳሳዊው ሥርዓተ ቅዳሴ በብሄራዊ ስታዲየሙ ለማከናወን በሚቻሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት ተገናኝቶ ተወያይቷል። ስብሰባው ያተኮረው ዝግጅቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጥበቃ፣ የጸጥታ፣ የትራፊክ ቁጥጥር እና የህክምና ቡድኖችን በማደራጀት ላይ ነው።

የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ ስለ ጳጳሱ ጉብኝት መረጃ ሲያሰራጭ ቆይቷል።
ቡድኑ በዲጂታል እና በህትመት ሚዲያዎች ዙሪያ የሚሰሩ ጸሃፊዎችን፣ ቪዲዮ አንሺዎችን እና የማህበራዊ ሚዲያ አዘጋጆችን ለህዝቡ መረጃ እንዲሰጡ እና ዝግጅቶቹን በሰነድ እንዲመዘግቡ ማድረግን ያካትታል።

የቲኬት ንኡስ ኮሚቴ የምዝገባ ችግሮችን ለመፍታት እና የቲኬት ጉዳዮችን ለማሳለጥ በትጋት ሲሰራ ቆይቷል። ቡድኑ ከሃምሌ 15 እስከ 19 ድረስ ምዕመናን በ myCatholicSG አካውንታቸው በኩል ተመዝግበው በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ እንዲችሉ ለመርዳት አምስት ቁምስናዎችን ጎብኝቷል።

 

08 August 2024, 15:49