ፈልግ

በማይናማር በሚገኙ የካኖሳዊያን ገዳማዊያት የሚተዳደር ማዕከል በማይናማር በሚገኙ የካኖሳዊያን ገዳማዊያት የሚተዳደር ማዕከል 

የሲንጋፖር መነኮሳት በግጭት ውስጥ ላለችው ማይናማር የተስፋ ጭላንጭል መሆናቸው ተነገረ

ሲስተር ጃኔት ዋንግ በግጭት በምትታመሰው ማይናማር የካኖሲያን ማህበር ገዳማዊያት እየሰሩት ስለሚገኘው ስራ ሲያብራሩ መምህራንን በማሰልጠን እና ወጣቶችን በማስተማር ተስፋ ሰጪ የሆነ ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በ 2013 ዓ.ም. ወታደራዊው ጁንታ በማይናማር ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ ወደማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ የገባች ሲሆን፥ ቀድሞውንም አስቸጋሪ የነበረው ሰብአዊ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሷል።

ለበርካታ አስርት ዓመታት ከሲንጋፖር የመጡትየካኖሳዊያን የበጎ አድራጎት ሴት ልጆች ማህበር በማይናማር ውስጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ የሃይማኖት ጉባኤ ሲሆን፥ ለሃገሪቱ ወጣቶች የወደፊት ብሩህ ተስፋ ለመገንባት በማለም ሰፋፊ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ይሄንን አስመልክተው የካኖሲያ ማህበር አባል የሆኑት ሲስተር ጃኔት ዋንግ በማይናማር ስላለው የሃይማኖት ጉባኤያቸው ተግባራት ለማብራራት ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የወደፊት መምህራንን ማሰልጠን
ሲስተር ጃኔት በቃለ ምልልሳቸው ወቅት እንደገለጹት የካኖሲያን ገዳማዊያት ከሲንጋፖር ወደ 2,000 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በምትገኘው ማይናማር ለመጀመሪያ ጊዜ የገቡት በ 1988 ዓ.ም. እንደሆነ በማስታወስ፥ ገዳማዊያቱ በወቅቱ ወደ ስፍራው ለመጓዝ ያነሳሳቸው የበርማ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹእ አቡነ ማትያስ ዩ ሽዌ ባቀረቡት የእርዳታ ጥሪ መሠረት እንደሆነ አብራርተዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ለገዳማዊያቱ ጥሪ ያደረጉት የሃገሪቱን ወጣቶች እንዲያስተምሩ እና ወጣት ወንጌላውያን ቡድኖችን በማቋቋም እንዲረዷቸው በማሰብ እንደሆነ የጠቀሱት ሲስተር ጃኔት፥ በጎ ፈቃደኞች ከሲንጋፖር ወደ ማይናማር በመደበኛነት ለሚስዮናዊ ጉዞዎች ከአስር ዓመታት በላይ ይጓዙ እንደነበር ገልጸው፥ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች ከአመራርነት ስልጠናዎች እስከ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመሳሰሉ ሁሉንም ዓይነት ኮርሶች ያደራጁ ነበር ብለዋል።

በ 2000 ዓ.ም. ካኖሳዊያን በወቅቱ አነስተኛ ቁጥር ለነበራቸው የገዳማዊያት ቡድን እና ድጋፍ ሰጪ ሰዎች መኖሪያነት የሚያገለግል በሀገሪቱ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን ማዕከላቸውን ያቋቋሙ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማህበረሰብቡን “በፍቅር አገልግሉ” በሚል መሪ ቃል በመምህራን ምስረታ ላይ ያነጣጠረ ፕሮግራም ቀርጸው እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ በ 2004 ዓ.ም. ለመምህራን ምስረታ የሚያገለግል፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ማረፊያ ሆኖ የሚያገለግል ‘ካኖሳ ሆም’ ተብሎ የሚጠራውን የመኖሪያ ህንጻዎችን ገንብተዋል።

ከማዕከሉ ሰልጥነው የሚወጡ መምህራን በአከባቢው በሚገኝ አጥቢያ ቤተክርስትያን በሚተዳደሩ አዳሪ ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ ሙያዊ ስልጠና ማግኘት ለማይችሉ ህጻናት እና ታዳጊዎች አንድ ቀን ራሳቸው መምህራን እንዲሆኑ በማስተማር ጥራት ያለው እንክብካቤ እንዲሰጡ የሰለጠኑ እንደሆነ አብራርተዋል።

ማዕከሉ በ 2000 ዓ.ም. ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ገዳማዊያቱ ወደ 350 የሚጠጉ ወጣት ሴቶችን ያሰለጠኑ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ወደ መጡበት አከባቢ በመመለስ በመላው ማይናማር የሚገኙ ማህበረሰቦቻቸውን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ሲስተር ጃኔት ጠቁመው፥ ይህ በእንዲህ እንዳለ በ 2009 ዓ.ም. ገዳማዊያቱ በአካባቢው ለሚገኙ ህፃናት የሚያገለግል ተጨማሪ መዋዕለ-ህፃናት ትምህርት ቤት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

'የተስፋ በር': ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ስልጠና
ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ዓመት፣ ማለትም በ 2009 ዓ.ም. ገዳማዊያኑ የቱሪስት ማዕከል በሆነው በኢንሌ ሀይቅ አጠገብ “የተስፋ በር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሌላ ማእከል የከፈቱ ሲሆን፣ በዚህ ማዕከል ውስጥ ለወጣት ሴቶች በመስተንግዶው ዘርፍ በሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች ውስጥ ሥራ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ሥልጠና እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

በማይናማር ያለው አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይህንን ሥራ የበለጠ አጣዳፊ ያደርገዋል ያሉት ሲስተር ጃኔት፥ ሃገሪቷ በብዛት የምታመርተው የሩዝ ምርት ዋጋ እንኳን ሳይቀር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሦስት እጥፍ መጨመሩን እና የቱሪስት ኢንደስትሪው ውድቀት ብዙ ሰዎችን ያለ ሥራ ማስቀረቱን ገልጸዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም እንዲረዳ ካኖሲያውያን በየሳምንቱ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን እና ቤተሰቦቻቸውን ለሚረዳው ፕሮጄችት 300 የምግብ እሽጎችን እንደሚሰጥ ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶችን እንግሊዝኛ የማስተማር ጥረታቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ የገለጹት ሲስተር ጃኔት “ይህ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ለማስተማር የምናረገው ጥረት ልጆቹን ከተቀረው ዓለም ጋር እንዲገናኙ እንደሚያደርጋቸው እና ወደ ውጭ ሃገራት ሄደው ሥራ እንዲፈልጉ ያስችላቸዋል” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ገዳማዊያቱ በማዕከላቸው አቅራቢያ ከሚገኙ ማህበረሰቦች ጋር በመሆን “ቁሳዊ፣ ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍ ለማድረግ” ወደ ገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሚጓዙ የገለጹት ሲስተሯ፥ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት እግዚአብሔርን ለእነሱ ያለውን ፍቅር እና እንክብካቤ ለማሳወቅ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

ተስፋን በሕይወት ማቆየት
በ 2012 ዓ.ም. ከተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ገደቦች ምክንያት እና አልፎም በ 2013 ዓ.ም. ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ጀምሮ ከሲንጋፖር የሚመጡ በጎ ፈቃደኞች ወደ ማይናማር መጓዝ አልቻሉም ነበር።

በሲንጋፖር ውስጥ ያሉ ገዳማዊያት እህቶች እና በጎ ፈቃደኞች የምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ያካተቱ የእርዳታ ጥቅሎችን በመላክ ላይ ይገናኛሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በማይናማር ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች በስድስት የአካባቢው ተወላጅ በሆኑ የካኖሳዊያን ገዳማዊያት እና በአንድ ከሲንጋፖር በመጡ ልምድ ባላቸው መነኩሴ ሥልጠና በወሰደች የአከባቢው ምእመን እንደሚመሩ የተገለጸ ሲሆን፥ ወሩ በገባ በ13ኛው ቀን ለፋጢማ እመቤታችን ክብር፥ ገዳማዊያት፣ በጎ ፍቃደኞች፣ መምህራን እና በሁለቱም ሃገራት ማለትም በማይናማር እና ሲንጋፖር ውስጥ ያሉ ልጆች በበይነ መረብ አማካይነት ተገናኝተው የመቁጠሪያ ጸሎት እንደሚያደርጉ እና ለማይናማር ሰላም እንዲወርድ ጸሎት እንደሚያደርሱ ሲስተር ጃኔት ዋንግ ገልጸው፥ “ከምንም በላይ አሁን የሚያስፈልገን ሰላምና ስምምነት ነው” በማለት አጠቃለዋል።
 

29 August 2024, 14:50