የነጻነት ትግል የካቶሊክ እምነት በቲሞር-ሌስቴ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቲሞር ሌስቴን የጎበኙ ሁለተኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ይሆናሉ፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 12 ቀን 1989 ዓ.ም በዋና ከተማይቱ ዲሊ አጭር ቆይታ ካደረጉት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በዚያው ዓመት የዓለምን ትኩረት በመሳብ በአፋኝ የኢንዶኔዥያ አገዛዝ ስር ያሉ የምስራቅ ቲሞር ሰዎችን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ዝግጅቶች
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሦስት ቀናት ቆይታቸው ከ35 ዓመታት በፊት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ቦታ በዲሊ በሚገኘው በታሲ ቶሉ ግቢ ውስጥ ከአካባቢው ቀሳውስት እና ገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ ወጣቶች እና ምእመናን ጋር ተገናኝተው ቅዳሴን እንዲመሩ ተወስኗል። ከ700,000 በላይ ምእመናን ከቲሞር-ሌስቴ እና ከአጎራባች ኢንዶኔዢያ እና ከሌሎች ሀገራት የመጡ ምእመናን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በእስያ ትንሿ ሀገር (እ.ኤ.አ. በ2002 ዓ.ም ነፃነቷን ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ትግል እና አለመግባባት በኋላ ባገኘችው እና በ1999 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የተደገፈ ህዝበ ውሳኔ ነጻነቷን የተጎናጸፈች አገር ናት) ከ96% በላይ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ለጉብኝቱ ቅድመ ዝግጅት እያጧጧፉ ነው።
የቲሞር-ሌስቴ ጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊ አባ ቤንቶ ፔሬራ ለፊደስ ኤጀንሲ እንዳብራሩት፣ ዝግጅቱ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ነው፣ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚነበበው ልዩ ጸሎት እና ዑደት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮ እና በጉብኝቱ ማዕከላዊ ጭብጥ ላይ 'እምነትህ ባህልህ ይሁን' በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው።
በቲሞር ሕዝብ የካቶሊክ እምነት፣ በባህላቸው እና በታሪካቸው መካከል ያለው ግንኙነት
የዲሊ ሊቀ ጳጳስ እንደራሴ ሆነው የሚያገለግሉት አባ ግራሲያኖ ሳንቶስ ባሮስ ለፊደስ እንደተናገሩት የተመረጠው መሪ ቃል የቲሞር ካቶሊኮች እምነታቸውን ከባህላዊ ቅርሶቻቸው ጋር አስማምተው እንዲኖሩ የቀረበ ግብዣ ነው። እንደራሴው አክለው እንደገለጹት ከሆነ በካቶሊክ እምነታቸው እና በኢንዶኔዥያ ወረራ ውስጥ በነበሩት አስርት ዓመታት መካከል ያለውን የጠበቀ ትስስር የሚያስታውስ መሆኑን ተናግረዋል።
“እምነት በእያንዳንዳችን መከራና ተስፋ ውስጥ አጅቦናል” ሲሉ ተናግሯል “ዛሬ ለነጻነት ህዝበ ውሳኔ ከተካሄደ 25 ዓመታት በኋላ ታሪካችንን በታረቀ ልብ ማየት እንችላለን፣ የእግዚአብሄርን ስራ ያበራልናል። በብዙ ወሳኝ ጊዜያት ውስጥ የሰዎች አእምሮ እና ልብ" ውስጥ እምነት ውሳኝ ነገር ነበር ብለዋል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን በፖርቹጋላዊው (የቀድሞ የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ነበረች አገሪቷ) የተሰበከ ታሪክ በ25 ዓመታት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ትግል ውስጥ ትልቅ ሚና ከተጫወተችው ቤተክርስትያን ጋር በቅርበት እየተሰቃየ ካለው የምስራቅ ቲሞር ህዝብ ጋር በመቀራረብ እና የተፈጸመውን ግፍ በማውገዝ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው።
የቲሞር ቤተ ክርስቲያን ለነጻነት በሚደረገው ትግል ውስጥ ያላት ትልቅ ሚና
የዲሊ የቀድሞ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪዎች የሆነበሩት ጳጳሳት አቡነ ማርቲኖ ዳ ኮስታ ሎፔስ፣ አልቤርቶ ሪካርዶ ዳ ሲልቫ እና ካርሎስ ዚሜኔስ ቤሎ፣ ስማቸው አሁንም በቲሞር ሰዎች ልብ ውስጥ ይገኛል። ይህ ሰላማዊ ትግልን ለመደገፍ ቁርጠኝነት የሳሌዢያን ጳጳስ ካርሎስ ዚሜኔስ ቤሎ የ1996 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ሽልማትን ከነፃነት መሪ እና ከወደፊቱ ፕሬዝደንት ሆሴ ራሞስ ሆርታ ጋር ተካፍሏል። እንዲሁም በዚያን ጊዜ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ካቴኪስቶች እና ገዳማዊያን/ገዳማዊያት ለተሰቃዩ ሰዎች ያላቸውን ቅርበት በማሳየት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡- “ሁልጊዜ ቅርብ ነበሩ፣ እጣ ፈንታችንን ይጋሩ ነበር” ሲሉ አባ ባሮስ ተናግሯል።
ካቶሊኮች ከህዝቡ 95 በመቶውን ይይዛሉ
ይህ ቅርበት እና ድጋፍ በቲሞር-ሌስቴ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል፤ እነዚህም ዛሬ ከ1.4 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 95 በመቶ ያህሉ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ናቸው።
ይህ የሚያሳየው ምንድነው ሲባል “በጭቆና ጊዜ፣ እምነት ለሰዎች መሰረታዊ ምሰሶ ነበር” ሲሉ የዲሊ አገረስብከት እንደራሴ የሆኑት አባ ባሮስ “የምስራቅ ቲሞር ሰዎች በተከፈተ ልብ፣ ወንጌል ብቸኛው መንገድ፣ ብቸኛው መዳን እንደሆነ በራሳቸው ተረድተው ነበር፡ ወደ ጌታ ጮኹ፣ በእርሱ ታምነዋል እናም ጌታ ጸሎታቸውን ሰማ፣ እየመራቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ይዟቸው ሄዷል” ሲሉ እንደራሴው ተናግሯል።