ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤   (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ:- "እየሰፋ የሚሄድ ፍሬያማነት"

አንዳንድ ባለትዳሮች ልጅ መውለድ አይችሉም። ይህም ለእነርሱ ተጨባጭ የሥቃይ ምክንያት እንደሚሆንባቸው እናውቃለን። በተመሳሳይ “ጋብቻ የተመሠረተው ልጆችን ለመውለድ ብቻ” እንዳልሆነ እናውቃለን። “…የባለትዳሮች ጥልቅ ምኞት ቢኖርም፣ ልጆች በሌሉባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ጋብቻ የሕይወት ምሉእ ምግባርና ሱታፌ ሆኖና እሴቱንና የማይፈርስ የመሆኑን ባሕርይ ይዞ ይቀጥላል።” እንደዚሁም፥ “እናትነት ሥነ ሕይወታዊ እውነታ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች የሚገለጽ ነው።”

ጉዲፈቻ ወላጆች ለመሆን ትልቅ የልግስና መንገድ ነው። ስለዚህ ልጅ መውለድ የማይችሉ ባለትዳሮች ተገቢ የቤተሰብ ሁኔታ ያልተመቻቸላቸውን ሕጻናት ለማቀፍ የጋብቻ ፍቅራቸውን እንዲያሰፉ እመክራቸዋለሁ። ለጋስ በመሆናቸው ከቶ አይጸጸቱም። ልጅን በጉዲፈቻ ማሳደግ፣ የቤተሰብ ስጦታ ለሌለው ቤተሰብ የሚደረግ ትልቅ የፍቅር ሥራ ነው። ከሁሉ በላይ ያልተፈለጉ ሕጻናት ባሉበት ሁኔታ ውርጃን ወይም ወልዶ መጣልን ለመከላከል እንዲቻል የጉዲፈቻን ሂደት የሚያቃልል ሕግ መኖር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። አንድን ሕጻን ያለ ቅድመ ሁኔታ በልግስና በጉዲፈቻ የመቀበል ፈተናን የሚጋፈጡ የእግዚአብሔር የፍቅር መሣሪያ ይሆናሉ። ‹‹እናትሽ ብትረሳሽ እንኳ እኔ አልረሳሽም›› (ኢሳ. 49፡15) ተብሎ ተጽፎአልና።

“የጉዲፈቻና የማደጎ ምርጫ፣ በመካንነት ረገድ ብቻ ሳይሆን፣ በጋብቻ ተሞክሮ ውስጥ ልዩ የፍሬያማነት መገለጫ ነው። የራስ እርካታን እንደ ማሟያ መብት ተደርጎ ከሚቆጠረውና ማናቸውንም መሥዋዕትነት ከፍሎ ልጅ የማግኘት ምኞትን ከማሳካት ሁኔታ አንጻር ሲታይ፣ ጉዲፈቻና ማደጎ፣ በትክክል ከተረዱአቸው፣ የወላጅነትንና ልጆች የማሳደግን ዋና ገጽታ የሚያሳዩ ናቸው። በተፈጥሮ፣ በጉዲፈቻ ወይም በማደጎ የተገኙ ሕጻናት ወደዚህ ዓለም መምጣትን ብቻ ሳይሆን፣ ተቀባይነትን፣ መወደድንና ክብካቤን የሚሹ የራሳቸው የሆነ መብት ያላቸው ሰዎች ናቸው። በማናቸውም የጉዲፈቻና የማደጎ ውሳኔዎች ውስጥ የሕጻኑ መሠረታዊ ፍላጎቶች ምንጊዜም ቢሆን ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል።” በሌላ በኩል፣ “በአገሮችና በአህጉሮች መካከል የሚካሄድ የሕጻናት ሕገ ወጥ ዝውውር በተገቢ ሕጋዊ እርምጃና መንግሥታዊ ቁጥጥር ሊወገድ ይገባል።”

ተዋልዶና ማደጎ የፍቅርን ፍሬያማነት መለማመጃ ብቸኛ መንገዶች እንዳልሆኑ ማስታወስ ያስፈልገናል። ሰፊ ቤተሰቦች እንኳ በኅብረተሰቡ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩና ሌሎች የፍሬያማነትን መገለጫዎች የሚያሳድግ ፍቅርን እንዲሹ ተጋብዘዋል። ክርስቲያን ቤተሰቦች “እምነት ከዓለም እንደማያስቀረን፣ ይልቁንም ይበልጥ ወደ ዓለም ውስጥ እንደሚያስገባን…” ከቶ መርሳት የለባቸውም። “በመሠረቱ፣ እያንዳንዳችን ለእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ዓለማችን መምጣት የምንጫወተው ልዩ ሚና አለን።” ቤተሰቦች ራሳቸውን ከህብረተ ሰብ መሸሸጊያ አድርገው ማየት የለባቸውም፤ ይልቁንም ከሌሎች ጋር በመተባበር መንፈስ ወደ ኅብረተሰብ መቅረብ ይኖርባቸዋል። በዚህ ዐይነት፣ ቤተሰቦች ሰዎችን ከኅብረተሰብ ጋር የሚያዋህዱ መገናኸሪያዎችና በሕዝባዊና ግላዊ መስኮች የመገናኛ ነቁጦች ይሆናሉ። ባለትዳሮች ስለ ማኅበራዊ ግዴታዎቻቸው የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። በዚህም መንገድ፣ ፍቅራቸው በመቀነስ ፈንታ በአዲስ ብርሃን ይጥለቀለቃል። ገጣሚው እንዳለው፥ “እጆችህ አሻሹኝ፣ ቀኖቼን የሚሞላ ኅብር ሆኑልኝ። እኔም አንተን የምወደው እጆችህ ጽድቅን ቢያደርጉ ነው። ብወድህ፣ አንተ ፍቅሬ፣ ባልንጀራዬና ሁሉም ነገሬ ብትሆን ነው፤ በጎዳና ላይ፣ ጎን ለጎን ስንሆን፣ ከሁለት በላይ ነን” ።

ራሱን ከሌላ የተለየ ወይም “የተገለለ” አድርጎ የሚያይ ቤተሰብ ፍሬያማ ሊሆን አይችልም። ይህን ስጋት ለመከላከል፣ በጸጋና በጥበብ የተሞላው የኢየሱስ ቤተሰብ ራሱ ልዩ የሆነ ወይም ከሌላ የተለየ መስሎ እንዳልታየ ማስታወስ ይገባናል። ለዚህም ነው ሰዎች የኢየሱስን ጥበብ ማወቅ የከበዳቸውና “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ አናጢው የማርያም ልጅ አይደለምን (ማር. 6፡ 2-3)? “ይህ የአናጢው ልጅ አይደለምን (ማቴ. 13፡ 55)? በማለት የተደነቁት። እነዚህ ጥያቄዎች የእነርሱ ቤተሰብ ተራ ቤተሰብ፣ ለሌሎች የቀረበ፣ የማኅበረሰቡ መደበኛ አካል እንደ ሆነ በግልጽ ያሳያሉ። ኢየሱስ ያደገው ከማርያምና ከዮሴፍ ጋር በጠባብና አፋኝ በሆነ ግንኙነት ውስጥ ሳይሆን፣ ከሰፊው ቤተሰብ፣ ከወላጆቹ ዘመዶችና ከጓደኞች ሁሉ ጋር በመግባባት ነበር። ይህም፣ ከኢየሩሳሌም መልስ በጉዞ ላይ ሳሉ፣ ማርያምና ዮሴፍ የአሥራ ሁለት ዓመቱ ልጅ ኢየሱስ ስለ ሰዎች ታሪክ እየሰማና ጭንቀታቸውን እየተጋራ ከመንገደኞች ጋር የነበረ የመሰላቸው በዚህ ምክንያት እንደ ሆነ ያስረዳል። ‹‹ከመንገደኞች ጋር ያለ መስሎአቸው የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ” (ሉቃ. 2፡ 44)። አሁንም ቢሆን፣ አንዳንድ ክርስቲያን ቤተሰቦች፣ በkንk አጠቃቀማቸው፣ በድርጊታቸው ወይም በአያያዛቸው፣ ወይም አንድን ነገር ሁለቴ ወይም ሶስቴ ደጋግመው በመናገራቸው ምክንያት ከማኅበረሰቡ የራቁና የተለዩ መስለው ይታያሉ። በእነርሱም ምክንያት ዘመዶቻቸው እንኳ የተናቁ ወይም የተኮነኑ ይመስላቸዋል።

የፍቅርን ኃይል በተግባር የሚለማመዱ ባለትዳሮች ግን ይህ ፍቅር የተገፉ ሰዎችን ቁስል የሚጠግን፣ የግንኙነት ባህልን የሚያዳብርና ለፍትህ የሚታገል መሆኑን ያውቃሉ። እግዚአብሔር ለቤተሰብ ዓለምን “የመግራት” እና እያንዳንዱ ሰው ሌሎች ሰዎችን እንደ ወንድሞችና እህቶች እንዲመለከት የመርዳትን ኃላፊነት ሰጥቶታል። “የዛሬ ወንዶችንና ሴቶችን የየዕለት ኑሮ በትኩረት መመልከት፣ የቤተሰብ መንፈስ የማስረጽን የላቀ አስፈላጊነት ያሳያል።… የመደበኛ ሕይወት አደረጃጀት ከመሠረታዊ የሰው ልጅ ትስስሮች ፈጽሞ በራቀና ውጣ ውረድ በበዛበት አሠራር ምክንያት ይበልጥ እየተጨናገፉ ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግብረ ገቦችም ጭምር የመላሸቅ ምልክት እያሳዩ ናቸው”። (206) ግልጽና ተንከባካቢ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ ለድሆች ቦታ ያመቻቻሉ፣ ከራሳቸው ያነሰ ዕድል ካጋጠማቸው ጋር ወዳጅነትን ይመሠርታሉ። በወንጌል ምክር መሠረት ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት “ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” (ማቴ. 25፡ 40) የሚለውን የኢየሱስን ቃላት ይገነዘባሉ። ሕይወታቸው፥ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ፣ በአጸፋው እንዳይጋብዙህና ብድራትህን እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ከበርቴ ጎረቤቶችህን አትጋብዝ። ነገር ግን፣ ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድሆችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስውሮችን ጥራ፤ ትባረካለህም” (ሉቃ. 14፡ 12-14) የሚለውን ከሁላችን የሚጠበቀውን የውዴታ ግዴታ በተጨባጭ መንገድ ያንጸባርቃል። አዎን ትባረካላችሁ። የደስተኛ ቤተሰብ የደስታ ምሥጢር ያለው እዚህ ላይ ነው።

ቤተሰቦች በምስክርነታቸውና በአንደበታቸው ስለ ኢየሱስ ለሌሎች ይናገራሉ። እምነትን ያስተላልፋሉ፣ ስለ እግዚአብሔር ያለውን ምኞት ይቀሰቅሳሉ፣ የወንጌልን ውበትና የአኗኗር ሁኔታውን ያንጸባርቃሉ። ስለዚህ፣ ክርስቲያን ጋብቻዎች በወንድማማችነት ምሥክርነታቸው፣ በማኅበራዊ ክብካቤአቸው፣ በችግረኞች ስም በግልጽ በመናገራቸው፣ በአንጸባራቂ እምነታቸውና በንቁ ተስፋቸው ኅብረተሰብን ያደምቃሉ። የእነርሱ ፍሬያማነት ይሰፋል፣ በአያሌ መንገዶችም የእግዚአብሔር ፍቅር በኅብረተሰብ ውስጥ እንዲሰፍን ያደርጋል።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 179-184 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ ዳንኤል ኃይለ

07 September 2024, 16:16