ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ "ጋብቻ እና ድንግልና"

“ያላገቡ ብዙ ሰዎች ለራሳቸው ቤተሰብ ትኩረት ከመስጠት ባሻገር፣ አብዛኛውን ጊዜ ባሉባቸው የወዳጅነት ቡድኖች፣ አባል በሆኑበት የቤተክርስቲያን ማኅበረሰብና በሙያ ሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ አገልግሎት ያበረክታሉ። አንዳንድ ጊዜ የእነርሱ መገኘትና አስተዋጽኦ ችላ ስለሚባል፣ የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ብዙዎች በበጎ አድራጎትና በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ሙያቸውን ለክርስቲያን ማኅበረሰብ አገልግሎት ያውላሉ። ሌሎቹ ሳያገቡ የሚኖሩት ሕይወታቸውን ለክርስቶስና ለባልንጀራ ፍቅር ስለሚቀድሱ ነው። የእነርሱ ለዓላማ መሠዋት፣ ቤተሰብን፣ ቤተክርስቲያንንና ኅብረተሰብን በእጅጉ ያዳብራል”።

ድንግልና የፍቅር ዐይነት ነው። የፍቅር ምልክት እንደ መሆኑም፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣትና ለወንጌል ዓላማ ሙሉ በሙሉ የመሰጠትን አስፈላጊነት ይነግረናል (ንጽ. 1 ቆሮ. 7፡ 32)። እንደዚሁም ‹‹የማያገቡበትና የማይጋቡበት (ማቴ. 22፡ 30) የሰማያዊ ፍጻሜ ነጸብራቅ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ድንግልናን የመረጠው የኢየሱስን ዳግመኛ መምጣት ተስፋ ስላደረገና ሁሉም ሰው ወንጌልን በማስፋፋት ላይ እንዲያተኩር ስለ ፈለገ ነው። ‹‹ዘመኑ አጭር ስለ ሆነ ነው›› (1 ቆሮ. 7፡ 29)። ይሁን እንጂ፣ ይህ የራሱ ሐሳብና የራሱ ምርጫ ብቻ (ንጽ. 1 ቆሮ. 7፡ 6-9) እንጂ ‹‹ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም›› ( 1 ቆሮ. 7፡ 25) በማለት የክርስቶስ ትእዛዝ እንዳልሆነ ግልጽ አድርጎአል። እንደዚሁም፣ የተለያዩ ጥሪዎችን ዋጋ መገንዘቡን ሲገልጽ፡- ‹‹እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለው የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው›› (1 ቆሮ. 7፡7) ይላል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይህን ሐሳብ በማስተንተን ሲናገሩ፣ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ወሲባዊ እቀባን መሠረት በማድረግ “የጋብቻን የበታችነት” ወይም የድንግልናን ወይም የብህትውናን “የበላይነት” የሚያረጋግጥ ምክንያት እንደሌላቸው›› አስረድተዋል። የድንግልናን የበላይነት አረጋግጦ ከመናገር ይልቅ የተለያዩ የሕይወት ሁኔታዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆናቸውን፣ ከዚህም የተነሣ አንዳንዶቹ በአንድ በኩል ይበልጥ ፍጹም ሌሎቹ ደግሞ በሌላው ፍጹም እንደሆኑ ማመልከቱ በቂ ይሆናል። አሌክሳንደር ዘሐሌ፣ ለምሳሌ፣ ጋብቻ፣ ‹‹ክርስቶስ ከቤተክርስቲያን ጋር ያለውን አንድነት ወይም የመለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያቱን አንድነት›› የሚያመለክት ትልቅ እውነታ እስከሆነ ድረስ፣ በአንድ በኩል ከሌሎች ምሥጢራት የበላይ ነው ተብሎ ሊገመት እንደሚችል አስረድቶአል። ስለዚህ ዋናው ቁም ነገር፣ ‹‹መታቀብን በመደገፍ የተክሊልን ዋጋ ዝቅ የማድረግ ጉዳይ አይደለም”። “አንዱን ደግፎ ሌላውን ለመጥላት ምንም ምክንያት የለም… አንድ ሰው አንድን የነገረ መለኮት ትውፊት ተከትሎ ‹ስለ ፍጽምና› ቢናገር፣ ይህ የሚያመለክተው ራሱን መታቀብን ሳይሆን፣ በወንጌላዊ ምክር ላይ የተመሠረተ አጠቃላይ ሕይወትን ነው››። ያገባ ሰው ከሁሉ የላቀ በጎ ሥራ ስለሚሠራ፣ ‹‹ለእነዚያ ምክሮች ታማኝ በመሆን ከዚያ በጎ ሥራ ወደሚፈልቅ ፍጽምና ይደርሳል። ይህን የመሰለ ፍጽምና ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት የሚቻልና ተደራሽም ነው››።

የድንግልና ዋጋ የተመሠረተው ሌላውን ሰው በባለቤትነት የመያዝ ፍላጎት በሌለው የፍቅር ተምሳሌት ላይ ነው። በዚህ ዐይነት ድንግልና የመንግሥተ ሰማይን ነጻነት ያንጸባርቃል። ድንግልና ባለትዳሮች በክርስቶስ ወሳኝ ፍቅር መሠረት የጋብቻ ፍቅራቸውን እንዲኖሩበትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሙላት በአንድነት እንዲጓዙ ያበረታታቸዋል። የጋብቻ ፍቅር በበኩሉ፣ ለሌሎች እሴቶች ተምሳሌት ይሆናል። በሌላ በኩል፣ የጋብቻ ፍቅር በቅድስት ሥላሴ ውሰጥ የሚገኘው በልዩነት ውስጥ ያለ ሙሉ አንድነት ልዩ መገለጫ ነው። ቤተሰብ ደግሞ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ቤተሰብ የእያንዳንዱ ሰብአዊ ሕይወት አካል የሆነውን የእግዚአብሔርን ቅርበት ያመለክታል። ምክንያቱም ክርስቶስ ሥጋ በመልበሱ፣ በሞቱና በትንሣኤው ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖአል። እያንዳንዱ ባለትዳር ከሌላው የትዳር አጋሩ ጋር ‹‹አንድ ሥጋ›› ይሆናል፤ ይህም እስከ ሞት ድረስ ሁሉንም ነገር ከእርሱ ወይም ከእርስዋ ጋር ለመካፈል ፈቃደኛ የመሆን ምልክት ነው። ድንግልና ግን ከሙታን የተነሣው የክርስቶስ ‹‹ዳግም ምጽአት›› ምልክት ሲሆን፣ ጋብቻ ደግሞ በዚህ ዓለም ውስጥ የመኖራችን ‹‹ታሪካዊ›› ምልክት፣ ከእኛ እንደ አንዱ ለመሆን የመረጠውና ስለ እኛ ደሙን እስከ ማፍሰስ ድረስ ራሱን አሳልፎ የሰጠው የምድራዊ ክርስቶስ ምልክት ነው። ድንግልናና ጋብቻ የተለያዩ የመውደድ መንገዶች ናቸው፣ መሆንም አለባቸው። ምክንያቱም “ሰው ያለ ፍቅር ሊኖር አይችልም። ፍቅር ካልተገለጠለት በቀር ለራሱ የማይገባ፣ ሕይወቱ ትርጉም አልባ የሆነ ፍጡር ሆኖ ይቀራል”።

ምንኩስና ነጻ የመሆን ፣ ከአንድ መኖሪያ ወይም ሥራ ወይም አማራጭ ወደ ሌላው የመዘዋወር፣ ገንዘብን ተገቢ በመሰለው መንገድ የማውጣትና ከሌሎች ጋር እንደ ፈለጉ ጊዜን የማሳለፍ ዕድል የሚሰጥ ምቹ የብቸኝነት ኑሮ የመሆን ስጋት አለበት። እነዚህን በመሰሉ ሁኔታዎች፣ የባለትዳር ሰዎች ምስክርነት ይበልጥ ልብ የሚነካ ይሆናል። ለድንግልና የተጠሩ ሰዎች በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ የእግዚአብሔርን ለጋስነትና ለቃል ኪዳኑ ጽኑ ታማኝ የመሆንን ምልክት ያያሉ፤ ይህም ለሌሎች ሰዎች ይበልጥ ተጨባጭና ለጋስ የሆነ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ያነሣሣቸዋል። ብዙ ባለትዳር ጥንዶች የአንዳቸው አካላዊ ማራኪነት ቢቀንስም፣ ወይም የሌላውን ፍላጎት ለማርካት ባይችልምና በኅብረተሰባችን ውስጥ እርስ በርስ እንዳይተማመኑ ወይም እንዲለያዩ የሚያበረታቱ ድምጾች ቢኖሩ እንኳ በታማኝነታቸው ጸንተው ይኖራሉ። ሚስት የታመመ ባልዋን ትንከባከባለች፣ ወደ መስቀል ዘንድ ቀርባም እስከ ሞት ድረስ ልትወደው ያላትን ዝግጁነት ታድሳለች።

በዚህ ዐይነት ፍቅር ውስጥ፣ ከመወደድ ይልቅ መውደድ የተገባ በጎ ምግባር ስለ ሆነ ፣ የእውነተኛ አፍቃሪ ክብር እንደ ብርሃን ያንጸባርቃል። እንደዚሁም በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ሕጻናት ሲያስቸግሩና ምስጋና ቢስ ሲሆኑ ጭምር፣ ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍቅራዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ብቃት እንዳለ ማሳየት እንችላለን። ይህም እነዚያን ወላጆች የኢየሱስ ነጻና ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍቅር ምሳሌ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች መነኮሳት ለእግዚአብሔር መንግሥት የገቡትን ቃል በታላቅ ልግስናና ግልጽነት እንዲኖሩ ያበረታቱአቸዋል። ዛሬ፣ ዓለማዊነት የዕድሜ ልክ አንድነትንና የጋብቻ ጥሪ ውበትን አደብዝዞታል። በዚህ ምክንያት፣ ስለ ጋብቻ ፍቅር አዎንታዊ ገጽታዎች ያለውን ግንዛቤ ማስፋት ያስፈልጋል።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 157-162 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ
 

14 September 2024, 16:59