ፈልግ

አንዲት ሴት በሃይድራባድ ውስጥ በመስቀል ቅርጽ የተሠራ የአበባ ጉንጉን ስትነካ አንዲት ሴት በሃይድራባድ ውስጥ በመስቀል ቅርጽ የተሠራ የአበባ ጉንጉን ስትነካ  (AFP or licensors)

በህንድ የሚገኙ ክርስቲያናዊ ብጹአን ጳጳሳት ባደረጉት ስብሰባ የህንድ አናሳ ክርስቲያኖች መብቶች እንዲጠበቁ አሳሰቡ

በህንድ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ የተጠራው ብሔራዊ የክርስቲያን ጳጳሳት ህብረት ስብሰባ ላይ ከተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች የተውጣጡ 40 ታዋቂ መሪዎች ቤንጋሉሩ በሚገኘው የቅዱስ ዮሃንስ ብሄራዊ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተሰባስበው በዋናነት በህንድ በሚገኙ አናሳ ክርስቲያኖች ላይ ስለሚደርሰው በደል እና መብቶቻቸ ዙሪያ ተወያይተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ኅብረት እና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ያለመ የብሔራዊ የክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይ ጳጳሳት ኅብረት ስብሰባ፣ የማኅበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴን በማጠናከርና አስቸኳይ አገራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች በማመላከት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ተገልጿል።

በስብሰባው ላይ የተለያዩ የክርስቲያን ተቋማት ፕሬዚዳንቶችን፣ አወያዮችን እና በህንድ ውስጥ የሚገኙ የቤተክርስትያን መሪዎችን ለአንድ ምሽት የውይይት፣ የጸሎት እና የአብሮነት ጊዜ አንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ መርሃ ግብሩን የመሩት የህንድ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ አንድሪውስ ታዝሃት የስብሰባው ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

ስብሰባውን አስመልክቶ የወጣው ይፋዊ መግለጫው እንደሚገልፀው ጳጳሳቱ በዚህ የህብረት ስብሰባ ላይ የተሰባሰቡበት ዋነኛ ዓላማ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ህብረት እና ወንድማማችነት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ብጹአን ጳጳሳት እና የአብያተ ክርስቲያናት ሓላፊዎች መካከል ማሳደግ እንደሆነ በመግለጽ፥ ‘ሁሉም አንድ ይሁኑ’ (ዮሐ 17፡21) የሚለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስንብት ምኞትና ጸሎት በቅርቡ እውን ይሆን ዘንድ በህንድ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ክርስቲያናዊ ህብረት እንቅስቃሴን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።

በክርስቲያናዊው ህብረት ውይይት ወቅት ተሳታፊዎች አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮችን እና በህንድ ውስጥ ከሚገኘው የክርስቲያን ማህበረሰብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ጉባኤው በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር ያለመ ቁልፍ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ሲሆን፥ በቤተክርስትያን መሪዎች መካከል ህብረት እና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ብዙ ጊዜ መሰባሰብ እንደሚያስፈልግ በአፅንዖት አመላክቷል።

በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉትን የክርስቲያናዊ ህብረት ፌዴሬሽኖችን በማጠናከር ብሔራዊ የአብያተ ክርስቲያናት ፌዴሬሽን እንዲቋቋም ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ መግለጫው ገልጿል።

የስብሰባው ተሳታፊዎችም ክርስትና በአገር ግንባታ ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና በመግለጽ ክርስትና የውጭ ሃይማኖት ነው የሚለውን የተሳሳተ ትርጓሜ ለማስወገድ ያለመ እንደሆነ በመግለጽ፥ ክርስትና በህንድ ውስጥ አዲስ የመጣ ሃይማኖት ሳይሆን ለ2000 ዓመታት ያህል መቆየቱን አስታውሰዋል።

በክርስቲያኖች እና በሌሎች አናሳዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እየጨመረ መሄዱ እንዳሳሰባቸው የገለጹት ተሰብሳቢዎቹ የአናሳዎች መብት እንዲጠበቅ እና ለሁሉም አናሳ ማህበረሰቦች ደህንነት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል።

የዳሊት ክርስቲያኖች የእኩልነት ጥያቄ እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ያለ ምንም ውጣ ውረድ እንዲተገበር ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁት የነበረውን ጥያቄያቸውን የጉባኤው ተሳታፊዎች ደግመው ማንሳታቸውም ተነግሯል።

በተጨማሪም ስብሰባው ለጎረጎሳዊያኑ 2025 ኢዮቤልዩ ዓመት የጋራ ክርስቲያናዊ በዓላትን ለማዘጋጀት እና 1,700 ኛው የኒቂያ የመጀመሪያ የክርስቲያን ህብረት ጉባኤ እንዲከበር ወስኗል።

በመጨረሻም ስብሰባው የተጠናቀቀው የክርስቲያን ማህበረሰብ እና አብያተ ክርስቲያናት “ለሀገር እና ለጋራ ጥቅም የላቀ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ” ጥሪ በማቅረብ፥ ብሔራዊ የክርስቲያን ኃይማኖት ብጹአን ጳጳሳት ኅብረት ስብሰባው ለክርስቲያናዊ አንድነት ፀሎት በማቅረብ እና የወዳጅነት እራት በመካፈል ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ወንድሞችና እህቶች በአንድነት በመገናኘታቸው በጣም ተደስተው እንደነበር ገልፀዋል።
 

24 September 2024, 14:31