የነቀምት ሀገረስብከት ተተኪ ጳጳስ ክቡር አባ ጌታሁን ፈንታ ቅብዓተ ጵጵስና ተከናወነ
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ ዓመት በረከት የሆነው የአዲስ ጳጳሳት ቅብዓተ ጵጵስና ከሶዶው ሃገረ ስብከት በመቀጠል በዓመቱ የመጀመሪያ ወር፣ በ12ኛው ቀን የክቡር አባ ጌታሁን ፈንታ በጵጵስና ስማቸው የብፁዕ አቡነ ሚልክያስ ሢመተ ጵጵስና በነቀምት ኪዳነ ምሕረት ካቶሊክ ካቴድራል ተከናውኗል።
በቤተክርስቲያን ውስጥ ሦስቱ የሐዋርያዊ አገልግሎት ምሥጢር ተካፋይ የሆኑት አካላት ጳጳስ፣ ካህን እና ዲያቆን እንደሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተምህሮተ ክርስቶስ - 1536 በግልጽ ያስቀምጣል፥ ከእነዚህም ውስጥ የበላዩ ጳጳስ ወይም ኤጴስ ቆጶስ ቀዳሚው እንደሆነ ይህ አስተምህሮ በተጨማሪም ይነግረናል። ጳጳስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚያገለግሉ አገልጋዮች መካከል አንዱ እናቀዳሚው አካል ሲሆን፥ የመጀመሪያ ማዕረግን የያዘ ነው፡፡
ጳጳሳትበእግዚአብሔር ቦታ ሆነው መንጋውን በበላይነት ይመሩ ዘንድ እረኞች፣የትምህርተ ሐይማኖት መምህራን፣ የቅዱስ አምልኮ ካህናትና የቤተክርስቲያንመንግሥት አስተዳዳሪዎች ሰለሆኑ አጋዦቻቸው በሆኑ በቀሳውስትናበዲያቆናት እየተረዱ ሕዝበ ክርስቲያንን ለማገልገል ኃላፊነት ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ ጳጳሳት ሢመተ ጵጵስና ሲቀበሉ፥ ከመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያንታሪክ ጀምሮ የነበሩት የቅዱሳንሐዋርያት ተተኪ በመካከላችን እንደተቀባ፣በእርሱም አማካኝነት እግዚአብሔር ቤቱን ለመሥራት እና በመንፈስ ቅዱስመሪነትም ክርስቶስ የመረጣቸው አባት እንደሆኑ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የነቀምት ሀገረስብከት ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቫርጌስ ወደ ህንድ ሀገር ከተዘዋወሩበት ጊዜ ጀምሮ ሰበካውን በጊዜያዊ አስተዳዳሪነት ክቡር አባ ግርማ ተስፋዬ ሲመሩ ቆይዋል። ባሰለፍነው ሀምሌ ወር ክቡር አባ ጌታሁን ለነቀምት ሀገረስብከት ቋሚ ጳጳስ ሆነው በርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሾማቸው ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ መስከረም 12 ዕለት በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ እና የሲመተ ጵጵስና ስርዓት ብፁዕ አቡነ ሚልክያስ የነቀምት ሀገረስብከት ጳጳስ ሆነው ተቀብተዋል። በሥነ ሥርዓቱም የቀድሞ የሀገረስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቫርጌስን ጨምሮ ብፁዓን ጳጳሳት፣ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ በርካታ ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ምዕመናን፣ የሌሎች ሀይማኖት ተወካዮች፣ የመንግስት አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዕለቱም ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ባስተላለፉት ቃለምዕዳን ሐዋርያት በኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበሉት የመንፈስ ቅዱስ ሀይል አማካይነት ይሰጡት የነበረውን የሚስጥረ ክህነትን ማዕረግ ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ አገልግሎት አስታውሰው ይህ የክርስቶስ ቅዱስ ሥራ ህያው ሆኖ በመቀጠል ዛሬም ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አዲስ እረኛ መገኘቱን ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው የመልካም ሞኞታቸውን ከገለጹ በኋላ ለብጹዕ አቡነ ሚልክያስ ባስተላለፉት መልዕክት እግዚአብሔር ለሾማቸው አዲስ አገልግሎት በታላቅ ትዕግስት እና በጸሎት እንዲመሩ አደራ በማለት፥ ለመላው ካቶሊካውያንም አዲሱን እረኛ እንዲያግዙ አሳስበው መላው የኢትዮጵያ ጳጳሳትን በመወከል የአብሮነታቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል። በመርሃግብሩ ማጠናቀቂያ ብፁዕ አቡነ ሚልኪያስ የምስጋና መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥በመልዕክታቸውም መላው ካቶሊካውያን ለአገልግሎት ቆይታቸው በጸሎት እንዲያግዟቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሚልኪያስ እ.አ.አ የካቲት 25 ቀን 1973 ዓ.ም. በነቀምት ሀገረስብከት ምዕራብ ወለጋ አለኩ ቃቄ የተወለዱ ሲሆን በቅዱስ ፍራንቼስኮስ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የፍልስፍና እና የነገረ መለኮት ማዕከል የክህነት ትምህርት ዝግጅታቸውን በመጨረስ እ.አ.አ ሀምሌ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ክህነት ተቀብተዋል። በአሜሪካ ቺካጎ በሚገኘው የደ ፖል ዩኒቨርስቲ በሰው ሃይል አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ብፁዕ አቡነ ሚልኪያስ በሰኮ የመድኃኔዓለም ቁምስና እና መቲቻ የቅድስት ማርያም ቁምስና ቆሞስ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ለቬንሰንሽያን ገዳም የሴሚናሪዎች አለቃ፣ በሁለት የኃላፊነት እርከን እና ወቅት የቬንሰንሽያን ገዳም የበላይ አለቃ በመሆን አገልግለዋል።