የፊሊፒንስ ዶሚኒካኖች የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰብአዊ መብቶች መመሪያ መፅሃፍ ማሳተማቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
“የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰብአዊ መብት ትምህርት ለወጣቶች በፊሊፒንስ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መመሪያ መጽሃፍ ማስመረቂያ ሥነ ስርዓትን የቅዱስ ቶማስ የሲምባሀያን ማህበረሰብ ልማት ጽ/ቤት እና በሃገሪቱ ከሚገኘው የሙያ ትምህርት እና ልማት ማዕከል በጋራ በመሆን ማዘጋጀታቸው ተነግሯል።
የዶሚኒካን ማህበር ለፍትህ እና ሰላም ቢሮ የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ላውረንስ ብላትመር የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰብአዊ መብቶች ግንኙነቶችን ለማስተማር የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለመምህራን ማሟላት እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “ይህ ሲሆን መምህራኖች የአየር ንብረት ለውጥን እና የሰብአዊ መብቶችን በጥልቀት በመረዳት ተማሪዎችን ንቁ ዜጋ እንዲሆኑ ማበረታታት እና ማብቃት እንደሚችሉ” በአፅንዖት ተናግረዋል።
የፍትህ እና የሰላም ቢሮ ዋና አስተባባሪ እና የተባበሩት መንግስታት ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አባ አኒዲ ኦኩሬ በበኩላቸው የሰው ልጅ ለአካባቢው እና ለመጪው ትውልድ ያለበትን ሀላፊነት ጎላ አድርገው በመግለጽ፥ “እኛ አሁን በሕይወት ያለን ሰዎች ከአባቶቻችን መሬት አንወርስም፥ ነገር ግን ከመጪው ጊዜ እንበደራለን” ካሉ በኋላ “መሬት ከተሰጠህ የመንከባከብ ግዴታ አለብህ” በማለት ገልጸዋል።
የመጽሃፉ የማስመረቂያ መርሃ ግብር ላይ የሰብአዊ መብት እና የአየር ንብረት ተሟጋቾች እና የተለያዩ ምሁራን በመገኘት ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ ሁሉም ተሳታፊዎቹ ስለነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ የመምህራን ሚና ወሳኝ መሆኑን ተስማምተውበታል።
መፅሃፉ ከመመረቁ በፊት የአየር ንብረት ለውጥ እና የሰብአዊ መብት ትምህርትን ከሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር ማቀናጀት ስለሚቻልብቸው መንገዶች ላይ ያተኮረ የአራት ቀናት አውደ ጥናት ሐምሌ ወር ላይ በቅዱስ ጁአን የካቶሊክ ኮሌጅ ውስጥ መካሄዱ ተነግሯል።