ፈልግ

የቲሞር-ሌስቴ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ብጹእ አቡነ ሊያንድሮ ማሪያ አልቬስ የቲሞር-ሌስቴ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ብጹእ አቡነ ሊያንድሮ ማሪያ አልቬስ 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቲሞር-ሌስቴ ያሉ ካቶሊኮች በየቀኑ በእምነታቸው መሰረት እንዲኖሩ ያበረታታሉ ተብሎ ይጠበቃል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ እስያ እና ኦሽንያ የሚያደርጉትን 45ኛ ሐዋርያዊ ጉዞ ሦስተኛውን ዙር በቲሞር-ሌስቴ የጀመሩ ሲሆን፥ የቲሞር ሌስቴ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ እና የዲሊ ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብጹእ አቡነ አልቬስ ከቫቲካን ዜና ጋር ከጉብኝቱ ስለሚጠበቀው ውጤት እና በእስያ አህጉር ውስጥ ስላለችው ትንሿ የካቶሊክ ሃገር ምዕመናን ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች አስመልክተው አጠር ያለ ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሰኞ ዕለት ከዲሊ አየር ማረፊያ ወደተዘጋጀላቸው መንበረ ጵጵስናቸው ሲጓዙ እሳቸውን ለመቀበል በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ የተሰበሰበው የሰው ብዛት የምስራቅ-ቲሞር ህዝብ በብጹእነታቸው ጉብኝት ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው እና ጉጉት እንደነበራቸው ያረጋግጣል ተብሏል።

ብጹእ አቡነ አልቬስ የቲሞር-ሌስቴ ካቶሊካዊያንን እምነትን ለማጠናከር የተደረገ ጉብኝት ነው ማለታቸው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከኢንዶኔዥያ በቅርብ ርቀት ላይ ወደምትገኘው እና ግማሽ ህዝቧ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ወደሆነችው ደሴት ለመጓዝ እየተዘጋጁ በነበረበት ወቅት የባውካ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሊዮናርዶ ማሪያ አልቬስ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በሀገሪቱ ያሉት የካቶሊክ ምእመናን ቅዱስ አባታችንን በጉጉት ሲጠባበቁ እና “በእርሳቸው አማካኝነት ከእግዚአብሔር ብዙ በረከቶችን” እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ይህ ለምስራቅ-ቲሞር ህዝብ፥ በተለይም ለቲሞር ክርስቲያኖች አስፈላጊ እና አስደናቂ ጊዜ ነው” በማለት የተናገሩት ብጹእ አቡነ አልቬስ “የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት በክርስቶስ ያለንን እምነት እና እንዲሁም ለቤተክርስቲያን፣ በተለይም ለብጹእነታቸው ያለንን ታማኝነት ያረጋግጣል” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ አልቬስ በተጨማሪም አብዛኛው ህዝብ በተለይም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በዝግጅቱ ወቅት ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው እና በትልቅ ጉጉት ሲጠብቁ እንደነበር ገልጸዋል።

አባ ጆቪቶ ሬጎ: ከተጠበቀው በላይ ነው ማለታቸው
የዲሊ ሃገረስብከት ሃዋሪያዊ ሥራዎች አስተባባሪ የሆኑት አባ ጆቪቶ ሬጎ በበኩላቸው የብጹእነታቸውን ጉብኝት አስመልክተው እንደተናገሩት “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በእውነት የሚሰብኩትን እየኖሩ ነው” ካሉ በኋላ፥ ቲሞር ሌስቴ በእስያ አህጉር ውስጥ የምትገኝ “በጣም ትንሽ” የካቶሊክ አገር እንደሆነች በማስታወስ፣ “የካቶሊክ ቤተክርስቲያ የተረሱትን ለመፈለግ የምትወጣ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች አረጋግጠዋል” በማለት ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ2011 ዓ.ም. ወደ እዚህ አከባቢ ለመምጣት አቅደው እንደነበር፥ ሆኖም ግን በወቅቱ በተከሰተ የኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ጉብኝቱ እንደተሰረዘ እና የምስራቅ ቲሞር ዜጎች ብጹእነታቸው ለማግኘት ከነበራቸው ትልቅ ጉጉት የተነሳ በመቅረታቸው በጣም ቅር ተሰኝተው እንደነበር በማስታወስ፥ “በአሁኑ ወቅት እሳቸው ካሉበት የጤና ጉዳይ አንፃር እኛን ሊጎበኙን ይመጣሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር” ብለዋል።

ለጉብኝቱ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉ
አባ ጆቪቶ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለሚያደርጉት ጉብኝቱ ከመንግስት ጋር በመተባበር በሎጀስቲክም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት እንደተዘጋጁ ያብራሩ ሲሆን፥ በመንፈሳዊ ደረጃ፣ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሦስቱ ማለትም የዲሊ፣ ባካው እና ማሊና ሃገረ ስብከቶች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሕይወት ታሪክ፣ በሥነ-ምግባራቸው፣ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነታቸው ያላቸው ተልእኮ እና በቲሞር-ሌስቴ የሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት አስፈላጊነት ላይ በማተኮር ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የአከባቢው ብጹአን ጳጳሳትም በጉብኝቱ ማዕከላዊ መሪ ቃል ላይ በመመርኮዝ “እምነትህ ባህልህ ይሁን” በሚል መሪ ቃል፣ እምነትን ከባህል ጋር በስልት ማስተሳሰር ያለውን ፋይዳ የሚያስተምሩ ብሄራዊ መንፈሳዊ መርሃግብሮችን ማዘጋጀታቸውን አክለው ገልጸዋል።

በምስራቅ ቲሞር ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች
የዲሊ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት፣ ቲሞር-ሌስቴ ከሁለት አስርት የነፃነት ዓመታት በኋላ አሁንም እያጋጠሟት ያሉትን “የፖለቲካ ውጥረቶች፣ የእርቅ፣ የሞራል ጉዳዮች እና ሙስናን” ጨምሮ በርካታ “ያልታዩ” ተግዳሮቶችን ጠቅሰው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለዚህ ሁኔታ ግንዛቤው እንዲኖራቸው እና የቲሞር-ሌስቴን ሰዎች ሁል ጊዜ በልባቸው እንዲያስቡ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ጉብኝቱ በቲሞር-ሌስቴ ውስጥ የበለጠ ሲኖዶሳዊ ቤተክርስቲያንን ያበረታታል
አባ ጆቪቶ በመጨረሻም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ጭብጥ የቲሞር ካቶሊኮች እምነታቸውን “በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር” እንዲኖሩ፣ እንደ ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ጳጳሱ ጋር በመተባበር እና በተልዕኮአቸው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያበረታታቸው እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
 

10 September 2024, 15:34