ፈልግ

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንሲስ ቤልጂየም በሚገኘው ሌቭን የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለአንድ ፍልስጤማዊ ስደተኛ ሰላምታ ሲያቀርቡ ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንሲስ ቤልጂየም በሚገኘው ሌቭን የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለአንድ ፍልስጤማዊ ስደተኛ ሰላምታ ሲያቀርቡ  (Vatican Media)

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት ካሪታስ ቤልጂየም ለአንድነት ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክራል ተባለ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቤልጂየምን በጎበኙበት ወቅት የካሪታስ ቤልጂየም ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጊልስ ክኖከርት ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መገኘት ለቤተክርስቲያኗ የሰብአዊ አገልግሎት ተልእኮ የተስፋ ጊዜን ይሰጣል ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከመስከረም 16 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ወደ ቤልጂየም ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ከተለያዩ የቤልጂየም ማህበረሰብ አካላት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በብራሰልስ ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ጋር ቆይታ ያደረጉት የካሪታስ ቤልጂየም የኮሚዩኒኬሽን እና ቅስቀሳ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጊልስ ክኖከርት ቤተክርስቲያኗ በተልዕኮዋ ውስጥ ህብረተሰቡን ለማገልገል ባላት ሃላፊነት ለተለያዩ ቀውሶች ምላሽ በመስጠት እና ድህነትን በማቃለል ረገድ ጠንክራ እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በሰብአዊ ቀውሶች እና ድንገተኛ አደጋዎች ለተጎዱ ሰዎች ዘላቂ መፍትሄዎችን እንደሚሰጥ፥ በተለይም በስደተኞች ላይ በማተኮር ስደተኞቹን አስተናገጅ ሀገራት ተቀብለው እንዲያስተናግዷቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ካሪታስ ቤልጂዬም በፕሮግራሞቹ ውስጥ ከዓለም አቀፍ የካሪታስ ትስስር ጋር በመተባበር ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ የተለያዩ ተጋላጭ ቡድኖች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ጭምር ሃላፊው ገልጸዋል።

አቶ ክኖከርት በማከልም በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ ለመጣው ግጭት ምላሽ ለመስጠት እና በቀጠናው አስቸኳይ የሰብአዊ ፍላጎቶችን ለመፍታት ካሪታስ ቤልጂየም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የቤልጂየሞች 'የእንግዳ ተቀባይነት ባህል'
በስደት ላይ ያተኮረው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የቤልጂየም ጉብኝት ዋና ጭብጥ በተመለከተ አቶ ክኖከርት ሲናገሩ፣ ምንም እንኳ ሃገሪቷ የስደተኞች አቀባበልን ለመገደብ አጠቃላይ አቋም ቢኖራትም፥ ካሪታስ ቤልጂየም ለ “እንግዳ ተቀባይነት ባህል” ያለውን ቁርጠኝነት አጽንዖት በመስጠት አንስተዋል።

አቶ ክኖከርት ከዚህም በተጨማሪ ስደተኞችን በመቀበል የሚቀጥሉ የቤልጂየም ዜጎችን አመስግነው፥ ካሪታስ ስደተኞችን በተመለከተ የሀገሪቱን ገዳቢ አካሄድ እንደማይደግፍ አስምረውበታል።

ሃላፊው በአሁኑ ወቅት ከ4,000 የሚበልጡ ሰዎች ዓለም አቀፍ ከለላ እየፈለጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ሀብትን በተገቢው ሁኔታ የሚያንቀሳቅሱ እና ለስደተኞች የማህበረሰብ ድጋፍ ፕሮግራሞችን የሚተገብሩ ቁምስናዎች እና የእንግዳ ተቀባይ ቡድኖች እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት ያመላከቱ ሲሆን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጉብኝት በማስታወስ፣ “ይህ ጉብኝት ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ቀን ጋር በመገጣጠሙ ለቤተክርስቲያኒቱ ይህ የተስፋ ጊዜ ነው” በማለት አክለዋል።

ካሪታስ ቤልጂየም ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት የሚጠብቀው ነገር
አቶ ክኖከርት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቤልጂየም ያደረጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት በሃገሪቷ ውስጥ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን ትልቅ ተስፋን እንደሚያመጣ የገለጹ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን በስፋት በተሰራጩት የጾታዊ ጥቃት ቅሌቶች ምክንያት ቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ፈተናዎች እየገጠሟት እንደሆነ ጠቁመው፥ ከእነዚህ ጉዳዮች አንፃር ለተጎጂዎች ተጨባጭ ትኩረት እንደሚሰጥ እንጠብቃለን ብለዋል።

አቶ ክኖከርት ከካሪታስ መቀበያ ማዕከላት የመጡ አሥር ነዋሪዎች እሁድ ዕለት በብራሰልሱ ሃይሴል ስታዲየም በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከቅዱስ አባታችን ጋር እንደተካፈሉ በማስታወስ፥ ከዚህም በተጨማሪም በማዕከሉ ውስጥ በሚረዱ ሕጻናት የተሠሩ የማስታወሻ ዕቃዎች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮ በስጦታ መልክ እንደተሰጡ ጠቅሰዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንድነትን እና ሰብአዊ ክብርን በማበረታታት ረገድ ያላትን ተልእኮ በተመለከተ፣ ካሪታስ ቤልጂየም የዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነትን አስፈላጊነት እየተቃወመም ቢሆን፣ በእነዚህ እሴቶች በተግባር የመኖር አስፈላጊነትን በማሳየት ቋሚ ምስክር ሆኖ እንዳሳየ ገልጸዋል።

አቶ ክኖከርት በመጨረሻም ካሪታስ ቤልጂየም በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ድጋፍ የቤተክርስቲያን ተልእኮ ወሳኝ አጀንዳ የሆኑትን የማህበራዊ እና የአከባቢያዊ ፍትህን በመተግበር ይቀጥላል በማለት አጠቃለዋል።
 

30 September 2024, 15:08