ፈልግ

የሴኡል 2027 የዓለም ወጣቶች ቀንን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ አቅራቢዎች የሴኡል 2027 የዓለም ወጣቶች ቀንን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ አቅራቢዎች  (Dicastero per i laici, la famiglia e la vita)

በኮሪያ ዋና ከተማ ሴኡል የሚከበረው የ2027 የዓለም ወጣቶች ቀን ዝግጅት ይፋ ሆነ

በኮሪያ የሴኡል ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሶን-ታይክ ቹንግ እና የዓለም ወጣቶች ቀን አስተባባሪ ብጹእ አቡነ ኪዩንግ ሳንግ ሊ በቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ሴኡል ስለሚካሄደው የ2027 የዓለም ወጣቶች ቀንን አስመልክቶ ስለሚደረገው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ስብሰባ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ማክሰኞ መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በቅድስት መንበር የመግለጫ ጽ/ቤት የቀጣዩ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ስብሰባ አዘጋጆች እና አራማጆች በደቡብ ኮሪያ ሴኡል በሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተናጋጅነት የሚከበረውን የ2027 የዓለም ወጣቶች ቀንን አስመልክተው ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከሁለት ዓመት በኋላ የሚከበረው 41ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን መሪ ቃል የተወሰደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ቁጥር 33 ላይ የተናገረው “አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” የሚለው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህን በተጨማሪም አምና የተከበረው 40ኛው የዓለም የወጣቶች ቀን መሪ ቃል የነበረው “ከእኔ ጋር ኖራችኋልና እናንተም ምስክሮቼ ናችሁ” የሚለውም ጭምር ከዮሐንስ ወንጌል ቁጥር 15 ምዕራፍ 27 ላይ ተወስዶ እንደነበረ አዘጋጆቹ አስታውሰዋል።

የሴኡል ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ በዓላት አከባበር ዝርዝሮችን ያቀረቡት የዓለም ወጣቶች ቀን ዝግጅቶችን የሚቆጣጠረው የቫቲካን ጽ/ቤት የሆነው በቅድስት መንበር የምእመናን እና ቤተሰብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋረል፣ በደቡብ ኮሪያ የሴኡል እና የሴኡል አካባቢ የ2027 የዓለም ወጣቶች ቀን አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ብጹእ አቡነ ፒተር ሶን-ታይክ ቹንግ፣ የዓለም ወጣቶች ቀን ዋና አስተባባሪ የሆኑት የደቡብ ኮሪያው ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፖል ክዩንግ ሳንግ ሊ እና ከዚህን ቀደም በነበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ የተሳተፈችው እና ልምዷን ያካፈለችው ገብርኤላ ሱጂ ኪም የተባለች ወጣት ኮሪያዊ በጋራ በመሆን ነበር።

ብጹእ አቡነ ኪዩንግ-ሳንግ በመግለጫው ወቅት ባደረጉት ንግግር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” የሚለውን የዝግጅቱን መሪ ቃል በመምረጣቸው አመስግነው፥ “መሪ ቃሉ የኮሪያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያጋጠሟትን ተግዳሮቶችን እና በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች በጥልቅ ያስተጋባል” ካሉ በኋላ፥ “ኮሪያ ካለፉት የዓለም ወጣቶች ቀን አስተናጋጅ ሃገራት በተለየ ልዩ አውድ ውስጥ የምትገኝ እና የተለያዩ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ በመስማማት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ገልጸው፥ ይህም ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ ወጣቶች ልዩ እና የበለጸገ ልምድ ሊሰጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኮሪያን ክፍፍል አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “ቤተክርስትያን ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በዚህ ክፍፍል ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በትጋት በመስራት ለኮሪያ ህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ ጥራለች” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ኪዩንግ-ሳንግ ሊ የ 2027 የዓለም ወጣቶች ቀንን ድርጅታዊ ዝርዝሮችን እና ዝግጅቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ የዝግጅቱን ዓርማ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ በአርማው መሃከለኛው ክፍል የሚገኘው ቀይ እና ሰማያዊ ቀለሞች ያሉት መስቀል ክርስቶስ ዓለምን ያሸነፈበትን ድል የሚያመለክት መሆኑን ጠቁመዋል። በግራ በኩል ወደ ላይ የሚያሳየው ክፍል እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ እና በቀኝ በኩል ወደ ታች የሚጠቁመው የዓርማው ክፍል ደግሞ ምድርን የሚገልጽ ሆኖ ወጣቶቹ በአንድነታቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድር ላይ መፈጸሙን የሚገልጽ ሲሆን፥ ሁሉም የዓርማው አሰራር ባህላዊውን የኮሪያ ጥበብ ተምሳሌት በማድረግ እንደተሰራ ገልጸዋል።

የሴኡል ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሱን-ታክ ቹንግ የኮሪያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን “በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ የወንጌል ዘርን ያለ ሚስዮናውያን እርዳታ በተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ አማኞች ፈቃደኝነት እና ጠንካራ እምነት ላይ እንደተመሰረተች ህያው ምስክር ሆኖ ይኖራል” በማለት አብራርተዋል።

ይሄንን ጥንካሬ ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ወጣቶች በ 2027ቱ ዝግጅት ከኮሪያ ወጣት አማኞች ጋር በሚገናኙበት ጊዜ አድናቆት እንደሚቸሯቸው ተናግረው፥ “የአባቶቻቸውን ጽኑ እምነት የወረሱት ወጣቶች አንድ ላይ ሆነው ለእምነት ያላቸውን ጥልቅ ቅንዓትን ያድሳሉ” ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፋረል የዓለም ወጣቶች ቀን ዝግጅቶች በኮሪያ፣ እስያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ታላቅ መንፈሳዊ ጥቅሞችን እንዴት እንደሚያስገኝ የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የእስያ አህጉር ለባህሎች፣ ውይይቶች እና ተደጋጋፊነት በተፈጥሮ ክፍት መሆኑ “በጦርነት እና በግጭት በተመሰቃቀለው ዓለም ውስጥ የሰላም መልእክተኛ ለመሆን በጥረት ላይ ለሚገኙ ወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያን ትልቅ እገዛ እንደሚሆኑ ከገለጹ በኋላ፥ በማከልም “ወጣቶች በእምነት እና በዘመናዊነት መካከል ስላለው ውይይት እንዲያስቡ ይረዳቸዋል” በማለት የእስያን ጥንካሬ አወድሰዋል።

ወይዘሮ ሱጂ ገብርኤላ በበኩሏ ለወጣት አመራር ያላትን ፍቅር እና ለእምነት መነቃቃት የበኩሏን አስተዋጽዖ ለማድረግ ያላትን ተስፋ የገለጸች ሲሆን፥ የኮቪድ ወረርሽኝ አንዳንድ የእምነት ማህበረሰቦች እንዲበታተኑ ምክንያት መሆኑን ገልጻ “ሃይማኖታዊ ልምዶቻችንን ለማስተላለፍ በምናደርገው ጥረት በወረርሺኙ ወቅት የተበታተነው መንጋ ፈተና ሆኖብናል” ብላለች።

ከዚህም ባለፈ “የሴኡል 2027 የዓለም ወጣቶች ቀን በኮሪያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወጣቶችም ሃይማኖታቸውን ጠንክረው እንድይዙ ወሳኝ እድል እንደሚሰጥ በመግለጽ “የአንድነት፣ የተስፋ፣ የድፍረት እና የጥልቅ ፍቅር መንገድን በመገንባት፣ የካቶሊክ አማኞችን ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የሕይወት ዘርፎች የተውጣጡ ሰዎችን እንደምንቀበል እና ከሁሉም በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች ጋር ወደ ሩቅ ምስራቅ እና ባሻገር በምናደርገው መንፈሳዊ ንግደት ወቅት አምላክ ከእኛ ጋር እንደሚጓዝ እንተማመናለን በማለት እምነቷን ገልጻለች።
 

25 September 2024, 14:20