በላውዳቶ ሲ መንፈስ ወደ ኮፕ-29 ጉባኤ የሚደረግ ጉዞ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዓለም ሙቀት መጨመር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ከቅሪተ አካል ነዳጆች ወደ ታዳሽ እና ተመላላሽ የኃይል ምንጮች መሸጋገር አስፈላጊ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ ግንዛቤ ግንባር ቀደም ሆኖ የቀረበው ሰኞ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በማልታ ሉዓላዊ ሰራዊት ማህበር ኤምባሲ አማካይነት በሮማ ፓላዞ ኦርሲኒ ውስጥ በተዘጋጀው ከፍተኛ ደረጃ ያለው የውይይት መድረክ ላይ ነው።
‘በላውዳቶ ሲ መንፈስ ወደ ኮፕ-29 ጉባኤ’
"‘በላውዳቶ ሲ መንፈስ ወደ ኮፕ-29 ጉባኤ፡ የኢነርጂ ሽግግር ለማህበራዊ እና ለስራ ዕድል ፈጠራ” በሚል ርዕስ የቀረበው ዝግጅት በአዘርባጃን ለሚካሄደው የኮፕ-29 ጉባኤ ላይ የሜይር ፋውንዴሽንን የምርምር ውጤት እና እድገቶችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
በዱባይ በተካሄደው የኮፕ-28 ጉባኤ ላይ የቀረበው ይህ ጥናት ጣሊያን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቱርክ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ቻይና፣ ህንድ፣ አልጄሪያ፣ ቺሊ እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከአስር ሀገራት የተውጣጡ 1,700 ምላሽ ሰጪዎችን ግብአት እንዳካተተም ተነግሯል።
የሜይር ፋውንዴሽን (MAIRE Foundation) ጥናት የተካሄደው ከዓለም አቀፍ የገበያ ጥናትና አማካሪ ድርጅት (IPSOS) ጋር በመተባበር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ የተሟላ የጥናት ውጤቶቹን በተቋሙ ድረ-ገጽ ላይ ማማከር እንደሚቻል፥ ይህም የሰው ልጆችን ችግር ለማቃለል የሚጥሩ እና ለኃይል እና ዲጂታል ሽግግር አስተዋፅኦ ለማድረግ ሰፊ እይታቸውን እና ሁለገብ እውቀታቸውን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉትን ‘የወደፊቱ ሰብአዊ መሐንዲሶችን' ለመፍጠር ስልጠናዎችን በማስፋፋት ድርጅቱ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ተብሏል።
አስቸኳይ የታዳሽ ኃይል ፍላጎት
ከመረጃዎቻቸው በመነሳት ድርጅቱ በኢንዱስትሪ እና በኢኮኖሚያዊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና በታዳሽ ሃይል ላይ “ጥልቅ የሆነ ለውጥ” እንዲደረግ ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን፥ ይህ ካልሆነ ግን አካባቢው ሊስተካከል በማይችል መልኩ ሊጎዳ እንደሚችል በመግለጽ፥ ለዚህ ሽግግር አዳዲስ ክህሎቶች እና አሁን ያለው የሰው ኃይል ክህሎቶችን ማሳደግ በጣም ወሳኝ እንደሆኑ በአጽንዖት ይመክራል።
በጥናቱ እንደተረጋገጠው ይህንን ለውጥ የሚመሩት መሐንዲሶች ሽግግሩን መቋቋም የሚቻልባቸው አካሄዶች ላይ የበለጠ “ሰብአዊነት ያለው” አቀራረብ መከተል እንዳለባቸውም ጭምር ገልጿል።
የዜሮ ካርቦን ልቀት መጠን ግቦች
በተመሳሳይ መልኩ ፋውንዴሽኑ “ዜሮ ካርበን ልቀት ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልጉ ሰዎችን በማሰልጠን ሂደት ላይ ወሳኝ ለውጥ” እንዲደረግ ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን፥ “እንደ ፎንዳዚዮን ሜይር ተቋም በስልጠና እና በባህላዊ መነሳሳት ህብረተሰቡን ከዜሮ ካርበን ልቀት መጠን ግቦች ጋር ለማስተዋወቅ ያለንን ቁርጠኝነት እንቀጥላለን” ብሏል።
ለስራ ፈጠራ እና የአካታችነት እድሎች
ጥናቱ በተለይ በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሰሜን አፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ያለውን የኃይል ሽግግር ለመቅረፍ የክህሎት እድገት አስፈላጊነት ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን እና ከዚህም በላይ በሥነ-ምህዳር ሽግግር ውስጥ ከእነዚህ ክልሎች የሚወጣውን አዲስ የንቃተ ህሊና እና የአመራር ሚና ያመላክታል።
የኢነርጂ ሽግግር ለአየር ንብረት ቀውሱ አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጥ ብቻም ሳይሆን፥ ለሥራ ፈጠራ እንዲሁም ለሴቶች እና አናሳዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ ያለውን ሚና ጥናቱ አብራርቷል።
በትምህርት እና ስልጠና ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ
በዚህ አውድ ድርጅቶቹ እነዚህን አዳዲስ ተግዳሮቶች ለመቋቋም በትምህርት እና ስልጠና ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ፣ በአጠቃላይ ስነ-ምህዳር ላይ በማተኮር፣ ለዘላቂ የመጪው ትውልድ ግንባታ ያለውን ጠቀሜታ በማጉላት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አጥብቀው ይጠይቃሉ።
በዚህ መንገድ፣ ሃሳቡ በተመሳሳይ መልኩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ 2008 ዓ.ም. “ላውዳቶ ሲ” ወይም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል ርዕስ የጋራ ቤታችንን ስለ መንከባከብ በማስመልከት ካስተላለፉት ጳጳሳዊ መልዕክት ጋር ጥናቱ ይስማማል ሲልም አክሏል።
የባለሙያዎች ውይይት
በቅድስት መንበር የማልታ ሉዓላዊ ሰራዊት ማህበር አምባሳደር የሆኑት አንቶኒዮ ዛናርዲ እንዲሁም የሜይር ፋውንዴሽን ፕረዚዳንት እና መስራች ፋብሪዚዮ ዲ አማቶ በፋውንዴሽኑ ጄኔራል ዳይሬክተር በሆኑት ኢላሪያ ካታስቲኒ የሚቀረበው የምርምር ውጤት ገለጻ ከመቅረቡ ቀደም ብሎ እንግዶችን እንደተቀበሉም ተገልጿል።
በመቀጠል የጣሊያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማትዮ ፒያንቴዶሲ፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ እና በኒውዮርክ የፎርድሃም ጋቤሊ የንግድ ትምህርት ቤት አማካሪ ቦርድ አባል እና በሚላን በሚገኘው የልበ ቅዱስ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ክሪስቲና ፊኖቺ በተሳተፉበት የፓናል ውይይት አድርገዋል።
የፓናል ውይይቱን የመሩት በሜይሬ ግሩፕ የተቋማዊ ግንኙነት፣ ኮሙዩኒኬሽን እና ዘላቂነት ዳይሬክተር በሆኑት በካርሎ ኒኮላስ እንደሆነም ተገልጿል።