የካቶሊክ ማህበረሰብ መስከረም 27 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምድራችን ሰላም ፆም ጸሎት ማድረጉ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
መስከረም 27 የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት የፈነዳበት ልክ አንድ ዓመት እንደሆነው የሚታወቅ ሲሆን፥ በዓለም ዙሪያ ያሉ ካቶሊኮች ባለፈው ረቡዕ ዕለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ በመስጠት በምድራችን ሰላም እንዲሰፍን ቀኑን በጸሎት እና በፆም አሳልፈዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከጥቂት ቀናት በፊት በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹእ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ያደረጉትን ጥሪ በመድገም መላው የካቶሊክ ማህበረሰብ ስለ ሰላም እንዲጸልይ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።
“የሰላም ራዕይ”
ይህ የፓትርያርኩ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጥሪ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ የካቶሊክ ድርጅቶች እና ቡድኖች፣ ከፎኮላሬ ንቅናቄ እና የትናንሽ መነኮሳት ማህበር እስከ የአውሮፓ ህብረት የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ድረስ ተቀባይነት በማግኘት ተስተጋብቷል።
በእስራኤል የዕብራይስጥ ተናጋሪ የካቶሊክ ማኅበረሰብ አገልጋይ የሆኑት አባ ፒዮትር ዘላስኮ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በአከባቢው የሚገኙ ምዕመናን ለሰላም ለመጸለይና ለመጾም እድሉን ተጠቅመውበታል ብለዋል።
አባ ዘላስኮ በማከልም በአከባቢው እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከፍተኛ ሥቃይ ቢያስከትልም፣ “የዕብራይስጥ ተናጋሪ ካቶሊኮች ጥልቅ በሆነ እምነታቸው እና በእግዚአብሔር በተሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት የሰላም ራዕይን እና የፈውስ መንገድን ይከተላሉ” ብለዋል።
መለወጥ፣ ንስሐ እና ይቅርታ
ፓትርያርክ ፒዛባላ የጸሎት ቀን እንዲደረግ ጥሪ ባደረጉበት የመጀመሪያ መግለጫ ላይ ክርስቲያኖች “ልባችንን ከጥላቻ ሁሉ በመጠበቅ” እና “ለማንኛውም ሰው መልካም ምኞትን በማሰብ ራሳችንን ለሰላም የመስጠት ግዴታ አለብን” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ፓትርያርኩ ለህዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት የተቸገሩትን እንዲደግፉ፣ በዚህ ጦርነት የተጎዱትን ወገኖች ስቃይ ለማቃለል በግላቸው የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉትን ሰዎች እንዲረዷቸው እና እያንዳንዱን የሰላም፣ የእርቅ እና የውይይት ተግባራትን እንዲያበረታቱ አሳስበዋል።
ሆኖም ግን ይላሉ ፓትሪያርኩ፣ “ሕመማችንን እና የሰላም ፍላጎታችንን ወደ እግዚአብሔር ለማድረስ መጸለይ ያስፈልገናል” ካሉ በኋላ፥ ‘መለወጥ፣ ንስሐ መግባት እና ይቅርታን መለመን አለብን’ በማለት አሳስበዋል።
ምፅዋት
ፆም ጸሎቱ የብጹአን ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጠናክሮ በቀጠለበት በሮም ውስጥም እንደተከበረ ተገልጿል።
ጳጳሳዊ የገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ክራጄቭስኪ በሲኖዶሱ ጉባኤ ወቅት ለጋዛ ሕዝብ በተለይም እዚያ ለምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ መዋጮ እንደሚሰበስቡ የተናገሩ ሲሆን፥ “ቅዱስ አባታችን በተለይ ዛሬ ለዓለም ሁሉ ሰላም እንዲወርድ ፆም ጸሎት እንድናደርግ በጠየቁበት ወቅት ይሄን ማድረግ ተገቢ ነው ካሉ በኋላ፥ ጸሎት እና ፆም መስዋዕትነትን በሚፈልገው ያለ ምጽዋት ሊደረግ እንደማይችል ጠቅሰው፥ ለተቸገረው ጎረቤታችን ለመስጠት የኛ የሆነውን ስንተወው ሊጎዳን ይገባል ብለዋል።