የካቶሊክ በጎ አድራጊ ተቋም በሊባኖስ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን የሚያደርገውን እርዳታ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሊባኖስ ውስጥ እየተባባሰ ለመጣው ሰብአዊ ቀውስ ምላሽ ይሆን ዘንድ፣ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ለሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውን ድጋፍ በማጠናከር፣ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የትምህርት እና ሌሎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎችን እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
ኤሲኤን በአደጋ ጊዜ ዘመቻው 1 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ማቀዱ
ይህ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት በዓለም ዙሪያ በስደት ላይ ላሉ ክርስቲያኖች ሃዋሪያዊ ሥራ እና መንፈሳዊ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ ያለ ተቋም ሲሆን፥ በሊባኖስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን በቅርብ ጊዜ በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል በተከሰተው አስከፊ ግጭት መባባስ ምክንያት የተፈጠረውን አዳዲስ ፈተናዎችን ለመቋቋም እየታገለች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 1 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እየአካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
700,000 የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል
የተባበሩት መንግስታት ምንጮች እንደሚሉት ጦርነቱ ከተከሰተ በኋላ ወደ 700,000 የሚጠጉ ዜጎች ወደ ቤይሩት፣ ማውንት ሊባኖስ፣ ሰሜን ሊባኖስ እና ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መፈናቀላቸውን ተከትሎ ደቡቡ የሃገሪቱ ክፍል ባዶውን እየቀረ እንደሆነ ተነግሯል።
በእነዚህ ሁሉ ቦታዎች ላይ ቤተክርስቲያኒቷ ተፈናቃዮችን ለመርዳት ወደ ተግባር መግባቷ የተነገረ ሲሆን፥ የሃይማኖት እና የብሄር ልዩነት ሳታደርግ ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች በሯን ክፍት ማድረጓ ተገልጿል።
በሀገሪቱ ወደ 200 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ እየደገፈ የሚገኘው ይህ ጳጳሳዊ ተቋም በእርዳታ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውን ሰባቱን ሀገረ ስብከቶች እና አምስት ሃይማኖታዊ ጉባኤዎችን በማነጋገር በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮቹን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በተፈናቃዮቹ ዘንድ በጣም ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ምግብ፣ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች፣ ፍራሾች፣ መድሃኒቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያካትትም ተገልጿል።
በጦርነቱ በቀጥታ የተጎዱ ክርስቲያኖች
ምንም እንኳን ቀውሱ መላ አገሪቱን እየጎዳ ያለ ቢሆንም፣ እጅግ የከፋው በእስራኤል እና በሊባኖስ አዋሳኝ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ይበልጥ ተጎጂ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
ኤሲኤን እንደዘገበው የመልካይት ግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚያስተዳድረው የስደተኞች መጠልያ መስከረም 29 በሚሳኤል መመታቱን እና በጥቃቱም በደቡባዊ የጢሮስ አውራጃ በሆነችው ዴርግሃያ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል። እንደ የአከባቢው አጥቢያ ቤተክርስትያን ምንጮች ከሆነ በሌላ የሚሳኤል ጥቃት የካህናት መኖሪያ እና የሃገረ ስብከቱ ቢሮ የነበረው ባለ ሶስት ፎቅ ህንፃ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ይፋ አድርገዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን፥ ይህም በአብዛኛዎቹ ዘንድ የቤተሰብ መለያየትን እንደሚያስከትል፣ ምክንያቱም ደግሞ እናት እና ልጆች ቤተክርስቲያን ባዘጋጀቻቸው መጠለያዎች ወይም ዘመዶቻቸው ቤት ውስጥ መጠለያ ሲፈልጉ፣ አባት ግን ንብረትን ለመጠበቅ እዚያው የቤተሰብ ቤት ውስጥ ስለሚቆይ በዚህ መሃል የቤተሰብ መለያየት ይከሰታል ተብሏል። በዚህም ምክንያት በደቡብ የሃገሪቱ ክፍል ያሉ የክርስቲያን መንደሮች ባዶዋቸውን ለመቅረት እየተቃረቡ እንደሆነም ጭምር ተዘግቧል።
በቅርብ ወራት ውስጥ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት በሺህ ለሚቆጠሩ ቤተሰቦች የምግብ እሽጎች ማድረሱን እና ከፍተኛ ስጋት ቢኖርም በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ንብረታቸውን ለመጠበቅ ለቀሩ 1,200 ሰዎች የህክምና ዕርዳታ ማሰራጨቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች መሬታቸውና አዝመራው በግጭቱ ምክንያት በመውደሙ የገቢ ምንጫቸውን ያጡ ገበሬዎች ናቸው ተብሏል።
በጦርነቱ በጣም በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ወላጆች መሥራት የማይችሉ ስለሚሆኑ እና የትምህርት ክፍያ ለመክፈል ስለሚቸገሩ፥ አብዛኛዎቹ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች የኦንላይን ትምህርቶችን መጀመራቸው ታውቋል።
ኤሲኤን ከሊባኖስ ቤተክርስቲያን ጎን ቆሟል
የኤሲኤን ኢንተርናሽናል ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ሬጂና ሊንች እንዳሉት በጎ አድራጎት ድርጅቱ በዚህ የችግር ጊዜ ከሊባኖስ ቤተክርስትያን ጎን መቆሙን እንደሚቀጥል ገልጸው፥ “በሊባኖስ ያለችውን ቤተክርስቲያንን ወደጎን እንደማንተው እንዲሁም ቤተክርስቲያኗን የመደገፍን አጣዳፊነት ደጋፊዎቻችን እንደሚረዱት እርግጠኞች ነን” ሲሉ ተናግረዋል።