ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ “የተክሊል በዓልን ለማክበር ስለ መዘጋጀት”
ለጋብቻ የሚደረጉ የአጭር ጊዜ ዝግጅቶች በሰርግ ጥሪ፣ በአልባሳት፣ በድግስና ገንዘብን ብቻ ሳይሆን ጉልበትንና ደስታን ጭምር በሚያሟጥጡ ሌሎች በርካታና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ጥንዶቹ ወደ ሰርጉ ሥነ ሥርዐት የሚመጡት ለሚወስዱት ትልቅ እርምጃ ትኩረት ሰጥተውና ተዘጋጅተው ሳይሆን፣ ደክሞአቸውና ተቻኩለው ነው። ከትልቅ ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ተመሳሳይ ጭንቀት አንዳንድ ሕጋዊ ያልሆኑ የጋብቻ አንድነትንም ይነካሉ። ከእነዚህ ሥርዓቶች ጋር የተያያዙ ወጪዎች በመኖራቸው፣ ጥንዶቹ ከሁሉ በላይ ስለ ፍቅራቸውና እርሱንም በሌሎች ሰዎች ፊት ለማክበር ከመጨነቅ ይልቅ ፈጽሞ አይጋቡም። እዚህ ላይ ስለ እጮኛሞች አንድ ነገር ልበል። ልዩ ለመሆን ድፍረት ይኑራችሁ። በፍጆታና በከንቱ ታይታዎች በተሞላ ኅብረተሰብ አትዋጡ። ዋናው ነገር በእግዚአብሔር ጸጋ የጠነከረና የተቀደሰ የጋራ ፍቅራችሁ ነው። ፍቅር ከማንኛው ነገር በላይ ቅድሚያ የሚያገኝበትን መጠነኛና ቀላል ሥነ ሥርዓት መምረጥ ትችላላችሁ። የሐዋርያዊ ሥራ ሠራተኞችና መላው ማኅበረሰብ ይህን ቅድሚያ እንደ ልዩ ነገር ሳይሆን እንደ መደበኛ መመዘኛ መውሰድ ይችላሉ።
ጥንዶቹ ለጋብቻ ሲዘጋጁ፣ ሥርዓተ አምልኮን መሠረታዊ የግል ልምድ እንዲያደርጉና የእርሱንም የእያንዳንዱን ምልክት ትርጉም እንዲያውቁ ማበረታታት ያስፈልጋል። ሁለቱም ሰዎች የተጠመቁ ከሆኑ፣ በቃለ መሐላና ጋብቻን ምሉእ በሚያደርገው አካላዊ ውህደት የሚገለጸው ዝግጁነት፣ ሥጋ በለበሰው በእግዚአብሔር ልጅና በቤተክርስቲያኑ መካከል እንዳለው የቃል ኪዳን ፍቅርና የአንድነት ምልክት የሚታይ ነው። በተጠመቁ ሰዎች ውስጥ፣ ቃላትና ምልክቶች ቀጥተኛ የእምነት ምልክት ናቸው። እግዚአብሔር በሰጠው ትርጉም የተፈጠረ አካል “የምሥጢሩ አዳዮች ክንውን ይሆናል፤ እነርሱም በጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ ከራሱ ከእግዚአብሔር የመነጨው ምሥጢር እውን ሆኖ እንደሚገለጽ ያውቃሉ”።
አልፎ አልፎ፣ ጥንዶቹ ከቃለ መሐላ ቀጥለው የሚመጡ ምልክቶችን ሁሉ ትርጉም የሚገልጽ ነገረ መለኮታዊና መንፈሳዊ ቁም ነገር አይረዱትም፡፡ እነዚህ ቃላት ወደ አሁኑ ጊዜ ዝቅ ሊሉ እንደማይችሉና ‹‹ሞት እስኪለየን ድረስ” ያለውን ሙሉውን መጪውን ጊዜ ጭምር የሚያካትቱ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። የቃለ መሐላው ይዘት ግልጽ እንደሚያደርገው፣ “ነጻነትና መተማመን እርስ በርስ የሚቃረኑ ሳይሆኑ፣ በግለ ሰባዊምሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው። በእርግጥ፣ በሉላዊ መገናኛ ባህላችን ውስጥ፣ ባልተከበሩ የተስፋ ቃላት መበራከት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት እናሰላስል… ቃልን ማክበር፣ ለሌላው የገቡትን የታማኝነት ቃለ መሐላ መጠበቅ፣ እነዚህ ነገሮች ሊሸጡና ሊለወጡ የሚችሉ ነገሮች አይደሉም። በኃይል ሊገደዱና ያለ መሥዋዕትነት ሊጠበቁ አይችሉም”።
የኬንያ ጳጳሳት እንዳመለከቱት፣ ‹‹ብዙ ወጣቶች በሰርጋቸው ላይ ስለሚያተኩሩ፣ የሚገቡበትን የረጅም ጊዜ የውዴታ ግዴታ ይረሳሉ”። ስለዚህ፣ ወጣቶች ምሥጢረ ተክሊልን እንደ አንድ ጊዜያዊና ትዝታው እየቆየ እንደሚረሳ ነገር ሳይሆን፣ የትዳር ሕይወትን በዘላቂነት የሚነካ እውነታ መሆኑን እንዲገነዘቡ መምከር ያስፈልጋል፡፡ የወሲባዊነት ተዋልዶአዊ ትርጉም፣ የአካላዊ ንክኪና በትዳር ሕይወት ውስጥ የሚገለጹ የፍቅር ምልክቶች ሁሉ “ቀጣይ የአምልኮ ክንውን” ይሆናሉ፤ “የጋብቻ ሕይወትም ሥርዓተ አምልኮአዊ ይሆናል”።
ባልና ሚስት በመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትና በሚለዋወጡአቸው የጣት ቀለበቶች እንዲሁም የሥነ ሥርዓቱ አካል በሆኑ ሌሎች ምልክቶች ትርጉም ላይ ማስተንተን ይችላሉ። አንድ ላይ ሆነው ለእርስ በርሳቸው ሳይጸልዩ፣ በታማኝነትና በልግስና ለመቀጠል የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔርን እርዳታ ሳይሹ፣ ጌታ ከእነርሱ ምን እንደሚፈልግ ሳይጠይቁና ፍቅራቸውን በድንግል ማርያም ምስል ፊት ሳይቀድሱ ወደ ሰርግ ስፍራ ቢመጡ መልካም አይሆንም። ስለዚህ ወጣቶችን ለጋብቻ የሚያዘጋጁ አካላት እነዚህን ጠቃሚ የጸሎት ወቅቶች እንዲለማመዱ ሊረዱአቸው ይገባል። “የጋብቻ ሥርዓተ አምልኮ የቤተሰብም የማኅበረሰብም በዓል የሆነ ዐይነተኛ ሁነት ነው። ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምር ያደረገው በቃና የሰርግ ግብዣ ላይ ነበር። በጌታ ተአምር ለአዲሱ ቤተሰብ ደስታን ያመጣው መልካሙ ወይን ጠጅ፣ በማናቸውም ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ጋር የተፈጸመ የክርስቶስ ቃል ኪዳን የሆነ አዲስ ወይን ጠጅ ነው… ብዙውን ጊዜ የሥነ ሥርዓቱ መሪ በቤተክርስቲያን ሕይወት እምብዛም ለማይሳተፉ፣ ወይም የሌላ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ወይም ቤተእምነቶች አባላት የሆኑ ሰዎችን ላካተተ ጉባኤ ይናገራል፡፡ ይህም የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ መልካም አጋጣሚ ይሆናል”።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 212-217 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ