ፈልግ

በቤይሩት የሚገኘው ጌይታው ሆስፒታል የቃጠሎ ህክምና ክፍል በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቀብለው ሲያክሙ በቤይሩት የሚገኘው ጌይታው ሆስፒታል የቃጠሎ ህክምና ክፍል በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቀብለው ሲያክሙ 

በቤሩት የሚገኘው የጌይታው ሆስፒታል በርካታ ህይወትን እያዳነ እንደሚገኝ ተነገረ

በሊባኖስ ውስጥ ለሚገኘው ብቸኛው እና የቃጠሎ ሕክምና መስጫ ማዕከል ያለው የቤይሩት ጌይታው ሆስፒታል ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት የሆስፒታሉ ዳይሬክተር የሆኑት ሲስተር ሀዲያ አቢ ቸብሊ፣ በሊባኖስ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን እና ጦርነትን በመቋቋም ረገድ ሆስፒታሉ እያጋጠመው ስላለው ትልቅ ፈተና ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“በዚህ የመከራ ወቅት ከእኛ ጋር እንድትሆኑ እለምናችኋለው” ያሉት ሲስተር ሃዲያ፥ በቤሩት የሚገኘው እና የቃጠሎ ህክምና የሚሰጠው ጌይታው ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ለቆሰሉ ሰዎች የህይወት አድን አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል የአብሮነት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ጥሪ የተሰማው መስከረም 13 ቀን እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ የጀመረችው ዘመቻ ከተባባሰበት ጊዜ አንስቶ ከ2,500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና 12,000 የሚጠጉ ሰዎች የቆሰሉበትን ቀጣይ እና እየጨመረ በመጣው የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ ነው።

የቤሩት የጤና አገልግሎት የማዕዘን ድንጋይ የሆነው የጌይታው ሆስፒታል እ.አ.አ. በ1927 ዓ.ም. በቅድስት ማሮናዊት እህቶች የተመሰረተ ሲሆን፥ ለሊባኖስ ህዝብ በህክምና ዘርፍ በሚሰጠው አገልግሎት ግንባር ቀደም ሆኖ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ቆይቷል” ያሉት ሲስተር ሀዲያ፥ ሆኖም ሃምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በቤሩት ከተከሰተው እና “ሆስፒታሉን ሙሉ በሙሉ ከጎዳው” አስደንጋጭ ፍንዳታ በኋላ፣ እንዲሁም በሃገሪቷ በተከሰተው የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ለማስቀጠል በከፍተኛ ትግል ውስጥ እንደነበር ገልጸዋል።

“ለለጋሾች ደግነት ምስጋና ይግባውና ሆስፒታሉ እንደገና አንሰራርቷል” በማለት የቀጠሉት ሲስተር ሀዲያ፥ ነገር ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ እየተባባሰ የመጣ የኢኮኖሚ ቀውስ ባለበት እና አሁን “በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለው የሌሎች ጦርነት” እየተባባሰ ባለበት ሀገር የሆስፒታሉን ማገገም ከባድ አድርጎታል” ካሉ በኋላ “በአገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው የሌሎች ጦርነቶች መቼ እንደሚጠናቀቅ ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።

     “በአገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው የሌሎች ጦርነቶች መቼ እንደሚጠናቀቅ ማወቅ አልቻልንም”

ከ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለው ግጭት እና የኢኮኖሚ ውድቀት የሆስፒታሉ ስራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ በመግለጽ “ብዙ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ በርካታ ሃኪሞቻችን እና ነርሶቻችን ታክቷቸው አገሪቷን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል” በማለት ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጫና እያስከተለ ያለው ግጭት
በ 1983 ዓ.ም. የተመሰረተው የሊባኖስ ብቸኛ የቃጠሎ ህክምና ማዕከል ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጫና ውስጥ በገባበት በአሁኑ ወቅት፣3 እንዲሁም በከባድ ጉዳቶች እና በከባድ ቃጠሎ የሚሰቃዩ ህሙማን እየጎረፉ ባለበት በዚህ ወቅት የሆስፒታሉ ዳይሬክተር “አሁን ያለው ሁኔታ አገልግሎት የመስጠት አቅማችንን ወደ ዜሮ ደረጃ አውርዶታል” በማለት በምሬት ተናግረዋል።

ሲስተር ሃዲያ የህክምና ማዕከላቸው 10 አልጋዎች የመያዝ አቅም ቢኖረውም ካለው የታካሚዎች ብዛት ምክንያት ወደ 25 ለማስፋፋት ተገደው እንደነበር በመግለጽ፥ በሊባኖስ ውስጥ የቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸው ህሙማንን የማከም ልምድ ያለው ብቸኛው ሆስፒታል ስለሆነ እና ይህ ለእነዚህ ታካሚዎች ህይወትን ማዳን በመሆኑ ሁሉንም ታካሚ ተቀብሎ የማስተናገድ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

                  “የቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸውን ታካሚዎችን የማከም ችሎታ ያለን እኛ ብቻ ነን”

የቃጠሎ አደጋ የደረሰበት ሰው ረጅም የሆስፒታል ቆይታ፣ ልዩ እንክብካቤ እና ውድ የህክምና ቁሳቁሶችን የሚጠይቅ በመሆኑ ለህክምናው የሚያወጣው ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ እንደሆነ በአጽንዖት የገለጹት ሲስተር ሃዲያ፥ ‘የእስራኤል ዘመቻ ከተባባሰበት ጊዜ አንስቶ በከፍተኛ ሁኔታ የቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸው 42 ሲቪል ሕሙማንን ስናስተናግድ ሌሎችንም በመቀበል ላይ እንገኛለን’ ካሉ በኋላ፥ በሀገሪቱ ላይ የሚደርሱ የእስራኤል ጥቃቶች እየተጠናከሩ በመጡ ቁጥር በሆስፒታሉ ላይ ያለው ጫና እየጨመረ መምጣቱ እርግጥ ነው በማለት ተናግረዋል።

'ጦርነቱ መጨረሻ ያለው አይመስልም'
ሲስተር ሀዲያ የሊባኖስ ዜጎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጹ “በዋሻ ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች” በማለት የተናገሩ ሲሆን፥ ጦርነቱ ማብቂያ የሌለው እንደሆነ፣ እንዲሁም የመድሃኒት እና የቁሳቁስ እጥረት የማያቋርጥ ስጋት ማስከተሉን አክለው ገልጸዋል።

በጦርነቱ ምክንያት በሃገሪቷ ውስጥ የኤሌክትሪክ አገክግሎት እንደተቋረጠ የገለጹት ሲስተር ሃዲያ፥ በዚህም ምክንያት 10 ጀነሬተሮች እንደሚጠቀሙ፣ ለእነዚህም ጀነሬተሮች የሚውል ነዳጅ ለመግዛት በወር 240,000 ዶላር እንደሚከፍሉ፥ ከዚህም በተጨማሪ የህክምና አገልግሎት መሳሪያዎችን ለሚያቀርበው ድርጅት በርካታ ገንዘብ እንደሚከፍሉ በመግለጽ የማዕከሉን አገልግሎት ለማስቀጠል በአስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሲስተር ሀዲያ ጥሪ ለሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ የጤና አጠባበቅ ማዕከላት ሲሆን፥ የዓለም አቀፍ እርዳታ ካልተደረገ እንደ ጌይታው ያሉ ሆስፒታሎች ሥራቸውን መቀጠል እንደማይችሉ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሊባኖስ ለተከሰተው ግጭት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ደጋግመው የጠየቁ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ሁሌም በጸሎታቸው ሃገሪቷን እንደሚያስታውሷት የገለጹት ሲስተር ሃዲያ፥ ለቀውሱ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በማሳሰብ፥ “የሆስፒታሉን አገልግሎት እኛ በራሳችን አቅም ማስቀጠል አንችልም፥ ይህንን ጦርነት ለማለፍ ድጋፍ እንፈልጋለን” በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።

                                                          “በራሳችን መቀጠል አንችልም”

የተስፋ ምልክት
ሲስተር ሀዲያ በማጠቃለያቸው ላይ የጌይታው ሆስፒታል የጤና እንክብካቤ ማዕከል ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፥ “ሆስፒታላችን ከሆስፒታልም በላይ ነው፤ የተስፋ ምልክት ነው፣ የታላቅ ኩራት ምንጭ ነው። የቃጠሎ ህክምና መስጫ ማዕከላችን በሊባኖስ ለተቃጠሉት ሁሉ የተስፋ ምልክት ነው፥ ምክንያቱም ሌላ የሚሄዱበት ሆስፒታል ዬለም፥ ስለዚህ እንድታግዙን እንፈልጋለን፥ እባካችሁ እመኑኝ” ሲሉ ተማጽነዋል።

ሲስተር ሃዲያ ምንም እንኳን ከፍተኛ ጫና ቢኖርባቸውም፣ ምንም እንኳን ተጨማሪ የሞት መንፈስ እያንዣበበ ቢሆንም ተስፋ እንደማይቆርጡ የገለጹ ሲሆን፥ “ሆስፒታላችን በድጋሚ ጥቃት እንዳይደርስበት እጸልያለሁ፥ ምክንያቱም እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ መገንባት አንችልም፥ በመጀመሪያው አደጋ ምክንያት የጀመርነውን መልሶ ግንባታ እንኳን አልጨረስንም” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል።

ጥሪ
ሲስተር ሀዲያ የድጋፍ ጥሪያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ሁሉም ሰው እንዲተባበር በመጋበዝ፥ “እኛን በመርዳት ህይወትን ማዳን ብቻ ሳይሆን የጌይታው ሆስፒታል የሊባኖስን ማህበረሰብ በማገልገል እንዲቀጥል ያስችለዋል” ካሉ በኋላ፥ “እያንዳንዱ ልገሳ፣ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን፣ ሥራችንን እንድንቀጥል፣ አስፈላጊ የሕክምና መሣሪያዎችን እንድናገኝ እና ለተወሰኑት ሠራተኞቻችን ደሞዝ እንድንከፍል ያስችለናል” ሲሉ በድጋሚ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

                    “እያንዳንዱ የድጋፍ መዋጮ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ሥራችንን እንድንቀጥል ያስችለናል”
 

29 October 2024, 14:18