ፈልግ

በትንሳኤው እሁድ የቦንብ ጥቃት የሞቱ ሰዎች መቃብር ላይ ቤተሰቦቻቸው ሻማ ሲያበሩ በትንሳኤው እሁድ የቦንብ ጥቃት የሞቱ ሰዎች መቃብር ላይ ቤተሰቦቻቸው ሻማ ሲያበሩ   (ANSA)

ስሪላንካ በ2011 በትንሳኤ በዓል ዕለት የተፈጸመውን ጥቃት ምርመራ እንደገና በመጀመሯ የሃገሪቱ ጳጳስ የተሰማቸውን ተስፋ ገለጹ

በስሪላንካ የራትናፑራ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፒተር አንቶኒ ዋይማን ክሮስ የስሪላንካ መንግስት በ2011 ዓ.ም. የትንሳኤ ዕለት የተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶችን በጥልቀት ለመመርመር ባሳየው አዲስ ቁርጠኝነት ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሚያዝያ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በሶስት አብያተ ክርስቲያናት እና ሶስት ሆቴሎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃቱ የ279 ሰዎች ህይወት ሲቀጥፍ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።

ብጹእ አቡነ ፒተር አንቶኒ ከቫቲካኑ ፊደስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቅርብ የተመረጡት አዲሱ የአኑራ ኩማራ ዲሳናያኬ መንግሥት በ 2011 ዱ የትንሳኤ ጥቃት ላይ ጥልቅ ምርመራ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸው ጥሩ ምልክት መሆኑን ገልጸው፥ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ በእርግጠኝነት ፍትህ እንደምናገኝ በተስፋ እንጠብቃለን” ብለዋል።

በስሪላንካ ፖለቲካ እና ደህንነት ላይ ከባድ ጥላ ያጠላው የዚህ ጥቃት ምርመራ መዘግየት እና ተሸፋፍኖ ማለፍ ለብዙዎች ዋነኛ የስጋት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም በፕሬዚዳንት አኑራ ኩማራ የሚመራው መንግስት አዲስ ምርመራ ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው አረጋግጧል።

የመንግስት ቃል አቀባይ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪጂታ ሄራት በበኩላቸው ለአደጋው ተጠያቂ የሆነ ማንም ሰው ከህግ አግባብ እንደማያመልጥ ለህዝቡ አረጋግጠው፥ “በትንሳኤው ጥቃት ላይ ትክክለኛ ምርመራ ተጀምሯል፥ ለስሪላንካ ህዝብ የምናረጋግጠው ነገር ቢኖር ለግፍ መንገድ እንደማንጠርግ ነው፥ ማንንም አንደብቅም ወይም አንከላከልም። ለዚያ ክስተት ተጠያቂ የሆኑ በሙሉ በተገቢው የህግ መስመሮች በኩል ይስተናገዳሉ” በማለት ለህዝብ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የምርመራ ውጤቱም ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ቃል በመግባት፥ “ምርመራው እንደተጠናቀቀ ሙሉ ሪፖርት እናቀርባለን፥ የሚወሰዱ እርምጃዎችንም እንገልፃለን” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ዲሳናያኬ በ 2011 ጥቃት ከደረሰባቸው ቦታዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን በኔጎምቦ የሚገኘውን የቅዱስ ሴባስቲያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ጎብኝተው ለምዕመናኑ ጠንከር ያለ ቃል ከገቡ በኋላ፥ “የትንሳኤ እሁድ ጥቃቶች ለፖለቲካዊ ጥቅም የተፈፀሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ እምነት አለ” በማለት ከአደጋው በስተጀርባ ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ያላቸውን አካላት የማጋለጥ እድሉ ሰፊ እንደሆነ አመላክተዋል።

ከመንግስት ምርመራ በተጨማሪ የሲሪላንካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች ሙሉ ካሳ ባለመክፈል በቀድሞው የመንግስት የስለላ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ኒላንታ ላይ ክስ መጀመሩን አስታውቀዋል። ዳይሬክተሩ 75 ሚሊዮን ሩፒ ካሳ እንዲከፍሉ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የከፈሉት 10 ሚሊዮን ሩፒ ብቻ እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

ጥር 2015 ዓ.ም. ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የስለላ ጥቃቱ ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ጥቃቶቹን መከላከል ባለመቻላቸው የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ማይትሪፓላ ሲሪሴናን ጨምሮ አራት ከፍተኛ ባለስልጣናትን እና ፖለቲከኞችን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።

ከቀድሞው ፕረዚዳንት ሲሪሴና በተጨማሪ የቀድሞ የፖሊስ ዋና አዛዥ ኢንስፔክተር ፑጂት ጃያሳንዴራ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሄማሲሪ ፈርናንዶ እና የቀድሞ የደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሲሲራ ሜንዲስ ከፍተኛ ቅጣት ተጥሎባቸዋው እንደነበርም ተገልጿል።

እነዚህ ህጋዊ ሂደቶች ቢኖሩም፣ የጥቃቱ አቀነባባሪዎች እና አነሳሶች በተመለከተ የሚነሱ ቁልፍ ጥያቄዎች አሁንም አልተፈቱም።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር የምታደርገውን ጥሪ የቀጠለች ሲሆን፥ ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ጥብቅና በመቆም “ፍትህ እና ግልፅነት” እንዲሰፍን ግንባር ቀደም የሆኑ የቤተክርስቲያኑ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች ናቸው።

ከምርመራው ጎን ለጎን አዲሱ የሲሪላንካ መንግስት አስቸኳይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየተጋፈጠ እንደሆነ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ብጹእ አቡነ ክሩስ በመጨረሻም ይሄንን አስመልክተው ሰፊው ህዝብ የሚጠብቀውን ጉልህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማስታወስ፣ በተለይም ተራ ዜጎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መፍታት እንደሚገባ ጠቁመው፥ “ህዝቡ ከአዲሱ ፕሬዚዳንት የሚጠብቀው መንግስት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ፣ የቤተሰብን ችግር ለማቃለል እና የሥራ ዕድልን ለማሻሻል ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስድ ይጠብቃሉ” ካሉ በኋላ ከመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እርምጃዎች በተጨማሪ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ለዕለት እንጀራ የሚታገሉትን ድሆችን ለመደገፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ በመምከር አጠቃለዋል።
 

18 October 2024, 13:12