ፈልግ

ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ፣ የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ፣ የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ 

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ ‘ሲኖዶሱ በሰላም አብሮ የመኖር መንገድን ያሳያል’ አሉ

በመካከለኛው ምሥራቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ያለውን ግጭት አስመልክቶ ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡባዊ ዓረብያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፓኦሎ ማርቲኔሊ ኃይማኖቶች በሰላም አብሮ ለመኖር የሚያደርጉትን ወሳኝ አስተዋጽዖ አጽንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ እየተካሄደ ያለው የሲኖዶሱ ጉባኤም ልዩነቶች በውይይት እና በመደማመጥ እንዴት አብረው ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያሳይ ተጨባጭ ምሳሌ ነው በማለት ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“አሁን ያለውን የግጭት አዙሪት ለማስቆም የዲፕሎማሲውን ግንኙነቶች በአስቸኳይ ማሻሻል ያስፈልጋል” ያሉት ብጹእነታቸው፥ ሆኖም ግን አብረን መሄድ እንደምንችል የሚያሳዩ እና ሃይማኖቶች ለዓለም ሰብአዊነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ የእምነት ሰዎች ምስክርነት ያስፈልገናል ብለዋል።

የበቀል አዙሪትን መስበር
በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ኦማን እና የመን ውስጥ በቤተክርስቲያን መሪነት ከሁለት ዓመታት በላይ የቆዩት ጣሊያናዊው የካፑቺን ማህበር አባል የሆኑት ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ በሮም እየተካሄደ ባለው የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ሮም የሚገኙ ሲሆን፥ በቅድስት ሀገር እና በሊባኖስ በዓረብ ባሕረ ገብ መሬት ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት፣ በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት ስለምትታመሰው የመን በማንሳት፥ ሃገሪቷ በእስራኤል እና በሐማስ ግጭት በቀጥታ እየተጎዳች እንደሆነ እና የሃውቲ አማፂያን ከእስራኤል ጋር ተኩስ እየተለዋወጡ ብሎም በቀይ ባህር መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ስለሚያደርሱት ጉዳት በማንሳት በቀጠናው ውስጥ ስላለው ችግር አብራርተዋል።

ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ በአስቸኳይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንደገና በመጀመር ይህንን የበቀል አዙሪት መስበር እንደሚያስፈልግ አጥብቀው በማሳሰብ “ለሁሉም የሚጠቅም የእርቅ እና የሰላም መንገዶችን መፈለግ አለብን” ብለዋል።

ብጹእነታቸው በማከልም “ጦርነቱ በቅርቡ እንዲያበቃ እንጸልያለን፥ የመልካምነት፣ የመጋራት እና አብሮ የመጓዝ እሴቶቻችንን ለማከናወን እንድንችል የሰላም ጥረቶችን እንደገና ማስጀመር እንችላለን” ብለዋል።

በሰላም አብሮ መኖር ይቻላል
ብጹእነታቸው ካቫቲካን ዜና ጋር ያደረጉትን ቆይታ በመቀጠል የሀይማኖት ማህበረሰቦች ‘ራሳቸውን ለብሔርተኝነት ዓላማ አሳልፎ ባለመስጠት’ ለተሻለ ዓለም ለውይይት እና ለሰላም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚችሉም አስታውሰዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊድና ምኩራብ በሰላም ጎን ለጎን የቆሙባቸውን የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችን እና ኦማንን በምሳሌነት ጠቅሰው፥ በሰላም አብሮ መኖር እንደሚቻል እነዚህ ሃገራት ጥሩ አርአያ እንደሆኑ እና “መንፈሳዊ ትውፊቶችን መካፈሉ ለሁሉም የሚጠቅም መሆኑ ግልጽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሲኖዶስ ቀጥሎ ያለውን መንገድ ያሳያል
እንደ ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ ገለጻ፣ በሲኖዶስ ጉባኤ ላይ እየተካሄደ ያለው የሲኖዶሳዊነት ልምድ፣ ይህንን የሰላም ባህል ለማስፋት ቤተክርስቲያን የምታደርገውን አስተዋጽኦ ተጨባጭ ምስክር እንደሆነ በመጠቆም፥ “ከየትኛውም ቴክኒካዊ ውጤቶች በተጨማሪ እርስ በርስ መደማመጥ ጠቃሚ ነው” ካሉ በኋላ፥ “የልዩነቶቻችንን ብዝሃነት መገንዘብ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጋራ ማስተዋልን መማር ለቤተክርስትያን እና ለዓለም ምሳሌ እንደሆነ፥ ብሎም ህብረተሰቡ በመልካምነት ጎዳና እንዲጓዝ ሊያነሳሳ ይችላል” በማለት አስረድተዋል።

ልዩነቶችን መቀበል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ ወደ እስያ እና ኦሺኒያ አህጉራት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የደቡባዊ አረቢያ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ማርቲኔሊ፣ ቅዱስ አባታችን ወደ ኢንዶኔዥያ ተጉዘው የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት ባወጡት የጋራ የወንድማማችነት ሰነድ ላይ የፈረሙትን ጨምሮ በ 2011 ዓ.ም. በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በ2015 ዓ.ም ደግሞ በባሕሬን ያደረጉትን ሁለት ታሪካዊ ጉብኝቶች በርካታ ተመሳሳይነቶች ያሉት ሲሆን፥ ይህም “ወደ ወንድማማችነት የሚወስደው መንገድ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያሳያል” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ማርትኔሊ በመጨረሻም “ለልዩነቶቻችን ያለን ክብር በጣም አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ካሉ በኋላ፥ የሕይወት ዓላማ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት በሆነበት ቦታ ልዩነቶችን ማሸነፍ ሳይሆን፥ ብዝሃነቱን ተቀብሎ ከሌላው ጋር በሰላም መኖርን ማጣጣም ነው” በማለት አጠቃለዋል።
 

15 October 2024, 13:46