ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጥቅምት 12 ቀን 1971 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጥቅምት 12 ቀን 1971 ዓ.ም. 

ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ‘ሰላም እና ውይይትን’ ያበረታቱ ነበር አሉ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጵጵስና ዕለት መታሰቢያ ሥርዓተ ቅዳሴ ያካሄደች ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ዲዚዊስ ፖላንዳዊው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲመተ ጵጵስና ሲቀበሉ “አትፍሩ ለክርስቶስ በሮችን ክፈቱ” ያሉትን ቃል አስታውሰዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲመተ ርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ያደረጉበትን ጥቅምት 12 ቀን 1971 ዓ.ም. ለማስታወስ ብጹአን ጳጳሳት ሥርዓተ ቅዳሴ በማሳረግ አክብረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ዲዚዊዝ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በዩክሬን እና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስለ ሰላም ያስተማሩት ትምህርት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

‘ውጤታማ ድርድር ላይ መሳተፍ ውርደት አይደለም’
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የኢራቅ ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ መጋቢት 7 ቀን 1995 ዓ.ም. ባደረጉት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ወቅት “ወደ መግባባት ለመምጣት እና ውይይቶችን ለመቀጠል ጊዜው ረፍዶ አያውቅም፥ አንድ ሰው ግዴታውን ለማሰላሰል፣ በጠንካራ ድርድር ውስጥ መግባት ማለት መዋረድ ሳይሆን ለሰላም ሲል በሀላፊነት መስራት ማለት ነው” በማለት ተናግረዋል።

ለ39 ዓመታት የዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ የግል ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ በቃለ ምልልሱ ወቅት ፖላንዳዊው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲሰፍን የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

ብጹእነታቸው በማከልም በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ግምት ውስጥ በማስገባት ዛሬ የዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስተምህሮዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠቃሚ ናቸው ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

“አትፍሩ” - ጊዜ የማይሽረው ጥሪ
ጥቅምት 12 ቀን 1971 ዓ.ም. የጵጵስና ሥልጣናቸውን የጀመሩበትን ቀን አስመልክቶ በተከበረው የቅዱስ ቁርባን በዓል ሥነ ስርዓት ላይ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “አትፍሩ፣ ለክርስቶስ በሮችን ክፈቱ!” በማለት ተምሳሌታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ብጹዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ እነዚህን ቃላት በመጥቀስ፣ ይህ የዕለት ተዕለት ጥሪ እንደሆነ፣ አሁንም ለቤተክርስቲያን፣ ለዘመናዊው ዓለም፣ ለግለሰቦች እና ለተለያዩ ማህበረሰቦች ጠቃሚ እንደሆነ አጉልተው ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ ሰላምን፣ ሕይወትን መጠበቅ፣ የሠራተኞች መብትን፣ የፖለቲካ ክብር፣ የሴት ልሂቃን አድናቆት፣ ቅዱስ ቁርባን እና መለኮታዊ ምሕረትን ያካተቱትን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስተምህሮዎች ላይ በማስተንተን፣ ብጹእ አባታችን ስለ ሕይወት ቅድስና ላሳዩት ጠንካራ አቋም ምስጋና አቅርበዋል።

ብፁዕ ካርዲናሉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አንዴ በብራስልስ የሰውን ሕይወት ከጅምሩ እስከ ተፈጥሯዊ ፍጻሜው ድረስ ያለውን ክብር መጠበቅ እንደሚገባ ስለተናገሩት ቃል እናመሰግናለን በማለትም አክለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ ከሳተሙት ‘ላ ሜታ ኤላ ፌሊቺታ’ (La meta è la felicità) (ግቡ ደስታ ነው) መጽሐፍ መግቢያ ላይ “በተለይ የእሳቸውን ምሳሌ እና የአባትነት እንክብካቤ እንፈልጋለን፣ ነገር ግን አንድ ሰው የበፊቱን ካሮል ዎጅታይላን (የቀድሞ ስማቸው) ሳያውቅ ሙሉ በሙሉ ሊረዳው አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል።

በጣሊያንኛ የታተመው መጽሐፉ ካሮል ዎጅታይላ ሲመተ ጵጵስና ከመፈጸማቸው በፊት የፃፏቸው 366 በአብዛኛው ያልታተሙ ጽሑፎችን ያካትታል።

ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ እነዚህን ቃላት በማንፀባረቅ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አባ ጆርጅ ቤርጎሊዮን (ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ) በአርጀንቲና ጳጳስ አድርጎ እንደሾማቸው እና በኋላም ካርዲናል አድርገው እንደሾሟቸው አመልክተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ በማጠቃለያቸው ሁሉም የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆናቸው እያንዳንዱ ሰው በእነሱ ውስጥ እውነትን እንዲፈልግ እና በእያንዳንዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮ ውስጥ እምነት የሚጣልበት መመሪያ እንዲፈልግ አሳስበዋል።
 

23 October 2024, 14:36