ፈልግ

የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን ማህበር መስራች ብፁዕ ጁሴፔ አላማኖ የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን ማህበር መስራች ብፁዕ ጁሴፔ አላማኖ 

አሁን ባለንበት የ 'ቲክ ቶክ ማህበረሰብ' ውስጥ አሰላሳይ ትውልድ እንደገና ለመፍጠር መጣር እንደሚገባ ተገለጸ

በብፁዕ አባ ጁሴፔ አላማኖ የተመሰረተው የኮንሶላታ ሚስዮናውያን ማህበር የበላይ አለቃ የሆኑት ጣሊያናዊ ካህን አባ ጀምስ ቦላ ሌንጋሪን ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ዕለተ እሑድ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መሪነት ከሚካሄደው ቅድስና የመስጠት መርሃ ግብር አንድ ቀን ቀደም ብሎ በቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት በተዘጋጀው 'የመሰብሰቢያ መድረክ' ላይ ማህበሩ ለትምህርት የሰጠውን ትኩረት በማጉላት ንግግር አድርግርዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“እኛ ነገሮች ሁሉ በፍጥነት የሚሄዱበት የቲክ ቶክ ማህበረሰብ አካል ነን” ያሉት አባ ጀምስ፥ ነገር ግን ‘በነገሮች ላይ በትኩረት የሚያሰላስል እና አስፈላጊ የሆነውን ለይቶ የሚያወጣ ማህበረሰብ’ ለማግኘት መጣር አለብን ብለዋል።

የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን ማህበር የበላይ አለቃ የሆኑት ካህኑ የማህበሩ መስራች ብፁዕ ጁሴፔ አላማኖ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሲለማመዱ የኖሩትን ሰፊ የማህበረሰቡን እሴቶችን በማስታወስ፥ እነዚህ እሴቶች በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል ትክክለኛ እና ጠቃሚ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ከቅድስና ሥነ ስርዓቱ በፊት የተደረገ ውይይት
ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሪነት የተካሄደው የካርዲናሎች መደበኛ ጉባኤ ብፁዕ ጁሴፔ አላማኖን ጨምሮ የ15 ብጹዓንን ቅድስና ማጽደቁ እና የእነዚህ ቅዱሳን ስም በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ እሁድ ጥቅምት 10/2017 ዓ. ም. በይፋ እንደሚጻፍ መወሰናቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሁድ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚመሩትን ቅድስናን የማወጅ ሥነ ስርዓት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የብጹዕ ጁሴፔ አላማኖን ማንነት እና ሥራዎች ለማስታወስ የታቀደው ስብሰባ የተዘጋጀው በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት እንደሆነ ተገልጿል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዲሶቹ ቅዱሳን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1860 ዓ. ም. በሶርያ ከተማ ደማስቆ ውስጥ በሰማዕትነት የተገደሉ እና “የደማስቆ ሰማዕታት” በመባል የሚታወቁ ናቸው።

ከነዚህም ውስጥ አባ ማኑዌል ሩይዝ ሎፔዝ የተባሉ ፍራንችስካዊ ካኅን ከሰባት አጋሮቻቸው፣ አብደል ሞአቲ፣ ፍራንሲስ እና ራፋኤል ማሳብኪ የተባሉ ፍራንቺስካዊ ወንድሞች እንዲሁም ሦስት የማሮናዊት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እንደ ነበሩ ይታወሳል። አሥራ አንዱም የተገደሉት በሶርያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1860 ዓ. ም. ሲሆን፥ በወቅቱ በእምነት ጥላቻ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በሙስሊም ሚሊሻዎች በጭካኔ ተገድለዋል።

የሚስዮናዊው ማስታወሻ
በብራዚል የማኑስ ከተማ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብጹእ ካርዲናል ሊዮናርዶ እስታይነር እና ከ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኮንሶላታ ሚስዮናውያን እህቾች ዋና ጸሃፊ ከሆኑት እማሆይ ሉቺያ ቦርቶ-ሎማሲ እንዲሁም ከሌሎች እንግዶች ጋር በመሆን ንግግር ያደረጉት አባ ጀምስ ሌንጋሪን ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ የብጹዕ አላማኖን “መንፈሳዊነት” በአጽንዖት ገልጸዋል።

የብጹዕ አባ አላማኖ ዝና ከደቡብ ኢትዮጵያ የመጡትን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ካርዲናሎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን፥ ሲያገለግሉበት የነበረው ህዝብ የነበረበትን የመከራ ጊዜ እና የእግዚአብሔር ቃል በአከባቢው በስፋት አለመሰራጨቱን በሚገባ ስላስተዋሉ በብፁዕ አላማኖ ውስጥ ‘ሚስዮናዊ የመሆንን ሀሳብ’ የቀሰቀሰ ግብአት እንደሆነ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን አስቸጋሪው የጤና ሁኔታቸው በግል ይህን እንዲያደርጉ ባይፈቅድላቸውም፥ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተለያዩ ማስታወሻዎችን የመያዝ ልምድን በማዳበር፣ ሰዎችን በመስበክ እና በማዳመጥ እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን እና የህክምና ማዕከሎችን በስፋት በመገንባት በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል።

ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በፍቅር መውደቅ
አባ ጀምስ ሌንጋሪን በምዕራብ አፍሪካ ከዩሩባ ህዝቦች ጋር ለአስርት ዓመታት ያክል የነበራቸውን ቆይታ በማስታወስ፥ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ ህዝቡን “ለማጥመቅ እንኳን ፍላጎት እንዳልነበራቸው፣ ምክንያቱም ብፁዕ አላማኖ ከእሳቸው በፊት ባስተዋወቁት የአሰራር ዘዴ ምክንያት ሕዝቡ ራሱ ስለ ሚስዮናውያን “የተለየ ነገር” እንዳለው ማስተዋላቸውን ተናግረዋል። ምዕመኑ በመጨረሻም “ምን የተለየ ነገር ይዘን እንደሄድን እና ወደ እነሱ ለምን እንደመጡ አጥብቀው ይጠይቁ እንደነበር በማስታወስ፥ ይህ ጥያቄ የብዙ ንግግሮች መነሻ የነበረ ጥያቄ ሲሆን፥ ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ችላ አልተባለም ነበር ብለዋል።

የኮንሶላታ ሚስዮናውያን የበላይ ሃላፊ የሆኑት ካህኑ ብፁዕ አላማኖን ዛሬም ድረስ ከሚገልጹት ጠቃሚ እሴቶች መካከል “ታማኝነት” እንደሆነ ለይተው ማወቃቸውን ገልጸው፥ ‘ሚሲዮናዊው በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ ለመስራት የሚጠበቅባቸውን የሚከተሉ ጥሩ ሰው ነበሩ’ ካሉ በኋላ፥ ይህ በጎነት ከሁሉም በላይ በፍቅር የወደቁበትን የእግዚያብሄር ቃል በማዳመጥ የተንጸባረቀ እንደነበር ገልጸዋል።

በትምህርት እና በስልጠና ላይ ትኩረት ተደርጓል
በወንጌል እንድንሸነፍ መፍቀድ ማለት ብዙውን ጊዜ “ከራሳችን ውጪ” የምንፈልጋቸውን “በውስጣችን” ያሉ መሠረታዊ እሴቶችን እንደገና ማግኘት ማለት እንደሆነ የጠቀሱት አባ ሌንጋሪን፥ ብፁዕ አባ አላማኖ ለትምህርት እና ሥልጠና ትልቅ ትኩረት ይሰጡ እንደነበር በማስታወስ፥ ‘የማያነብ’ እና ‘ራሱን መግለጽ’ የማይችል ማህበረሰብ ዬትም መድረስ እንደማይችል ከምንም ጊዜ በላይ ተረድተው ነበር ብለዋል።

የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን የበላይ ጠባቂ የሆኑት አባ ጀምስ ሌንጋሪን በመጨረሻም ብጹእ አባ አላማኖ ከጎረቤታቸው ጋር እሱ ወይም እሷ በምትጓዝበት መንገድ በጥበብ የመኖርን እና የነበራቸውን አክብሮትን በማስታወስ፥ በፈገግታ ታጅበው “አንዳንድ ጊዜ ስቀልድ እግዚአብሔር ቀለም ስለማይለይ አይነስውር ነው እላለሁ” ያሉት ካህኑ፥ “ልባችን” ክፍት እንዲሆን እና እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን መርዳት እንድንችል አምላክ ዝም ብሎ ሊፈጥረን ይችል ነበር ብለዋል።
 

21 October 2024, 13:30