ፈልግ

"የፍራንቺስካዊያን ወር" በኒው ዮርክ "የፍራንቺስካዊያን ወር" በኒው ዮርክ 

በዚህ የፍራንቺስካዊያን ወር የኮሌጅ ተማሪዎችን ስለ ሰላም እና ግንኙነት ማስተማር እንደሚገባ ተገለጸ

በኒው ዮርክ ግዛት ብሩክሊን ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ፍራንቼስኮ ኮሌጅ የተልዕኮ፣ የአገልግሎት እና የሃይማኖቶች ውይይት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆነው ወንድም ግሪጎሪ ሴሊኒ በተወዳጁ ጣሊያናዊ ቅዱስ እሴቶች በመነሳሳት በያዝነው የጥቅምት ወር ተከታታይ ዝግጅቶች እንደሚዘጋጁ ገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ 

የብሩክሊን ፍራንቺስካዊያን ማህበር አባል የሆነው ወንድም ግሪጎሪ ሴሊኒ በጥቅምት ወር ላይ የሚከበረውን የፍራንስካዊያን ወርን” በማስመልከት በቅዱስ ፍራንቼስኮ ኮሌጅ ውስጥ የተከናወኑ ተከታታይ ዝግጅቶችን ሲገልጽ “በጸጥታ ውስጥ እራስን የማዳመጥ መርሃግብሮች ነበሩ፥ በዚህም በርካታ ሰዎች ያገኙት ነፃነት አስደናቂ ሆነው አግኝተውታል” ብለዋል።

     “ወሩ ከራስ የመራቅ ጉዳይ ነበር፣ በዚህም በርካታ ሰዎች የተሰማቸው ነፃነት አስደናቂ ሆነው አግኝተዋል”

አብዛኛዎቹ ተማሪዎች “ግሬግ” ብለው የሚጠሩት ወንድም ግሪጎሪ በመቀጠል ይህ ዝግጅት ጣሊያናዊው የአሲሲ ቅዱስ ለወንድሞቹ የተወውን ቅርስ በጥልቅ የሚያስተጋባ እንደሆነ በመግለጽ፥ “ማድረግ የሚገባኝን አድርጌአለሁ፣ አሁን ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልናደርገው የሚገባንን ያስተምረን” በማለት ተናግሯል።

ቅዱስ ፍራንቼስኮ ወንድሞቹ እሱን ለመሆን እንዳይሞክሩ በመምከር እንዴት ነፃ ሊያወጣቸው እንደፈለገ በመግለጽ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ለፍራንቼስኮ ዓላማ እንዳለው ሁሉ እንዲሁም ለሁሉም ወንድሞቹ የተለየ ዓላማ ስላለው እነሱ መሆን ለታሰቡለት ዓላማ ይሆናሉ ብሏል።

በ “ፍራንቼስኮ መንገድ” መመስረት
ወንድም ግሬግ ባለፉት ዓመታት በፕሮፌሰርነት እያገለገለ በነበረበት ጊዜያት ወጣቶች ጥሪያቸውን እና ድምፃቸውን እንዲያገኙ መርዳት ተልእኮ አድርጎ ነበር፥ አሁን ደግሞ የተልዕኮ፣ የሃዋሪያዊ አገልግሎት እና የሃይማኖቶች ውይይት ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ሆኖ ከሌሎች ፍራንቺስካዊያን ወንድሞች ጋር በመሆን የፍራንቺስካዊያን ቡድን በማቋቋም በቅዱስ ፍራንቼስኮ ኮሌጅ በሦስት ዋና ዋና ጭብጦች ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ዝግጅቶች በማዘጋጀት ወጣቶችን እያበረታታ ይገኛል።

ዝግጅቱንም በማስመልከት “ቅዱስ ፍራንቼስኮን እና ታላቁን የፍራንቺስካዊያን እንቅስቃሴን ማስተዋወቅ እንፈልጋለን” ካለ በኋላ፥ “ከዚህም ባለፈ ስለ ቅዱስ ፍራንቼስኮ እና እንቅስቃሴው ማስተማር እንፈልጋለን፥ ከሁሉም በላይ ተማሪዎቻችንን፣ መምህራንን እና ሰራተኞቻችንን በፍራንቺስካዊ መንገድ ማገዝ እንፈልጋለን” በማለት ገልጿል።

“ከዚህም ባለፈ ስለ ቅዱስ ፍራንቼስኮ እና እንቅስቃሴው ማስተማር እንፈልጋለን፥ ከሁሉም በላይ ተማሪዎቻችንን፣ መምህራንን እና ሰራተኞቻችንን በፍራንቺስካዊ መንገድ ማገዝ እንፈልጋለን”

የወሩ ተነሳሽነት
የዘንድሮው የፍራንቺስካዊያን ወር የተጀመረው መስከረም 20 ላይ በተደረገ የሰላም ሩጫ ሲሆን፥ በመርሃ ግብሩም ከመላው ዓለም የተውጣጡ የኮሌጅ ተማሪዎች ሀገራቸውን ወክለው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው “ሰላም” እያሉ አደባባዩን ችቦ በመያዝ የዞሩ ሲሆን፥ ‘ሰላም’ የሚለው የዘንድሮው መሪ ቃል ሆን ተብሎ እንደተደረገ እና አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ አንፃር መሪ ቃሉ ምክንያታዊ እንደሆነም ጭምር ወንድም ግሬግ ገልጿል።

በብሩክሊን ሃይትስ ውስጥ ስለተደረጉት ሌሎች ዝግጅቶች ሲገልጽ፥ በዝግጅቱ ቀን በተደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ፣ የመቁጠሪያ ጸሎት እና በተለይም “ያልተመጣጠነ ፍቅር” ብሎ የጠራውን ተማሪዎች ከስልኮቻቸው ጋር ያላቸውን ቁርኝት እንዲያሻሽሉ ለማበረታታት “ከተንቀሳቃሽ ስልክ ነፃ የሆነ ሰዓት” የሚል ዝግጅት በማዘጋጀት አክብረዋል።

ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ጨዋታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ከካህናቱ እና ከተለያዩ ሃይማኖቶች ጋር የሚደረገው የጸሎት ጊዜ ግን “የፍራንቺስካዊያን የጸጥታ ጊዜን” ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው ክፍት ነበር ተብሏል። አንዳንድ ተማሪዎች በጸጥታ ውስጥ ሆነው ማሰላሰልን የመረጡ ሲሆን፥ ሌሎች ደግሞ ከአንድ ሰው ጋር በእግር ለመጓዝ እና ግንኙነቶችን ለማደስ መርጠዋል። ሌላው ትልቅ ክስተት በማንሃታን የኮሎምበስ ቀን ላይ የተደረገ ሰልፍ ሲሆን በወቅቱ ተማሪዎች ስለ ፍራንቺስካዊያን ወር ግንዛቤን የሚፈጥር ባነር ይዘው ነበር ብሏል።

የሚያጓጓ አስተያየት
የተማሪዎች እና የመምህራን አስተያየት እጅግ በጣም አዎንታዊ የነበረ ሲሆን፥ ወንድም ግሬግ ይሄን አስመልክቶ እንደተናገረው በመቁጠሪያ ጸሎት ላይ ከተሳተፉት ተማሪዎች መካከል አንዱ ለአራት ወራት ያክል የመቁጠሪያ ጸሎት እንዳላደረገ መግለጹን፣ የሚገርመው ተማሪው ከዝግጅቱ ጋር ተደራራቢ የማጠናከሪያ ፕሮግራም እንደነበረው ጭምር በመግለጽ “የማጠናከሪያ ትምህርቱን ሰርዞ መጥቶ በመቁጠሪያ ጸሎቱ ላይ ንቁ ሚና ተጫውቷል” በማለት ተናግሯል።

እነዚህ የፍራንቺስካዊያን ወር ዝግጅቶች የኮሌጅ ህይወት ጭንቀቶችን እና ጫናዎችን ለማርገብ፣ ተማሪዎች የእምነት አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን በመንፈሳዊ ተግባራት እንዲገናኙ የሚያስችል ቦታ እንደሚሰጥ ወንድም ግሬግ የገለጸ ሲሆን፥ መርሃ ግብሮቹ ውድ የሆኑ ፍሬዎችን እንዳስገኙ፣ እንዲሁም ተማሪዎቹ ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን “ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና አጠናክሯል፥ ይህ ደግሞ ምናልባትም ከምንም በላይ የሆነ ትልቁ ስኬት ነው” ብሏል።

“ተማሪዎች ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና አጠናክረዋል፥ ይህ ደግሞ ምናልባትም ከምንም በላይ የሆነ ትልቁ ስኬት ነው”

የግንኙነቶች ኃይል
የፍራንቺስካውያን መንገድ በግንኙነቶች ውስጥ የተመሰረተ ነው፥ ይህ ግንኙነት ከእግዚአብሔር፣ ከሌሎች ጋር፣ ከራስ እና ከፍጥረት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ወንድም ግሬግ ያረጋገጠ ሲሆን፥ “ቅዱስ ፍራንቼስኮ ሁሉንም ሰው እና ሁሉንም ነገር ወንድም ወይም እህት ብሎ እንደሚጠራ፣ ለአብነትም ወንድም ፀሐይ፣ እህት ጨረቃ፣ እህት ውሃ፣ ወንድም እሳት ብሎ ይጠራ እንደነበር” ጭምር ገልጿል።

“ቅዱስ ፍራንቼስኮ ሁሉንም ሰው እና ሁሉንም ነገር ወንድም ወይም እህት ብሎ እንደሚጠራ፣ ለአብነትም ወንድም ፀሐይ፣ እህት ጨረቃ፣ እህት ውሃ፣ ወንድም እሳት ብሎ ይጠራ ነበር”

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ
ወንድም ግሬግ በፕሮፌሰርነት እና በዳይሬክተርነት ከሚጫወተው ሚና በተጨማሪ ‘ለሰኞ ስለደረስን እግዜር ይመስገን’ የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅቶ እንግዶችን ሙያዊ እርካታን እና አስተዋፅዖን ስለማሳደግ ግንዛቤዎችን እንዲያካፍሉ ይጋብዛል።

ይሄንንም በማስመልከት እንደተናገረው “ላለፉት አምስት ዓመታት ለተወሰኑት ዝግጅቶቻችንን በተለያዩ ወራት የተለያዩ ጭብጦችን ሰይመን የነበረ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የኩራት ወርን በሰኔ፣ የጥቁር ታሪክ ወርን በየካቲት፣ የሴቶች ታሪክ ወርን በመጋቢት አድርገን አስተላልፈናል ብሏል።

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ለቅዱስ ፍራንቼስኮ የሚውል ቀንስ ዬትኛው ነው የሚለው ሀሳብ ወደ እኔ የመጣ ሲሆን፥ ይህ ሃሳብ የእነዚህ ዝግጅቶች መነሻ ነበር ያለው ወንድም ግሬግ፥ ከዝግጅቶቹ በተጨማሪ፣ ‘ሁሉም መልካም ነገሮች’ የሚባል ድህረ ገጽ በጥቅምት ወር ውስጥ ዕለታዊ አስተያየቶችን ለማካፈል እንደተፈጠረ ገልጿል።

በያዝነው ዓመት በኒውዮርክ ከተማ አካባቢ ከሶስት አህጉረ ስብከት እንዲሁም ከኒው ጀርሲ ከሶስት አህጉረ ስብከት ጋር ትብብር መፈጠሩን በመግለጽ፥ በዚህ አካሄድ ወደፊት የመስፋፋት ተስፋ አለው በማለት ወንድም ግሬግ የተናገረ ሲሆን፥ በጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. ላይ አላማችን ሀገራዊ ክብረ በዓል ማዘጋጀት፣ በ 2026 ደግሞ ቅዱስ ፍራንቼስኮ ወደ ገነት የሄደበትን 800ኛ ዓመት በማክበር ዓለም አቀፋዊ እንሆናለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል።

የቅዱስ ፍራንቼስኮ የሰላም ጸሎት
ወንድም ግሬግ ከቅዱስ ፍራንቼስኮ ጋር ያለው ጥልቅ ግንኙነት ከልጅነት ጀምሮ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፥ የቅዱሱን ሐውልት፣ የወፍ መታጠቢያ ገንዳ ተብሎ የሚታወቀውን ስፍራ፣ በክሊቶን ኒው ጀርሲ የሚገኘውን የቤተሰቡን የአትክልት ስፍራ ያስጌጥ እንደነበረ ያስታወሰው ወንድም ግሬግ፥ “ልጅ ሆኜ ቅዱስ ፍራንቼስኮ ሁልጊዜ የአእዋፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ አስብ ነበር ብሏል።

መጀመሪያ ላይ በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ውስጥ ይሠራ የነበረው ወንድም ግሬግ፥ የፍራንቼስኮን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ሳይረዳ በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ እንደነበር ገልጿል።

“ቅዱስ ፍራንቼስኮ እዚያ የሚሆነው የአትክልት ቦታዎችን ለመጠበቅ ብቻ ነው ብዬ አስቤ ነበር” አስብ ነበር ያለው ወንድም ግሬግ፥ የፍራንቺስካዊያን ወንድም ከሆነ በኋላ ግን የቅዱሱን ጥልቅ ለውጥ እና ተልእኮ የተረዳ ሲሆን፥ ለእርሱ በተሰጠው የሰላም ጸሎት ውስጥ በተካተቱት “የተስፋ፣ የእምነት፣ የመስጠት፣ የመካፈል፣ የመውደድ እና የይቅርታ ቃላት እሱን መረዳት ችያለው ብሏል።

ጥገና የሚያስፈልገውን ዓለም መቀየር
የፍራንቺስካዊያን ወር ዋና ዓላማው የቅዱሱን ሙሉ ታሪክ የማያውቁ ሰዎችን ለመድረስ ሲሆን፥ “ቅዱስ ፍራንቺስኮስ በእውነት ለካቶሊኮች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ለአይሁዶች፣ እስላሞች፣ ቡዲስቶች፣ ሂንዱዎች፣ ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እምነት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀር ለሁሉም ሰው እንደቆመ ያስረዳው ወንድም ግሬግ፥ ብዙ ሰዎች የፍራንቺስካዊያንን የአኗኗር ዘይቤ ቢቀበሉ ዓለም በጣም የተሻለ ቦታ ላይ እንደምትሆን አምናለሁ ብሏል።

ቅዱስ ፍራንቼስኮ በ 1206 ዓ.ም. የተቀበለውን ጥሪ ያነሳው ወንድም ግሬግ፥ “ፍራንቼስኮ ጥገና ያስፈልጋት የነበረውን ቤተክርስቲያኔን እንደገና ገንብቷል” ካለ በኋላ፥ ዛሬ ላይ እድሳት የሚያስፈልጋት ዓለማችን በተመሳሳይ ሁኔታ ለሃይማኖት መስዋዕት መሆን እያንዳንዱን ሰው፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ እየተፈታተነ ያለ ነገር እንደሆነ እንደሚሰማው ገልጿል።

“ቅዱስ ፍራንቼስኮ በእውነት ለሁሉም ነው፣ ካቶሊኮች ብቻ አይደሉም። አይሁዶች፣ እስላሞች፣ ቡዲስቶች፣ ሂንዱዎች፣ ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እምነት ለሌላቸው ሰዎች እንኳ የቆመ ነው”
 

31 October 2024, 12:31