ለሴት ልጅ ፍላጎቷን፣ ክብሯን እና አቅሟን ለማጠናከር ድምጽ እንዲኖራት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ይህ ዓለም አቀፍ የሴት ልጅ ቀን በየዓመቱ በጎረጎሳዊያኑ ጥቅምት 11 ቀን የሚከበር ሲሆን፣ ሴት ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች አጉልቶ ለማሳየት፣ ለመብታቸው ለማብቃትና ለመሟገት የሚያስችሉ ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ የበዓሉ ዋና አላማ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም ባለፈ ዓለም አቀፍ የሴት ልጅ ቀን በየዓመቱ የሚከበረው ሴት ልጅ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ እንዲሁም ለዓለም ያላትን በረከት እና ውድ ሀብት ለዓለም ለማስታወስ ሲሆን፥ አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ፍቅር በሌለበት እና ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ እና ድምፃቸው እንዲሰማ አጥብቀው የሚናፍቁ እንዳሉ ይታወቃል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው የዘንድሮው መሪ ሃሳብ በሴቶች ድምጽ ተጽዕኖ እና የወደፊት ራዕይ የሚመራ፣ አስቸኳይ እርምጃ እና ጽኑ የሆነ ተስፋ አስፈላጊነትን እንደሚያሳይ የገለጸ ሲሆን፥ ዛሬ፣ በብዙ የአፍሪካ ማህበረሰቦች ዘንድ ሴት ልጅ ከቀድሞው በበለጠ ሁኔታ በትምህርት እና በተለያዩ ተሳትፎዎቿ ይበልጥ የምትወደድ፣ የምትመሰገን እና የምትበረታታ ሆናለች። ሆኖም ግን፥ አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ልጃገረዶች ደህንነቱ ባልተጠበቀ አካባቢ እንደሚኖሩ፣ ኢፍትሃዊ በሆኑ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ድርጊቶች እየተጎዱ እና ሴት በመሆናቸው ብቻ በሕይወታቸው ውስጥ የሚሰጣቸው ዕድል አነስተኛ እንደሆነ ይታወቃል።
ቤተክርስቲያን ለሴት ልጅን ክብር ትሰጣለች
ከበርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም ቡድኖች ጋር በመተባበር የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ሴት ልጅን በትምህርት፣ ልዩ ልዩ ክህሎቶችን በመስጠት እና የሴቶች ጥበቃ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በማጎልበት በትጋት መሥራቷን ቀጥላለች። ከእነዚህ ቡድኖች አንዱ የናይጄሪያ ሴት ገዳማዊያት ጉባኤ (NCWR) ሲሆን፥ በሃዋሪያዊ ሥራ ተግባሮቹ እና ፕሮጄክቶቹ የሴት ልጅን ክብር ለማስተዋወቅ የሚተጋ ሀገር አቀፍ የናይጄሪያ ገዳማዊያት እህቶች ትስስር ነው።
የሴቶች የወደፊት ራዕይ
በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ እየተከሰተ ባለው ጦርነት፣ ድህነት እና የአየር ንብረት ቀውስ ዓለም አቀፋዊ እውነታ በመሆኑ ምድራችን ለመኖር በጣም ፈታኝ ቦታ ያደርጋታል ተብሏል። እያንዳንዱ ልጅ በተለይም ሴት ልጅ በፍቅር፣ ሰላማዊ እና ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ መኖር ይፈልጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሴት ልጅ አቅሟን ሙሉ በሙሉ የምታዳብርበት እና ለህብረተሰቡ አወንታዊ የሆነ አስተዋፅዖ የምታደርግበት የወደፊት ጊዜን ትፈልጋለች።
ዓለም በዚህ ዓመት የሴት ልጅ ቀንን 'የልጃገረዶች የወደፊት ራዕይ' ብሎ ሲያከብር ህብረተሰቡ ማስታወስ ያለበት የተባበሩት መንግስታት ሰነድ እንደሚያሳየው “ሴቶች በአመራር ቦታ ላይ ሲቀመጡ የሚያሳድሩት ተፅዕኖው ፈጣን እና ሰፊ እንደሆነ፥ እንዲሁም የቤተሰቦችን፣ የማህበረሰቦች እና የኢኮኖሚውን አቅም የበለጠ ጠንካራ እንደሚያደርጉ ብሎም የወደፊት ሕይወታችንን ብሩህ እንደሚያደርጉ” መገንዘብ አለበት ተብሏል።