ፈልግ

አንድ መነኩሴ እየሩሳሌም በሚገኘው የቅዱስ ሴፑልክር ቤተክርስቲያን አጠገብ ሲራመዱ አንድ መነኩሴ እየሩሳሌም በሚገኘው የቅዱስ ሴፑልክር ቤተክርስቲያን አጠገብ ሲራመዱ  (AFP or licensors)

በእስራኤል የሚኖሩ የዕብራይስጥ ተናጋሪ ካቶሊኮች የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ጥሪ ተቀብለው ሰላም እንዲሰፍን ፆም ጸሎት አደረጉ

እስራኤላዊያን እና የዕብራይስጥ ተናጋሪ ካቶሊኮች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ጋር በመሆን መስከረም 27ን በጸሎት፣ በጾም እና በንስሓ ማሳለፋቸውን የቅዱስ ያዕቆብ ሃዋሪያዊ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቀጠናው ተጥናክሮ በቀጠለው ግጭት እና ስር የሰደደ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ሆነው በእስራኤል የዕብራይስጥ ቋንቋ ተናጋሪ ካቶሊካዊ ማህበረሰቦች መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በቂርያት ዬዓሪም መንደር ውስጥ በሚገኘው “የእመቤታችን የቃል ኪዳን ታቦት” ተብሎ በሚጠራው ገዳም ውስጥ ዓመታዊ ስብሰባቸውን ለማድረግ በተሰበሰቡበት ወቅት ለምድራችን ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አድርሰዋል።

የቅዱስ ያዕቆብ ሃዋሪያዊ አስተዳደር ካህን የሆኑት አባ ፒዮትር ዘላዝኮ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዓለም ሰላም እንዲሆን ያቀረቡትን የፆም ጸሎት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት አስመልክተው ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።

“እዚህ እስራኤል ውስጥ ያለው ነገር በጣም ከባድ ነው” ያሉት ካህኑ፥ “ባለፈው ዓመት መስከረም 27 በአከባቢው ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ጥቃት ለተጎዱ ሰዎች የጸለይን ሲሆን፥ ምን ያህል ግፍ እንደደረሰብንም አስታውሰናል” ብለዋል።

ይህ ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መስከረም 27 ለዓለም ሰላም የጸሎት እና የንስሐ ቀን እንዲሆን ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ለፆም ጸሎቱ ለመዘጋጀት ታስቦ የተካሄደም ጭምር መሆኑን አክለዋል።

ከካህኑ በተጨማሪ የጃፋ ደብር ምዕመን የሆኑት የሁለት ሴት ልጆች አባት አቶ ዬፊም ፋይተርበርግ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ የማህበረሰቡን ስብሰባ አስፈላጊነት አጉልተው በማንሳት፣ “ልጆቻችን ተመሳሳይ እምነት ካላቸው ልጆች ጋር እንዲገናኙ እና በትንሹም ቢሆን እንዲተገብሩት ማድረግ አስፈላጊ ነው” ካሉ በኋላ፥ “ቤተ ክርስቲያናችን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ጥልቅ ፍላጎት አላት፥ ስለዚህ እኛም በበኩላችን ዓለምን በተሻለ ሁኔታ መለወጥ እንደምንችል አምናለሁ” ብለዋል።

በትግል መካከል ያለ የተስፋ ዓመት
እነዚህ ማህበረሰቦች አንድ ላይ ለመሰባሰብ እየጣሩ ያሉት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ጉዟቸው ከፍተኛ ስቃይ እና ሀዘን ውስጥ ሆነው ነው።

አባ ዘላዝኮ ይሄንን አስመልክተው “በዚህ ስብራት መካከል፣ የዕብራይስጥ ተናጋሪ ካቶሊኮች ጥልቅ በሆነው እምነታቸው እና በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ተስፋዎች ላይ በመመሥረት የሰላም እና የፈውስ ራዕይን ይከተላሉ” ብለዋል።

የዕብራይስጥ ተናጋሪ ካቶሊኮች እስራኤል ሰሞኑን በምታከብረው የአዲስ ዓመት በዓል ላይ በመሳተፍ ከእስራኤል ማህበረሰብ ጋር ያላቸውን አንድነት እንደሚያሳዩ ካህኑ ጨምረው ገልጸዋል።

የቅዱስ ያዕቆብ ሰበካ ሃዋሪያዊ ሥራዎች አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ ሞኒካ ፋኤስ በበኩላቸው “በሮሽ ሃሻናህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ወደ አዲሱ ዓመት ስንገባ፣ ጸሎታችን ከማህበረሰባችን አልፎ ወደ ሁሉም ሰው ይደርሳል” ካሉ በኋላ ለሰው ልጅ በሙሉ ሰላም፣ ፈውስ እና መታደስ እንዲሆን ተስፋ እናደርጋለን፥ በልባችን የምንይዘውም ይህንን ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የዕብራይስጥ ቋንቋ ተናጋሪ ካቶሊኮች ለዓለም ሰላም እንዲሆን የፆም ጸሎት ቀናቸውን ያጠናቀቁት በኢየሩሳሌም በሚገኘው ሃዋሪያዊ ሰበካ ውስጥ የጦርነት ሰለባዎች በሙሉ ባስታወሱበት መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሆነም ተነግሯል።

የአይሁድ ዘር ከሆኑት ጋር መገናኘት
በእስራኤል ውስጥ ያሉት ዕብራይስጥ ተናጋሪ የካቶሊክ ማህበረሰቦች ከአይሁዶች ባህል እና ቋንቋ ጋር ባላቸው ጥልቅ ትስስር ምክንያት ልዩ እንደሚያደርጋቸው፣ ብሎም የተለያየ መሰረት ያላቸውን እና በክርስትና እና በአይሁድ እምነት መሃል ላይ ያሉትን ካቶሊኮች አንድ በማድረግ ላይ እንደሆኑም የተነገረ ሲሆን፥ እነዚህ ማህበረሰቦች የክርስትና እምነታቸውን በዕብራይስጥኛ እንደሚያከብሩ፣ እንዲሁም በክርስትና እና በአይሁድ እምነት መካከል ጥልቅ የሆነ ግንኙነትን እንደሚያመጡም ተገልጿል።
 

09 October 2024, 14:25