በሕንድ የተዘጋጀ ስብሰባ ወጣቶችን ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክሩ ማነሳሳቱ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ክርስቶስ ሕያው ነው! እርሱ ተስፋችን ነው” በማለት ይፋ ባደረጉት የድኅረ-ሲኖዶስ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ለማሰላሰል ከሕንድ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣት ካቶሊካዊ መሪዎች በጃላንድሃር ከተማ ተሰብስበዋል።
በሕንድ ጃላንድሃር ከተማ የተካሄደው 6ኛው ብሔራዊ የወጣቶች ስብሰባ ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 598 ልኡካንን ያቀፈ ሲሆን ከነዚህም መካከል የህንድ ካቶሊካዊ ወጣቶች ንቅናቄ (ICYM) መሪዎች፣ የወጣቶች ተወካዮች እና ካህናት እንዲሁም ከ14 ክልሎች እና ከ 81 ሀገረ ስብከቶች የተወጣጡ መሆናቸው ታውቋል።
በንድ ካቶሊካዊ ወጣቶች እንቅስቃሴ (ICYM) የተዘጋጀው እና ከጥቅምት 11-15/2017 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደው ስብሰባ ወጣት ካቶሊካውያን ቤተ ክርስቲያናቸውን በመገንባት ላይ ባላቸውን የጋራ ሃላፊነት ላይ አፅንዖት ሰጥቷል።
ክርስቶስን ለሌሎች በሃላፊነት እንዲመሠክሩ የቀረበ ጥሪ
ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች በመመስከር ጭብጥ ላይ ያተኮረው ይህ ጉባኤ የሕንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና የተግባር መርሃ ግብር ሲሆን፥ ኢየሱስን ለሌሎች በማስተዋወቅ ረገድ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ሚና እንዲጫወት ጉባኤው አሳስቧል።
በሁከት እና ብጥብጥ በተሞላ ዓለም ውስጥ ወጣቶች ወንጌልን ከመንፈሳዊ እና ከእምነት ጉዳዮች አልፈው ወደ ማኅበራዊ ተሃድሶዎች እንዲወስዱ ቤተ ክርስቲያን እንደምትጠራቸው ብሔራዊ የወጣቶች ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቼታን ማቻዶ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
የስብሰባው አንዱ የትኩረት ነጥብ ወጣቶች በማኅበራዊ ተግባር ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደ ነበር የተገልጸ ሲሆን፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች በሚዲያ ትረካዎች ከመታለል ይልቅ መረጃን በትችት እንዲገመግሙት፣ ኢፍትሃዊነትን እንዲቃወሙ እና ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር በመሆን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖች የጥናት ቡድኖች እንዲሳተፉ ተበረታተዋል።
የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች
በስብሰባው ላይ ወጣቶችን የሚያጋጥሙ ግንኙነት ያላቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች የተጠቀሱ ሲሆን፥ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚደርሰው ጫና እየጨመረ መምጣቱ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ እና ይህም ብዙውን ጊዜ በምናባዊ እና በተጨባጭ የሕይወት ተሞክሮዎች መካከል አለመመጣጠን ስለሚፈጥር ወጣቶች ላይ ላዩን የሕይወት አካሄድ ብቻ እንዲከተሉ ማድረጉ ተገልጿል።
ሌላው ተግዳሮት ለወጣት ካቶሊካውያን አግባብነት ያለው የእምነት ትምህርት አለመዘጋጀቱ ሲሆን፥ ይህም የውጭ ተጽእኖዎች እምነታቸውን እንዲሸፍኑ፣ በሃይማኖታዊ ውጥረቶች እና ዓለማዊነት መካከል ስለ ክርስቶስ በግልጽ ለመመስከር እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ተገልጿል።
ሌሎች ተግዳሮቶች፥ የአእምሮ ጤና ጉዳዮች፣ ሥራ አጥነት፣ የሕይወት አጋሮችን ዘግይቶ ማግኘት እና በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መንከባከብ የሚሉት እንደሚገኙባቸው እና ያልተስተካከሉ የቤተሰቦች አሉታዊ ተፅእኖ እና የትውልድ ክፍተቶችም ተብራርተዋል።
ወደፊት ለመጓዝ የሚያግዝ መንገድ
እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ስብሰባው የሚከተሉትን ቁልፍ ምክሮችን አቅርቧል፥
በቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ በሰበካ ማኅበረሰቦች እና በወጣቶች መካከል የላቀ ትብብር መፍጠር፣ የቅዱስ ቁርባንን አስፈላጊነት ማደስ፣
በጸሎት እና በተግባራዊ የማሰላሰል ሂደት ላይ ያለውን ንቁ አመለካከትን ማሳደግ፣ ወጣቶች ተስፋቸውን እና ስጋታቸውን እንዲገልጹ፣ ተግዳሮቶቻቸውን እንዲረዱ እና መመሪያን እንዲፈልጉ በማድረግ ክፍት የውይይት መድረኮችን መፍጠር፣
ውጫዊ ተጽእኖዎችን እንቋቋሙት ለማስቻል ወጣቶችን በእምነት ትምህርት ማጠናከር፣
በወጣቶች መካከል እየቀነሰ የመጣውን ተነሳሽነት ለመቅረፍ እና ጠንካራ የውጭ ድጋፍ ለማድረግ የምክር እና የጋራ ልምዶችን የሚያገኙባቸውን ዕድሎች መስጠት፣
ለሚስዮናዊነት ስልጠና ቅድሚያን መስጠት፣ ሙያዎችን ለማጠናከር የአጭር ጊዜ የማኅበረሰብ ኑሮ ልምዶችን መስጠት፣
ሁሉን አቀፍነት ማጎልበት፣ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ለታዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ከባህላዊ የቤተ ክርስቲያን ተግባራት ርቀው የሚገኙትን ጨምሮ በየአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ጭምር መድረሱን ማረጋገ፣
ቀጣይነት ያለው የኑሮ ልምዶችን ማበረታታት፣ ለፈጠራ ያላቸውን ፍቅርን ማጎልበት እና ዘላቂ ልምዶችን መተግበር፣
ለወጣቶች የሚሰጥ አገልግሎት ክስተት ተኮር ከመሆን ይልቅ ለስልጠና ትኩረት በመስጠት ዕውቅናን ለማግኘት ከሚደረግ ጥረት ይልቅ አገልግሎትን በማስቀደም የአገልጋይነት አመራርን ማሳደግ የሚገባ መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች ተገንዝበዋል።
የሕንድ ካቶሊክ ወጣቶች እንቅስቃሴ (ICYM)
በሕንድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1999 የተመሠረተው የቁምስና ወጣቶች እንቅስቃሴ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ሰበካዎች ውስጥ የሁሉንም ወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት ለማበረታታት በሕንድ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ በወጣቶች ኮሚሽን ሥር ሆኖ የሚሠራ እንቅስቃሴ እንደሆነ ታውቋል።