የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የአሥራ አንዱን ሰማዕታት የቅድስና አዋጅ የተመለከተ ዜናን ማጋራቷ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአሥራ አንዱ የደማስቆ ሰማዕታት የቅድስና አዋጅ
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1860 በሶርያ ዋና ከተማ ደማስቆ በክርስቲያኖች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ሰለባ ለሆኑት አሥራ አንድ የደማስቆ ሰማዕታት ርሠዕ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 10/2017 ዓ. ም. የቅድስና ማዕረግ መስጠታቸው ይታወሳል። የክርስትና እምነትን በሚጠሉ በድሩዝ ሺኣ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባደረሱት ጥቃት ከመቶ ዓመት በፊት የተገደሉ ክርስቲያኖች የብጽዕና ማዕረግ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፒዩስ 11ኛ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከእነርሱ መካከል በደማስቆ ውስጥ በክርስቲያኖች መንደር በሚገኝ ገዳም ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከሐምሌ 9-10/1860 ምሽት ላይ የተገደሉት ስምንት ፍራንሲስካውያን እና ሦስት ማሮናዊ ምዕመናን ይገኙበታል። ይህ አሳዛኝ ክስተት የፈረንሳይ ተጓዥ ቡድንን ወደ ሊባኖስ እንዲያመሩ ያደረገ እና የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ወደ አውሮፓ ለመሰደድ የተገደዱበትን ጊዜ የሚያመልክት እንደነበር ይታወቃል።
በዩክሬን ኦርቶዶክሶች መካከል የተፈጠረው ክፍፍል
በዩክሬን ቼርካሲ የሚገኝ የቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በቁጥጥር ሲወድቅ ሁከት መቀስቀሱ ይታወሳል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2019 ጀምሮ ከሞስኮ ፓትርያርክ ነፃ የሆነችው የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል በሞስኮ ፓትርያርክ ስትደገፍ የቆየች ቢሆንም በሁለቱ አገራት መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ዛሬ ካቴድራሉን የዩክሬይን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተዳድረው ታውቋል።
የዩክሬን ጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ካህን ካቴድራሉን ወደ “ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን” ለመቀየር ማቀዳቸውን ሲያስታውቁ በውስጡ ተጠልለው በሚገኙት ምእመናን መካከል ግጭት ተፈጥሮ አሥራ አራት ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል። በበጋ ወቅት በዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተጣለው እገዳ በሩሲያ ተጽእኖ ላይ ውጥረት ማስከተሉ ታውቋል።
በሞሱል የሚገኝ የማር ቶማ ቤተ ክርስቲያን ደወልን ወደ ነበረበት ማስመለስ
ሶርያ ውስጥ በሞሱል የሚገኝ የማር ቶማ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተማይቱ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በተያዘችበት ወቅት የወደመው እና በምዕራብ ፈረንሳይ እንደተሠራ የሚነገርለት የቤተ ክርስቲያን ደወል በቅርቡ አገልግሎት እንደሚጀምር ተነግሯል።
60 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው እና 55 ሴንቲ ሜትር ቁመት ያለው ይህ ደወል ከነሐስ የተሠራ ሲሆን፥ በዮሐ. 8: 32 እንደተጻፈው “እውነት ነፃ ያወጣችኋል” የሚለውን ጥቅስ ጨምሮ በሌሎች ንድፎች እና ቅርጾች ያጌጠ እንደ ሆነ ተመልክቷል።
የደወሉ አንደኛው ወገን የማር ቶማን ምስል የሚያሳይ ሲሆን፥ ሌላኛው በኩል ደግሞ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገጽታን እንደሚያመልክት ታውቋል። ደወሉ በታህሳስ ወር ወደ ሞሱል እንደሚላክ እና ከመጋቢት ወር 2017 ዓ. ም. ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ይጠበቃል።