ፈልግ

በደቡብ ፊሊፒንስ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች በዳቫኦ ከተማ በተካሄደው የ2024 የሚንዳኖ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ ለሰላምና ለፍትህ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል በደቡብ ፊሊፒንስ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች በዳቫኦ ከተማ በተካሄደው የ2024 የሚንዳኖ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ ለሰላምና ለፍትህ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል  

በፊሊፒንስ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ለሰላም እና ፍትህ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋገጡ

የፍሊፒንስ ሁለተኛ ትልቋ ደሴት በሆነችው ሚንዳናኦ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች በቅርቡ በዳቫኦ ከተማ በተካሄደው የሚንዳናኦ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ (MiRLeC) ላይ ለሰላም እና ለዘላቂ ልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከተለያዩ የሀይማኖት ማህበረሰቦች የተውጣጡ ቁልፍ ግለሰቦችን ያካተተው የሚንዳናኦ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ ስብሰባ ፍፃሜ ላይ እንደተገለጸው በግጭት ውስጥ በሚገኙ ክልሎች ላይ ሰላምን በማስፈን ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በአጽንኦት የተገለጸ ሲሆን፥ “እኛ ሰላም ፈጣሪዎች ነን፥ በፍትህ ላይ የተመሰረተ ሰላም ማስፈን የኛ ግዴታ ነው” ሲል የጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ የወጣው መግለጫ አስነብቧል።

መሪዎቹ በመግለጫቸው “ይህ ቁርጠኝነት በፍቅር፣ ፍትህ፣ ስምምነት፣ መከባበር፣ ታማኝነት፣ አንድነት፣ እርቅ፣ መንፈሳዊነት እና ሰብአዊነት እሴቶች የሚመራ ነው” ብለዋል።

የፊሊፒንስ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ አባ ሬክስ ሮካ-ሞራ እንዳሉት የሚንዳናኦ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ 24 የሙስሊም ኡለማዎች እና መሪዎች፣ 20 ብጹአን ጳጳሳት እና የክርስቲያን መሪዎች፣ ሶስት የአገሬው ተወላጅ ተወካዮች እና 10 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አባላትን እንደ ታዛቢ ያካተተ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሚንዳናኦ የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ወክለው የሚያገለግሉት ካህኑ እንደገለጹት እ.አ.አ. በ1996 ዓ.ም. በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ የተቋቋመውን የጳጳሳት-ኡላማ ጉባኤ (BUC) ለማሻሻል ያለሙ የመጀመሪያዎቹ ስብሰባዎች በነሐሴ ወር መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የጳጳሳት-ኡላማ ጉባኤ የተመሰረተው በፊሊፒንስ መንግስት እና በሞሮ ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት ተነሳሽነት እንደሆነም ጭምር ካህኑ ገልጸዋል።

የሃይማኖት መሪዎቹ በሚንዳናኦ ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ መልካም አስተዳደር እና ሰላምን ለማስፈን የሚያግዝ “ዘላቂ የሆነ የሰላም ንቅናቄ” ለማድረግ የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ጭምር አመላክተዋል።

የጉባኤው ዋና ጥረት በባንግ-ሳሞሮ ራስ ገዝ ክልል የሚንዳኖ ሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ እና ከዛም ባሻገር በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች ዘንድ ሰላምን ለማስፈን መሆኑን በመግለጫቸው አስገንዝበዋል።

መግለጫው በተጨማሪም በሙስሊም፣ በክርስቲያን እና በሃገሬው ተወላጅ ማህበረሰቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን “በአብሮነት መንፈስ የሃይማኖታዊ ትብብርን” ለማጎልበት የሃይማኖት ተቋማት ውይይት አስፈላጊነትን ጎላ አድርጎ ገልጿል።

መሪዎቹ የሱሉ ደሴቶችን መገለል፣ የአካባቢ ጥበቃ ኢፍትሃዊነት፣ ጽንፈኝነት እና ሽብርተኝነትን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ያነሱ ሲሆን፥ ከፖለቲካ መሪዎች፣ ከወጣት ድርጅቶች እና ከአገሬው ተወላጅ ቡድኖች ጋር “የሰላም ውይይቶችን እና ንግግሮች” መጀመር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ ጸሎት እና መንፈሳዊ ስብሰባዎች በተለያዩ እምነቶች መካከል አንድነትን ለመገንባት ወሳኝ ተግባራት እንደሆኑ ያስረዳው መግለጫው በመጨረሻም፥ “የሰላም ንግግሮችን እና ውይይቶችን ማስፋፋት፣ ሰላም ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከር፣ ከፖለቲካዊ እና ከሌሎች መሪዎች ጋር መነጋገር እንዲሁም ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና የአገሬው ተወላጆችን ማብቃት የመሳሰሉ የተጠናከረ የሰላም ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል” በማለት ተጠናቋል።
 

16 October 2024, 13:43