ፈልግ

በጎርፍ ተጥለቅልቆ የነበረው በለጋዝፒ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የፖላንጊ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጠለያ ለሚፈልጉ 300 ለሚጠጉ ተፈናቃዮችን እያስተናገደ ነው በጎርፍ ተጥለቅልቆ የነበረው በለጋዝፒ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የፖላንጊ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጠለያ ለሚፈልጉ 300 ለሚጠጉ ተፈናቃዮችን እያስተናገደ ነው  

በፊሊፒንስ የሚገኙት የካቶሊክ ሃገረ ስብከቶች በአውሎ ንፋስ አደጋ የተጎዱትን ለመታደግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተነገረ

በፊሊፒንስ የተከሰተው ‘ትራሚ ታይፎን’ የተሰኘው አውሎ ነፋስ በሃገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ባስከተለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ብዙ አደጋ በመድረሱ፣ ከብሔራዊ ካሪታስ የተውጣጡ የነፍስ አድን ቡድን፣ በአደጋው በተጎዱ አካባቢዎች ካሉ የካቶሊክ አህጉረ ስብከት ጋር በመሆን የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሥራቸውን በማስተባበር እና ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት ሥራ መጀመራቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአካባቢው የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማህበራዊ ሥራዎች ክንፍ የሆነው ካሪታስ ፊሊፒንስ በታይፎን ክሪስቲን (ዓለም አቀፍ ስሙ፡ ትራሚ) የተጎዱ ወይም በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሀገረ ስብከቶች የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ቡድኖችን እንዳደራጁ አስታውቋል።

የካሪታስ ፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹእ አቡነ ኮሊን ባጋፎሮ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት “እኛ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር አስቸኳይ እና ውጤታማ የሆነ እርዳታ በጣም ለተቸገሩት መድረሱን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።

የሀገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ቅነሳ እና አስተዳደር ምክር ቤት (NDRRMC) ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ በ14 አውራጃዎች ውስጥ ያሉ 77,910 ቤተሰቦች በታይፎን ክሪስቲን ተፅዕኖዎች መጎዳታቸውን ገልጿል። ከዚህም ባሻገር ካሪታስ ፊሊፒንስ እንደዘገበው የካቶሊክ አህጉረ ስብከት የጉዳቱን መጠን ለመገምገም እና ተገቢውን ምላሽ ለመወሰን ፈጣን ገምጋሚ ቡድኖችን ማሰማራቱን አስታውቋል።

ብጹእ አቡነ ኮሊን በበኩላቸው “የተጎዱትን ማህበረሰቦች አስቸኳይ ፍላጎቶች ለመገምገም እና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በአካባቢያችን ከሚገኙ የካሪታስ ቢሮዎች ጋር በቅርበት እየሰራን ነው” ብለዋል።

በናጋ ከተማ የሚገኘው የካሴ-ሬስ አህጉረ ስብከት የፔናፍራንቺያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ ክርስትያን እና በኢዬሱሳውያን የሚተዳደረው አቴንኦ ዴ ናጋ ዩንቨርስቲን ጨምሮ ቢያንስ 25 ደብሮች እና የቤተክርስቲያን ተቋማትን በአደጋው ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች ጊዜያዊ ማረፊያ ማዕከል እንዲሆኑ ክፍት ማድረጉን ገልጿል።

በጎርፍ የተጎዱ ማህበረሰቦችን ለመርዳት “የደብራችንን እና የተቋሞቻችንን አቅም እያጠናከርን እንገኛለን” ያለው ሃገረስብከቱ፥ ህብረተሰቡም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ከዚህን በፊት በጎርፍ አደጋ ተጎድቶ የነበረው የሌጋዝፒ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት መጠለያ ለሚፈልጉ ቤተሰቦች ክፍት መሆናቸውም የተጠቆመ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ የፖላንጊ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በጎርፍ ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ወደ 300 የሚጠጉ ግለሰቦችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ተነግሯል።

እርጉዝ እና የሚያጠቡ እናቶች ከነልጆቻቸው እንዲሁም ህመምተኞች እና አረጋውያንን ጨምሮ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ካህናት መኖሪያ እና የተሻሉ ቦታዎች መወሰዳቸውን ቁምስናው ዘግቧል።
 

24 October 2024, 14:58