ፈልግ

የጥቅምት 24/2017 ዓ.ም የ29 እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ! የጥቅምት 24/2017 ዓ.ም የ29 እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ!  (Dmitry Kalinovsky)

የጥቅምት 24/2017 ዓ.ም የ29 እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ!

"የጥምቀት ጸጋን የሚያድስልን መንፈስ ቅዱስ ነው"!

የእለቱ ንባባት

1.    ኢሳያስ 53፡2.3. 10-11

2.    መዝሙር 32

3.    ዕብራዊያን 4፡14-16

4.    ማርቆስ 10፡35-45

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የያዕቆብና የዮሐንስ ጥያቄ

ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት። ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።

እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት።

ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው።

ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ። ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።”

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት ከማር. 10፡ 35-45 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ያዕቆብ እና ዮሐንስ ኢየሱስን በመንግሥቱ ክብር፣ አንዳቸውን በቀኙ፣ አንዳቸውን በግራው እንዲያስቀምጣቸው ያቀረቡለትን ጥያቄ አስመልክቶ የሚናገር ነው። ነገር ግን ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ ተቆጡ። በዚህን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ታላቅ ትምህርት እንዲህ በማለት አስተማራቸው።

እውነተኛ ክብር የሚገኘው በሌሎች ላይ በመነሣት ሳይሆን፣ እርሱ ራሱ ከትንሽ ጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም የሚጠመቀውን ጥምቀት መጠመቅ የቻሉ እንደሆነ፣ ይህም እርሱ የሚጠጣውን የመከራ ጽዋ መጠጣት የቻሉ እንደሆነ በማለት ነገራቸው። ይህ ምን ማለት ነው? መጠመቅ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳለፈውን የስቃይ መንገድ ማለፍ ማለት ነው። ኢየሱስ እኛን ለማዳን ሲል ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ። ስለዚህም ይህን በማድረጉ የእግዚአብሔርን ክብር አገኘ። ይህ ክብር ሌሎችን በኃይል ለመጫን የተቀበለው ክብር ሳይሆን ወደ ፍቅር የተለወጠው የአገልግሎት ክብር ነው። በሌሎች ላይ የበላይነትን ለማግኘት የሚያስችል የኃይል ፍላጎት ወይም ምኞት አይደለም። ነገር ግን ወደ አገልግሎት የሚለወጥ የፍቅር ፍላጎት ወይም ምኞት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እና ለእኛም እንዲህ በማለት መልዕክቱን ያጠቃልላል። በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ መሆን አይገባም፤ ከመካከላችሁ ትልቅ ሊሆን የሚፈልግ አገልጋያችሁ መሆን አለበት፤ (ማር. 10፡43) ትልቅ ለመሆን ከፈለጋችሁ የአገልግሎት መንገድን መከተል እና ሌሎችን ማገልገል ይኖርባችኋል።

በሁለት የተለያዩ አመክኖዎች ወይም አስተሳሰቦች መካከል እንገኛለን፥ እነዚህም ደቀ መዛሙርት ከፍ ብለው ለመታየት ሲመኙ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ አገልጋይነት ደረጃ ለመውረድ ይፈልጋል። ጊዜ ወስደን እነዚህን ሁለት አስተሳሰቦች እንመልከታቸው። የመጀመሪያው “ራስን ከፍ ማድረግ” የሚል ሲሆን ይህ አስተሳሰብ ወይም ምኞት ሁልጊዜ የምንፈተንበት ዓለማዊ ምኞትን ያመለክታል። ፍላጎታችን ለማገዝ፣ የስኬት መሰላልን ለመውጣት ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊኖረን የምንፈልጋቸውን ማኅበራዊ ግንኙነቶች ጨምሮ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ የምናደርጋቸውን ጥረቶች ያካትታል። በመንፈሳዊው ዓለምም የሚታይ የግል ክብር ፍለጋ በሽታ ሊሆን ይችላል። ይህን የመሰለ የክብር ፍለጋ ከመልካም ዓላማዎች በስተጀርባ ያለ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ሃላፊነት ለተጣለብን የእግዚአብሔር ሕዝብ መልካም አገልግሎትን እያበረከትን፣ ወንጌልን እየሰበክንላቸው፣ ይህን በምናደርግበት ጊዜ ምናልባትም እራሳችንን ከሌሎች ነጥለን ማንነትን የመገንባት ማረጋገጫ እንፈልግ ይሆናል፤ በዚህም ከሌሎች በልጠን ለመታየት እና ወደ ፊት ቀድመን ለመውጣት እንፈልግ ይሆናል። በመሆኑም የልባችን ምኞት እና ፍላጎት ምን እንደሆነ ዘወትር ማየት መፈተሽ ይኖርብናል። “ይህን ሥራ የምሰራው ለምንድነው? ይህን ሃላፊነት የተቀበልኩት ወይም የተሸከምኩት ለምንድነው?” ብለን እራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። “በእውነት ሌሎችን ለማገልገል ነው ወይስ ምስጋናን ለመቀበል?” ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ዓለማዊ አስተሳሰቦችን ከራሱ ሕይወት ጋር በማነጻጸር እንዲህ በማለት ያስተምረናል፥ እራስን ከፍ ከማድረግ ይልቅ እራስን ዝቅ በማድረግ ለማገልገል መቆም እንደሚያስፈልግ ፣ እራስን ዝቅ በማድረግ የሌሎችን ሕይወት መጋራት እንደሚያስፈልግ ያስተመረናል። ሁሉም ሰው ሳይራብ በልቶ እንዲያድር የሚያሳስብ አንድ የበጎ አድራጊ ድርጅት የቴሌቪዥን ፕሮግራም እመለከት ነበር እና፣ ይህ ፕሮግራም ሰዎችን ባጋጠማቸው የረሃብ አደጋ ላይ መጨነቅን፣ እንዲሁም በበርካታ ሰዎች ፍላጎቶች ላይ መጨነቅን የሚያሳይ ነበር። በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ የሰዎች ዕለታዊ ፍላጎቶች እጅግ ጨምረዋል። ስለዚህ የሰዎች ችግር በጨመረበት ባሁኑ ጊዜ የራስን ክብር ለመጨመር ከመጨነቅ ይልቅ በአገልግሎት ተግባር ላይ ለመሰማራት መጨነቅ ያስፈልጋል።

ወደ ሁለተኛው አመክንዎ ወይም አስተሳሰብ ስንደርስ፣ “ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ አገልግሎት መግባት” የሚለውን እናገኛለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እራሳችንን በሌሎች ሰዎች ውስጥ በማስገባት በአገልግሎት እንድንሰማራ ይፈልገናል። ይህን ማድረግ የምንችለው ታዲያ እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችለው፣ በምናገኛቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ በርኅራሄ ልብ ስንገባ ነው። ረሃብን ለምሳሌ እንውሰድ። ለመሆኑ ዛሬ በርካታ ቤተሰቦች ወይም ሰዎች የሚገኙበትን የረሃብ መከራን በርኅራሄ ልብ እናስብ ይሆን? እኛ በእግዚአብሔር ጸጋ አማካይነት ዕለታዊ ምግባችንን አግኝተናል። ለወር የሚሆን በቂ ምግብ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ እናስብ። ስለዚህ እራሳችንን በርህራሄ ልብ የተሞላን እናድርግ። ርህራሄን የምናሳይላቸው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በርኅራሄው ወደ እኔ፣ ወደ እናንተ፣ ወደ ሁላችን ዘንድ እንደቀረበን ሁሉ፣ ለሰዎች የሚራራ ልብ አለኝን? በአካባቢያችን ለምናገኛቸው ሰዎች የሚራራ ልብ አለን? ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

በመስቀል የተሰቀለውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንመልከት። እርሱ በቆሰለው ታሪካችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ራሱን አስገብቷል። እግዚአብሔር ያደረገልንን ታላቅ ሥራ ማወቅ የምንችልበት መንገድ ይህ ነው። እግዚአብሔር እኛን ከላይ ወደ ታች ለመመልከት በከፈታ ሥፍራ ላይ እንዳልተቀመጠ እናያለን። ነገር ግን  እራሱን ዝቅ አድርጎ እግራችንን ማጠብ ፈለገ። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ፍቅርም ትሁት ነው። ራሱን ከፍ አያደርግም ፣ ነገር ግን እንደ ዝናብ ወደ ምድር ወርዶ ሕይወትን ይሰጣል። ነገር ግን እኛም ኢየሱስ ክርስቶስ የሄደበትን መንገድ መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው? እራሳችንን ከፍ ከማድረግ ይልቅ፣ ከክብራዊ አስተሳሰብ ይልቅ፣ ከዓለማዊ ክብር ይልቅ ወደ ክርስቲያናዊ የአገልግሎት ሕይወት መግባት የምንችለው እንዴት ነው?

ይህን ለማድረግ ወደ ቆራጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ያም በቂ አይደለም። ቆራጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ከባድ ነው ፣ ነገር ግን ይህን እንድናደርግ የሚረዳን ጥንካሬ በውስጣችን ስላለ የማይቻል አይደለም። የእኛን ፍላጎት እና ምኞት ወደ ጎን በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ፍላጎት እንድንከተል የሚያነሳሳን፣ እራሳችንን ለሌሎች አገልግሎት እንድናዘጋጅ የሚገፋፋን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለው የጥምቀት ጥንካሬ ሊኖረን ይገባል። ይህም መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ያቀጣጠለው እና እንክብካቤ የሚያስፈልገው የጸጋ እሳት ነው። በውስጣችን ያለውን የጥምቀት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲያድሰው ዛሬ እንጠይቅ። ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን፣ እርሱ የሄደበትን መንገድ መጓዝ እንድንችል፣ ሌሎችን ማገልገል የምንችልበትን የአልጋይነትን ጸጋ እንዲሰጠን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በጸሎት እንጠይቅ።

ከሴቶች መካከል የተመረጠች ብትሆንም በትህትናዋ ብዛት የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆንን የመረጠች፣ እራሷን ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት ውስጥ በማስገባት፣ በሕይወታችን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናገኝ ወደምትረዳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታችንን እናቀርባለን።” 

 

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥቅምት 7/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

 

02 November 2024, 10:27