የኤርቢል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ከእስላማዊ መንግሥት ግድያ የተረፉትን በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እስላማዊ መንግሥት እያለ ራሱን የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ወደ ሰሜናዊ ኢራቅ በመዝለቅ ሰፊ ግዛቶችን በወረራ መያዙ ሲታወቅ፥ በተለይ ክርስቲያኖችን፣ ያዚዲ ጎሳዎችን፣ ቱርክመን እና ሻባክ ባሉ አናሳ ቡድኖች ላይ የጅምላ መፈናቀልን ማስከተሉ ይታወሳል።
ከተፈናቃዮች አብዛኛዎቹ በሰሜን ምሥራቅ ኢራቅ ወደሚገኘው የኩርድ ክልል የተሰደዱ ሲሆን፥ በአካባቢው የሚገኝ የከለዳውያን ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት መኖሪያ ቤት፣ ምግብ እና የህክምና አገልግሎትን ለመስጠት መሞከሩን የሰበካው ካኅን አባ ካራም ሻህማሻ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሥረታ
እነዚህ የበጎ አድራጎት ተነሳሽነቶች ከጊዜ በኋላ የበለጠ ሌሎች እገዛዎችን እንዲያደርጉ ምክንያት ሆነዋል” በማለት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የተናገሩት አባ ሻህማሻ፥ በኤርቢል የተቋቋመው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (CUE) “በሁከት መካከል የሻማ ብርሃን” ለመሆን ማለሙን አስረድተው፥ ዋና ግቡ በሁሉም ዓይነት የአስተዳደግ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችን በተለይም በቅርብ ጊዜያት በተከሰቱ ሁከቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ለመቀበል እንደ ነበር ገልጸዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 በቦስተን ኮሌጅ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የኤርቢል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (CUE) ቻንስለር እና የአስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሻር ዋርዳ፥ ዩኒቨርሲቲው የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ክፉኛ የተጎዱትን ለማቋቋም መገንባቱን ገልጸው፥ በግዳጅ ለተፈናቀሉት ክርስቲያኖች እና የያዚዲ ቡድኖች ጠንካራ ድምጽ ለመሆን ቆርጦ መነሳቱን አስረድተዋል።
ለያዚዲ ባሕል የሚሰጥ ክብር
አባ ካራም ሻህማሻ የኤርቢል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (CUE) በክልሉ ክርስቲያኖች ላይ የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ባደረሱት ጭካኔያዊ ተግባር የዘር ማጥፋት ጥቃት ለደረሰባቸው የያዚዲ ማኅበረሰብ ተማሪዎች የሚሰጠውን ድጋፍ ገልጸዋል።
አባ ካራም ሻህማሻ ዩኒቨርሲቲው ካቶሊክ እና ካቶሊክ ላልሆኑት ተማሪዎች ለሚያበረክተው በጎ ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በየዓመቱ በርካታ የነጻ ትምህርት ዕድል ለየዚዲ ተማሪዎች መስጠት መቻሉን እና አዲስ ዓመት አከባበር የመሳሰሉ የያዚዲ ባሕልን የሚያከብሩ ዝግጅቶችን እና ለየዚዲ ሕዝቦች መብት ከሚታገሉ ድርጅቶች ጋር እንደሚተባበርም አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ድጋፍ ለሚያስፈልጋት ቤተ ክርስቲያን ዕርዳታን ከሚሰጥ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽ ጋር በመተባበር “በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የነጻ ትምህርት ዕድል” መርሃ ግብር አማካይነት በየዓመቱ ለበርካታ ክርስቲያን ተማሪዎች የትምህርት ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የኤርቢል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የሚገኝበት ደረጃ
ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዛሬ ከ600 በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አባ ሻህማሻ፥ የዩኒቨርሲቲውን አዲስ ተነሳሽነት ሲገልጹ ኮሌጁ የሚሰጠውን ምስራቃዊ የሥነ-ጥበብ ጥናት መርሃ ግብርን አስታውሰዋል።
“መርሃ ግብሩ በክልሉ በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው” ያሉት አባ ሻህማሻ፥ “በሜሶጶጣሚያን አካባቢ ለረጅም ጊዜ በነበሩ ሃይማኖቶች እና ጎሳዎች ላይ የተለያዩ ትምህርቶችን በመስጠት እንደ ኩርዲስታኒ ጥናቶች፣ የካቶሊክ ሥነ-መለኮት እና የኦሪት መጽሐፍት ታሪኮችን እንደሚያካትት አስረድተዋል።
ዓላማው በኢራቅ በሚገኙ የተለያዩ የጎሳ እና የሃይማኖት ቡድኖች መካከል በሰላም አብሮ የመኖር ባሕልን ለማሳደግ እና ለንቁ ማኅበረሰብ ግንባታ አስተዋፅኦ ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።