ፈልግ

የሰሜን አፍሪካ ክልላዊ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት የሰሜን አፍሪካ ክልላዊ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት 

በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነትን ለማስቆም ትህትናን የተላበሰ ድፍረት እንደሚጠይቅ ተገለጸ

በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስን መንበር ጎብኝቶ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው የሰሜን አፍሪካ ክልላዊ የጳጳሳት ጉባኤ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በትኅትና የተሞላ ደፋር ውሳኔን ማድረግ እንደሚገባ አሳሰበ። የጳጳሳቱ ጉባኤ ይህን ያስታወቀው በጉባኤው መዝጊያ ዕለት እሑድ ኅዳር 15/2017 ዓ. ም. ባስተላለፈው መልዕክት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰሜን አፍሪካ ክልላዊ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት በቅድስት አገር እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች በሚጠፋው የሰው ሕይወት እና በሚወድመው ንብረት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የፖለቲካ መሪዎች ትህትናን እንዲላበሱ ጥሪ በማቅረብ በአካባቢው ለሚገኙ ተፋላሚ ወገኖች የጦር መሣሪያን የሚያቀርቡ አገራት ከዲርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በሮም ባካሄዱት ዓመታዊ ስብሰባቸው እና ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ማጠቃለያ ላይ ተማጽኖአቸውን ያቀረቡት የሰሜን አፍሪካ ክልላዊ የጳጳሳት ጉባኤ አባላት የሞሮኮ፣ የአልጄሪያ፣ የቱኒዚያ፣ የሊቢያ እና የምዕራብ ሰሃራ ካቶሊክ ጳጳሳት እንደሆኑ ታውቋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ አነስተኛ የካቶሊክ ማኅበረሰቦች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ጳጳሳቱ ከተወያዩባቸው በርካታ ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆን፥ ጳጳሳቱ በስብሰባቸው መዝጊያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የአገራቱ ቤተ ክርስቲያናት በመጪው የብርሃነ ልደቱ ሰሞን ለአካባቢው ሰላም እና በግጭቱ የተጎዱ ወገኖችን በጋራ ሆነው በጸሎት እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል። 


በቅድስት አገር የጦርነት ሰለባ ለሆኑት ንፁሃን መጨነቅ
የሰሜን አፍሪካ ክልላዊ የጳጳሳት ጉባኤ አባላት በመልዕክታቸው፥ የተራዘመው ጦርነት ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ተቃውመው፥ ጦርነቱ ለቁጥር ለሚታክቱት እንደ ምግብ እና ሕክምና ያሉ አስፈላጊ ነገሮችን በመንፈግ ሞትን፣ ከፍተኛ የንብረት መውደም እና መፈናቀል ማስከተሉን ገልጸዋል።

ይህች ቅድስት አገር ኢየሱስ የተወለደባት፣ ያደገባት፣ የፍትህ እና የሰላም ቃል የተናገረባት፣ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ሁሉ አሳልፎ የሰጠባት እና እንደገና የተነሳባት ምድር እንደሆነች አስታውሰው፥ በአካባቢው ከአንድ ዓመት በላይ የተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ በርካቶች እንዲፈናቀሉ እና ንብረት እንዲወድም ማድረጉን አስታውሰዋል።

በፍልስጤም ግዛት የተካሄደ የሕገ-ወጥ ወረራ ውግዘት
ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው፥ በዌስት ባንክ እየተፈጸመ ያለውን ሕገ-ወጥ ቅኝ ግዛትን እና በፍልስጤም ግዛቶች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በጽኑ ተቃውመው፥ “በፍትህ እና በሰላም ለመኖር ብቻ የሚፈልግ ሕዝብ ንብረት የሆነችውን ፍልስጤምን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ እና ወረራውን ሕጋዊ ለማድረግ በምንም ዓይነት ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም አይቻልም” ብለዋል።

“ሰላምን አሁን እንፈልጋለን!” የሚለው የእስራኤል ፀረ-ወረራ እንቅስቃሴ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንዳመለከተው፥ በዌስት ባንክ በ146 ሠፈሮች እና 224 ምሽጎች ላይ ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን ሕገ-ወጥ የእስራኤል ሠፋሪዎች እንዳሉ ገልጾ፥ በተጨማሪም የሃማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 7/2023 ጥቃት ከፈጸሙ ወዲህ የእስራኤል ሠፋሪዎች በፍልስጤም ንብረቶች እና ይዞታዎች ላይ ያደረሱት ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጿል።

ሕዝቡ እና መንግሥታቸው አንድ አይደሉም
በተመሳሳይም መንግሥታትን እና ሕዝቦቻቸውን መለየት አስፈላጊ እንደሆነ የገለጸው የጳጳሳት መልዕክት፥ የእስራኤል መንግሥት ሁሉንም እስራኤላውያንን እንደማይወክል እና ሃማስ ሁሉንም ፍልስጤማውያን እንደማይወክል ገልጿል።

ለሰላም ድርድር ድፍረትን ማግኘት
ሁሉም ዓይነት ጦርነት፣ ሁከት እና የሽብር ተግባር ተወግደው ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን የማያወላውል ቁርጠኝነት ያረጋገጡት የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት፥ በግጭቱ ውስጥ ለሚሳተፉ ሀገራት መሪዎች የሰላም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። መሪዎቹ ትሕትናን በድፍረት እንዲቀበሉ፣ አንዳቸው የሌላውን መከራ በቅንነት እንዲያዳምጡ፣ ሁሉንም ሰው እንዲያብሩ፣ ጥላቻን ሁሉ እንዲያስወግዱ እና ማንኛውንም ዓይነት የጦርነት ቅስቀሳን፣ የበላይነትን፣ የጥፋትን እና የበቀል መንፈስን እንዲቃወሙ፣ እንዲሁም ሌሎች አገራት የጦር መሣሪያን ከማቅረብ ይልቅ የሰላም ድርድርን እንዲያበረታቱ አሳስበዋል።

የሰሜን አፍሪካ ክልል ጳጳሳት በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የአካባቢው አገራት ምእመናን በመጭው የብርሃነ ልደቱ ወቅት ለሰላም እንዲፀልዩ እና በግጭቱ ለተጎዱ ወገኖች የእርቅና የአብሮነት ሥራዎች እንዲያበረክቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የሰሜን አፍሪካ ጳጳሳት የሮም ጉብኝት
በሮም ቆይታቸው በቅርቡ በሮም በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደውን 16ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ውጤትን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፥ ጉባኤውን ለመምራት ባካሄዱት አዲስ ምርጫ የቱኒዝያ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኒኮላስ ሌኸርኖልን የጉባኤው ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም የአልጀርስ ጳጳስ ካርዲናል ዣን ፖል ቬስኮን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው መርጠዋል።

የሰሜን አፍሪካ አገራት ጳጳሳት በቫቲካን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ በተጨማሪም በሮም ከሚገኙት የሙስሊም ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋርም መገናኘታቸው ታውቋል።

 

27 November 2024, 17:00