ፈልግ

ሱዳናውያን ወደ ቻድ ሲሰደዱ ሱዳናውያን ወደ ቻድ ሲሰደዱ  

ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ የስደተኞችን ችግር እያባባሰ ነው ተባለ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ ወይም ኮፕ29 የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለማስወገድ ከመላው ዓለም የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዘርባጃን አገር ባኩ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህ የኮፕ29 ጉባኤ ላይ ከ198 ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን፥ ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ ኤጀንሲዎች በአዘርባጃን አገር ባኩ ከተማ ከሚካሄደው ኮፕ 29 (COP29) የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ጋር በመተባበር ባወጡት ሪፖርት ጦርነቶችን እና የተለያዩ የሃይማኖት እንዲሁም የፖለቲካ ጥቃቶችን ሸሽተው ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን የሚያገኙት ምንም ማምለጫ በሌለበት እና በአስከፊው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በጣም በተጎዱ አከባቢዎች መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን እና የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ አስቸኳይ ጥረቶችን በሚመለከት በተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አስቸጋሪው የአየር ንብረት ለውጥ ስደተኞች እና የተፈናቀሉ ሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰባቸው እንደሆነ በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ላይ እየተካሄደ ባለው የኮፕ 29 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተሳታፊዎች ሪፖርት ቀርቦላቸዋል።

እነዚህ የአየር ንብረት ለውጦች ስደተኞቹ በተሰደዱባቸው እና ማምለጥ በማይችሉባቸው አካባቢዎች ከሚያስከትሉት አደጋዎች መካከል ከባድ ድርቅ፣ ጎርፍ እና አውሎ ነፋሶች ይገኙበታል ተብሏል።

በግጭት ዞኖች ውስጥ የሚከሰቱ የአየር ንብረት አደጋዎች
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) ለኮፕ 29 ስብሰባ የሚቀርብ በዚህ ርዕሰ ጉዳዩ ላይ ሰፊ ዝርዝር የያዘ ሪፖርት ህዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ማሳተሙ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ሪፖርት የተዘጋጀው በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ባለሙያ ባላቸው 13 ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት እና በስደተኞች ከሚመሩ ቡድኖች ጋር በመተባበር እንደሆነ እና የአየር ንብረት አደጋዎቹ አብዛኛውን ጊዜ የግጭት ቀጠናዎችን እንዴት እንደሚያጠቃ የሚያሳየውን የቅርብ ጊዜውን መረጃ አጉልቶ እንደሚያሳይ ብሎም ቀድሞውኑ አደጋ ላይ ያሉትን ደግሞ እንዴት ወደ ከፋ ሁኔታ እንደሚገፋፋ ያሳያል ተብሏል።

ሪፖርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግዳጅ ከተፈናቀሉት 120 ሚሊዮን ሰዎች ሶስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከሚደርስባቸው ሀገራት ውስጥ እንዴት እንደሚኖሩ በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፥ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሄይቲ፣ ማይናማር፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ሶሪያ ያሉ ሀገራትን ጠቅሷል።

‘ዬትም ማምለጥ አይቻልም’
“ማምለጥ አይቻልም፡ በአየር ንብረት ለውጥ ግንባር ቀደም ጉዳዮች፣ ግጭት እና በግዳጅ መፈናቀል” በሚል ርዕስ የቀረበው ጥናቱ እ.አ.አ. በ 2040 “ከፍተኛ የአየር ንብረት-ተያያዥ አደጋዎች የሚጋፈጡ አገሮች ቁጥር ከ 3 ወደ 65 ከፍ ሊል እንደሚችል ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ ከእነዚህ ሃገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ የተፈናቀሉ ሰዎችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ሃገራት እንደሆኑ፥ በተለይም አማካይ የሙቀት መጠን እየጨመረ ባለባቸው እና የድርቅ ሁኔታዎችን በሚያስከትል ወይም በሚያባብስባቸው ሃገራት እንደሆኑ ይገልፃል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ እንደተናገሩት “በዓለም ላይ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ ህይወታቸውን በእጅጉ የሚጎዳ ከባድ እውነታ መሆኑን ገልጸው፥ “በግጭት እና በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎችን በሚያስተናግዱ ክልሎች ውስጥ ችግራቸውን በማባባስ ምንም ዓይነት መሄጃ ያሳጣቸዋል” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሪፖርቱ በሱዳን የተከሰተውን 'ችላ የተባለ' ግጭት በመጥቀስ፥ ግጭቱ ድርቅ እና ሙቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደደረሰባት ጎረቤት ቻድ የተሰደዱትን 700,000 ሰዎችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሰደዱ ያስገደደ መሆኑን ገልጿል።

ሱዳን ራሷ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከባድ የጎርፍ አደጋ እንደተመታች ያስታወሰው ሪፖርቱ፥ ከዚህም በተጨማሪ የማያንማር ስደተኞች በከባድ አውሎ ነፋሶች እና በጎርፍ እየተጎዳች በምትገኘው ባንግላዲሽ የተሻለ ደህንነትን ፍለጋ እንዴት እንደሚሰደዱ ይገልጻል።

በቁርጠኝነት ከተሰራ መፍትሄዎች ማምጣት ይቻላል
ጦርነትና ብጥብጥ እንዲሰማቸው የተገደዱትን ለመርዳት የሚደረገው ጥረት መጨመር እንዳለበት እና ለከባድ የአየር ንብረት ለውጥ የሚዳርጉ ተግባራት እንዲቀንሱ ተጽዕኖዎችን ማሳደር ይገባል ሲል ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን፥ እነዚህ ሰዎች ከምንም በላይ በጣም የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ ጥበቃ እና ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

“መፍትሄዎቹ በእጃችን ላይ ነው” ያሉት ፊሊፖ ግራንዲ “ነገር ግን አፋጣኝ እርምጃ እንፈልጋለን፥ በቂ ሃብት እና ድጋፍ ከሌለ ተጎጂዎቹ ከባድ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ” በማለት አሳስበዋል።

ከጉባኤው ቁልፍ አጀንዳዎች ውስጥ የአየር ንብረት ፋይናንስ አንዱ ሲሆን፥ የበለፀጉ አገሮች ታዳጊ አገሮችን ለመደገፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ መጨመር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው፣ ጉልህ ሚና ያለው አዲስ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት የፋይናንስ ግብ እንዲቀረፅ ጥሪ አቅርበዋል።

ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጎጂ በመሆናቸው ድጎማ ሊደረግላቸው ይገባል የሚለው ጥያቄ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በተደረጉ ጉባኤዎች ሁሉ ሲነሳ ቆይቷል።

ደሀ ሀገራት በየዓመቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ፕሮጀክት የሚውል 1ትሪሊዮን ዶላር እንዲሰጣቸው ጥሪ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።

ከ198 ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ1ሺ በላይ ሰዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው የባኩ የአየር ንብረት ጉባኤ በቀጣይ ሳምንት ይጠናቀቃል።
 

15 November 2024, 12:34