ፈልግ

የጥቅምት 24/2017 ዓ. ም. ዘጽጌ 5ኛ ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ የጥቅምት 24/2017 ዓ. ም. ዘጽጌ 5ኛ ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ 

የጥቅምት 24/2017 ዓ. ም. ዘጽጌ 5ኛ ዕለተ ሰንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፥

1.    ሮሜ 11: 13-24

2.    ራእ. 12: 13-18

3.    ሐዋ. 11: 1-11

4.    ማቴ 21፡ 33-46

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የወይን ዕርሻ ገበሬዎች ምሳሌ

“ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የወይን ዕርሻ ባለቤት ነበረ፤ በዕርሻው ዙሪያ ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው።

“ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም፣ ‘ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ።

“ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?”

እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን? አላቸው፤

“ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

የማእዘን ራስ  ሆነ፤

እግዚአብሔር ይህን አድርጓል፤

ሥራውም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’

“ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።”

የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወሰዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች።”

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሆይ! እንደምን ሰነበታችሁ።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ የእግዚአብሔር ፍቅና የመፈንሰ ቅዱሰ አድነት ከእናንተ ጋር ይሁን። በየዕለቱ በቃሉ አማካኝነት የሚባርከን የአምላካችን ቅዱስ ስሙ ተመሰገነ ይሁን። ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርአት አቆጣጠር ዘጽጌ 5ኛ የተሰኘውን ስንበት እናከብራለን። እንደ ወትሮው ዛሬም እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ቃሉን ያስተላልፍልናል። የእግዚአብሔር ቃል የምንስማማበት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር የምናሳይበት ነው። በቅዱስ ቃሉ ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት በየቀኑ መታደስ አለበት። በቃሉ ተደግፈን ወደ ንስሐና ወደ ቅዱስ ቁርባን መቅረብ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጸሐፈው መልዕክት አይሁዳውያን ክርስቶስን ባለ መቀበላቸው እንዲሁም ዕድሉን ባለ መጠቀማቸው ይህ ዕድል ፍሬ ለሚያፈሩት መተላለፉን ቅዱስ ጳውሎስ በወይራ ዛፍ ምሳሌ በኩል ይናገረናል።  

እስራኤላዊያን (ያዕቆብ) የእግዚአብሔር ሕዝብ ነበሩ። እግዚአብሔር ለሌሎች በረከት እንዲሆኑ መርጧቸው ነበር። “አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ፤ ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው፣ በዙሪያው ቈፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም ሃረግ ተከለበት፤ በመካከሉም ግንብ ሠራ፤ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ፤ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ (ኢሳ፣5:1) እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት፤ አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ።” (ሆሴ. 11:11) ይላል።  እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ለሌሎች በረከት እንዲሆኑ ነበረ የመረጣቸዉ። ነገር ግን ለነርሱ በተሰጣቸው ልዩ መብት ራሳቸውን ብቸኛ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ አድርገው በመቁጠራቸው ተሰናከሉበት።  እግዚአብሔር ከእነርሱ ፍሬ ጠብቆ ነበረ። ፍሬ እንዲያፈሩ እግዚአብሔር በተለያየ ጊዜ በነቢያት አማካኝነት ቃሉን አስተላልፎላቸው ነበር። ነገር ግን የወይኑን ባለ ቤት ከመስማት ይልቅ አገልጋዮቹን ደበደቡት፣ ገደሉትም።

እግዚአብሔር እስራኤላዊያንን የመረጣቸው በነርሱ በኩል ቃሉ እስራኤል ጎረቤት ላሉት እንደ ለከነአናዊያን፣ ለአሞናዊያን፣ ለኤዶማዊያን፣ ለሞአባዊያን እንዲሰበክ ነበረ።  ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ከእስራኤል ሀገር ውጪ ሊሰበክ አልቻለም። ነቢዩ ዮናስም የአሶር ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ነነዌ እግዚአብሔር በላከ ጊዜ ሃሳቡን ቀይሮ ወደ ሌላ አገር ነበር የሄደው። እግዚአብሔር በእነርሱ አማካኝነት ለሌሎች ቃሉ እንዲደርስ ነበረ ዓላማው። እግዚአብሔር የሁሉም አምላክ መሆኑን አልተረዱም ነበር፤ እግዚአብሔርን የራሳቸው ብቻ አደረጉ። “እኛ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች ነን!” በማለት ራሳቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤ በፊት ሐዋርያትን ለወንጌል አገልግሎት ሲልካቸው በማቴ. ምዕ. 10፡6 ላይ እንዲህ አላቸው፥ “ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደ ሆኑት፣ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ” አላቸው። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. ምዕ. 15፡ 24 ላይ እንዲህ ይላል፥ “እኔ የተላኩት ከእስራኤል ቤት ሆነው ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነዉ” አለ። ምክንያቱም ክርስቶስ የመጣው ለሁሉም ነው። ወንጌል የምስበከው  ለአረማዊያን እና ለአህዛብ ብቻ ሳይሆን ለአይሁዳዊያንም ጭምር ስለሆነ ዛሬም  ሌላ  መስህ ይመጣል ብሎ ለሚጠባበቁት አይሁዳውያን  የትንቢት  ሁሉ  ፍፃሜ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ እንዲጠቃለሉ ቤተ ክርስቲያን ስለነርሱ ትፀልያለች።

ስለዚህ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከዚህ ምንባብ ምን እንማራለን? ምንድነው ለህይወታችን የሚያስተላልፈው። አንደኛው መስፈርት ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነቶች ሊኖረን ይገባል። ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ አማካኝነት እንዲሁም በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት ወደ ልንባችን ይመጣል። ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ ፍሬ የማፍራት ጉዳይ ነው።  ፍሬ የምናፈራው ከርሱ ጋር አንድ ስንሆን ብቻ ነው። ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል ም.15 ላይ መመልከት እንችላለን። "እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ። ቅርንጫፍ ፍሬ ለማፍራት ከወይን ግንድ ጋር አንድ መሆን አለበት"። ስለዚህ እኛ ብቻችን ምንም ማድረግ አንችልም።  ከመቆረጥ ለመዳን የግድ ፍሬ ማፍራት አለብን። ከክርስቶስ ጋር አንድ ስንሆን ብቻ ነው ፍሬ ማፍራት የምንችለው።

በዛሬ በ2ኛው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕዩ በሰማይ በሚካኤልና በዘንዶ መካከል ስለተደረገው ጦርነት ይናገራል። ዘንዶ ተሸንፎ ወደ ምድር ከተጣለ በኋላ ወንድ ልጅ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፍት ቆመ ይላል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሲናገር በራዕይዩ ሴቲቱ ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ወንድ ልጅ ከወለደች በኋላ ልጅዋን ለመዋጥ ሴቲቱን አሳደዳት። እንግዲህ ይህ ዘንዶ የተባለው የመጀመሪያው እባብ የክርስቶስ ተቃዋሚው፣ ክርስቶስ በዚህ በምድር ላይ እንዳይወለድ ብዙ ሙከራ አደረገ። እንዲሁም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሄሮድስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቦታ ለማወቅ 3 የከዋክብት ተመራማሪዎችን ላከ። ምክንያቱም ሄሮድስ ሌላ ንጉሥ ተወልዷል ሲባል በሰማ ጊዜ እጅግ ታወከ፣ ደነገጠ። ማርያምና ዮሴፍ ህፃኑን ኢየሱስን ይዘው  ወደ ግብጽ  ሸሹ። ሄሮደስ ኢየሱስን ለማስገደል ያሰበው ክፉ ሀሳብ ስላልተሳካለት ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ሁሉ እንዲገደሉ አዋጅ አስነገረ። ስለዚህ ወንድሞቼና እህቶቼ ሆይ! ከሰማይ የውደቀው ዘንዶ ሁሉን የሚችለውን እግዚአብሔርን እንዲህ ከተፈታተነ፣ እኛ ስጋ ለባሾች፣ ደካሞች የሆንን እንደማይፈትነን ምን ዋስትና አለን? ስለዚህ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ ምንም ማድረግ አንችልም።  እምነታችንን እና ተስፋችንን በርሱ ላይ እናድርግ።

በ3ኛው ንባብ ቅዱስ ሉቃስ በፃፈው (የሐዋ. 1: 1-11) እንዲህ ይላል። ሐዋርያት ወደ ወንጌል አገልግሎት ከመሄዳቸው በፊት ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ነገር ግን እኔ ስናገር የስማችሁትን አብ የሰጠውን ተስፋ ቃል ጠብቁ አላቸው። ስለዚህ እዚህ ላይ ሐዋርያት ለአገልግሎት ከመሄዳቸው በፊት መጠበቅ ያለባቸው ነገር እዳለ  ያሳሰባቸዋል። “ጠብቁ”  የሚል ትዕዛዝ እና እንዲሁም ደግሞ “ሂድ” የሚል ትዕዛዝ አለ። እኛስ ዛሬ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እናስቀድማለን ወይስ የኛ ነው የሚናስቀድመው? ሐዋርያት ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረድ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የወንጌል አደራ እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ እንዲችሉ ኃይል ሰጣቸው።  በሐዋርያት ላይ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ እነርሱን ምስክሮችና ነቢያት አደረጋቸው። መንፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን ልብ ነው። ቤተ ክርስቲያንን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ነው። ሐዋርያት ወደ ወንጌል አገልግሎት በሚሄዱበት ጊዜ የሚመራቸው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ እውቀት እና ድፍረትን ይሰጣል። የሰማዕታት ምስክርነት የመንፈስ ቅዱስ ውጤት ነው። ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያመጣው ወይም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ነው።የወንጌል አገልግሎት ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም። ወንድሞችና እህቶች ሆይ! መልካም ክርስቲያን ለመሆን በትዕግስታችን መልካም ፍሬ ለማፍራት የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሕይወታችን እናስቀድም። ያለ እግዚአብሔር የምናከናወናቸው ነገሮች ሁሉ ፍሬ አልባ ናቸው። የሰው ጉልበት አላቂ ነው፤ ጊዜያዊ ነው።

በዛሬው የወንጌል ክፍል (በማቴ. 21፡33-43) ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሞቱ እና ስቃዩ አስቀድሞ ያሳወቀበት ነው። ከመግደል የማይመለሱ የወይን እርሻ ገበሬዎች ምሳሌ በመናገር፥አቅጣጫቸውን ስለ ሳቱት ጻፍቶች እና ሽማግሌዎች የተናገረበት ቦታ ነው። በእርግጥም ስለ እርሱ መጥፎ አስተሳሰብ ነበራቸውና ሊያጠፉትም ይፈልጉ ነበር።

በዚህ የወንጌል ክፍል የተነገረው የወይን እርሻ ገበሬዎች ምሳሌ፥ በእርሻው ዙሪያ አጥር አጥሮ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጉድጓድ ቆፍሮ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠርቶ፣ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ስለ ሄደ የወይን እርሻ ባለቤት ነው የሚያወሳው (ማቴ. 21፥33) በመቀጠልም የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። ገበሬዎቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች አገልጋዮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም ልጄን ያከብሩታል በማለት ልጁን ላከ። ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ እርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት (ማቴ. 21፡37-39)።

በዚህም ምሳሌ የወይን እርሻው፥ እግዚአብሔር ስለመረጣቸው እና በእንክብካቤ ስለ ሠራቸው ሰዎችን ያመለክታል። በወይን እርሻው ባለቤት የተላኩት አገልጋዮች ደግሞ በእግዚአብሔር ስለ ተላኩት ነቢያት ነው የሚናገረው፤ የባለቤቱ ልጅ ደግሞ የሚያመለክተው ክርስቶስን ነው። ነብያትም ተቀባይነት እንዳላገኙት ሁሉ ክርስቶስ ደግሞ ተቀባይነትን ካለማግኘትም ባሻገር ተገደለ።

በዚህ ምሳሌ መጨረሻ አካባቢም፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን ለሚመሩት ጥያቄ አቀረበላቸው።ይኸውም “ታድያ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” አላቸው (ማቴ. 21፥40)። እነርሱም እንዲህ በማለት መለሱለት፤ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ እርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት (ማቴ. 21፥41)።

በዚህ ከባድ ምሳሌ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውይይቱ ለነበሩ ሰዎች ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ይችሉ ዘንድ ትምህርትን እንዲያገኙ ነበር ፊት ለፊት የገጠማቸው። ነገር ግን የዚህ ምሳሌ አስተምህሮ በዘመኑ የነበሩ ክርስቶስን ያልተቀበሉት ሰዎችን ብቻ አይደለም የሚመለከተው። ይሁን እንጂ በዘመናችንም እኛንም የሚመለከት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በመሆኑም ዛሬም እግዚአብሔር በወይኑ እርሻ እንዲሠሩ ከተላኩት መልካም ፍሬን ይጠብቃል።

በየትኛውም ዘመን እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲመሩ ሥልጣን የሰጣቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን እቅድ ትተው የራሳቸውን ፍላጎት ሊፈጽሙ ይችላሉ። ነገር ግን የወይን አትክልት እርሻው የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አይደለም። ሥልጣን አገልግሎት ነው፤ ለሁሉም መልካምን በማድረግ የሚተገበር እና ወንጌልን ከቀደመው በተሻለ ሁኔታ ለማሰራጨት የሚጠቅም ነው።

በዛሬው ሥርዓተ ሉጥርጊያ ሁለተኛው ንባብ መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር የወይን አትክልት እርሻም መልካም ሠራተኞች መሆን እንዳለብን ያስተምራል። በመሆኑም በፊሊጵስዮስ መልዕክቱ ምዕራፍ 4፥8 ላይ እንዲህ ይላል፤ “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽንቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ” በማለት ይመክራል።በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያንም በቅድስና የበለጸገች ትሆናለች። በፍጹም ፍቅሩ ለሚደግፈን እግዚአብሔር አብ፣ በመስቀሉ ላዳነን እግዚአብሔር ወልድ እንዲሁም መልካምነትን በሙላት እንድንኖር ልባችንን ለሚከፍትልን መንፈስ ቅዱስ ክብር እና ምስጋና ይሁን።

ወደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተመልሰን በፖምፔ ምልጃን ከሚያቀርቡት አማኞችጋር አንድ ላይ በመሆን እንጸልይ። በዚህ ወርም በመታደስ የመቁጠሪያ ጸሎት እናድርግ።”

 

02 November 2024, 10:14