ፈልግ

ለሐዋሳ ሐዋርያዊ ሰበካ የተሾሙት ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ጎበዛየሁ ጌታቸው ይልማ ለሐዋሳ ሐዋርያዊ ሰበካ የተሾሙት ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ጎበዛየሁ ጌታቸው ይልማ 

በኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለማጠናከር የሀገር በቀል አመራር ወሳኝ መሆኑ ተነገረ

ባለፈው ወር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በኢትዮጵያ ላሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት አምስት አዳዲስ ብጹአን ጳጳሳትን በመሾም ትልቅ እርምጃ ወስደዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ ውስጥ የካቶሊካዊያን ቁጥር አናሳ ቢሆንም ቤተክርስቲያኗ በሃይማኖቶች መካከል ውይይት፣ የሰላም ግንባታ እና ሰብአዊ እርዳታን በማበረታታት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

ቤተክርስቲያኗ በተለያዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች በጋራ ዓላማዎች ላይ በጋራ እንዲሰሩ የጋራ ቦታዎችን በመፍጠር የክርስቲያን ወንድማማችነት የትብብር መድረክ ሆና ቆይታለች።

ባለፉት ወራት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አዲስ ከተሾሙት ዕጩ ጳጳሳት መካከል የሁለቱ ተሿሚዎች ማለትም ስለተለያዩ ሃይማኖቶች በቂ የአካዳሚክ ዕውቀትን ያካበቱት ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ ገብረስላሴ እና የሙስሊም ማህበረሰብ በሚበዛበት ክልል ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ጎበዛየሁ ጌታቸው ይልማ ቤተክርስቲያኒቷ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እና የክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተነሳሽነቶችን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ረዳት ጳጳስ ተደርገው የተሰየሙት ክቡር አባ ተስፋዬ ከዚህም በተጨማሪ የቅድስት መንበር የግብጽ የመንበረ ክሊዮፓትሪስ ተወካይ ተደርገውም ተሹመዋል።

በመሪነት ሚና የረጅም ዓመት ልምድ ያካበቱት ተመራጩ ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የማኅበረ ኮምቦኒ የበላይ አለቃ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ በዚያም የጉባኤውን ዓለም አቀፋዊ የተልእኮ ጥረቶች ይቆጣጠሩ ነበር።

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተመሳሳይ ሁኔታ የተመረጡት ሌላኛው ዕጩ ጳጳስ ክቡር አባ ጎበዛየሁ የሀዋሳ ሐዋሪያዊ ሰበካ ጳጳስ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፥ ዕጩ ጳጳሱ የመቂ ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ጸሐፊ እና የሰባካው ተወካይ በመሆን በማገልገላቸው በአስተዳደርነት እርከን ከፍተኛ ልምድን አካብተዋል።

ለተሻለ ተፅዕኖ የሀገር በቀል አመራር
በቅርቡ ከተሾሙት አምስት ጳጳሳት መካከል ለሀዋሳ እና ለነቀምት ሃገረስብከቶች የተመረጡት ጳጳሳት በእነዚህ አገረ ስብከቶች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሾሙ ኢትዮጵያዊያን ጳጳሳት ሲሆኑ፥ ይህ ወሳኝ ምዕራፍ ቤተክርስቲያን ለሃገር በቀል አመራር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያጎላ እና ይህም በተለይ በፖሊሲ አወጣጥ እና አስተዳደር ላይ ያለውን ተጽእኖ እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ከእርስ በርስ ግጭት ጋር እየታገለች ባለችበት ወቅት ጠንካራ ተደራሽነት እና መመሪያ የሚፈልግበት ወቅት በመሆኑ፥ በቤተክርስቲያኒቱ እየተስፋፋ የመጣው የሃገር በቀል የመሪነት ሚና ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ የተደረገ ነው ተብሏል።

ሰላምን ማበረታታት እና ወጣቶችን ማብቃት
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከዓለም አቀፉ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ጋር በመቀናጀት ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ወጣቶችን በማብቃት ሰላምን በማስፈን ረገድ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ ቤተክርስቲያኗ የሰላም አምባሳደሮችን ለማብዛት የውይይት መድረኮችን በስፋት እያዘጋጀች እንደሆነ ተገልጿል።

የበለጸገ መንፈሳዊ ቅርስ
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ሃገረ ስብከቶቿ ውስጥ ሁለቱንም የግዕዝ እና የላቲን ሥርዓቶችን የምታካሂድ፣ ልዩ የሆነ ሥነ ስርዓትን የምታንፀባርቅ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ አራት የግዕዝ ሥርዓትን የሚከትሉ ሃገረስብከቶችን እና ዘጠኝ የላቲን ሥርዓትን የሚከተሉ ሃዋሪያዊ ሰበካዎችን እንደሚያጠቃልል፥ ይሄም የአገሪቱን መንፈሳዊ ስብጥር ያሳያል ተብሏል።

አዲሶቹ ሹመቶች ይህንን ድርብ ቅርስ የሚያንፀባርቁ ሲሆን፥ ሁለቱ ጳጳሳት የግዕዝ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገረስብከቶች ውስጥ ሲያገለግሉ፥ ሦስቱ ደግሞ የላቲን ሥርዓትን የሚከተሉ ሰበካዎችን ያገለግላሉ።

በእነዚህ አዳዲስ ሹመቶች ቤተክርስቲያኗ በኢትዮጵያ ሰላምን፣ አንድነትን እና መንፈሳዊ እድገትን የማጎልበት ተልእኮዋን እንደምታስፋፋ ተስፋ ተጥሎባታል።
 

22 November 2024, 13:10