በኢንዶኔዥያ የካቶሊክ ወጣቶች ኮሚሽን የ1928ቱን የወጣቶች ቃል ኪዳን በዓል አከበረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በኢንዶኔዥያ የካቶሊክ ወጣቶች ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ አባ ፍራንሲስ ክሪስቲ አዲ ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ ወጣት ካቶሊኮች በታሪካዊው የ1928 የወጣቶች ቃል ኪዳን ላይ የታዩትን የአንድነት መንፈስ እንዲያሳዩ አሳስበው፥ ይህ ደግሞ የተለያየ እምነት ያላቸው እና የተለያየ ባህል ያላቸው ወጣቶች ለኢንዶኔዥያ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚሳይ ተናግረዋል።
ፊልሙ በሚያሳየው ትሩፋት ላይ በማሰላሰል የተናገሩት አባ ፍራንሲስ ክሪስቲ፥ “ኤክሲል” የተሰኘው ፊልሙ የኢንዶኔዥያን ወጣቶች ዘላቂ የሀገር ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኢንዶኔዥያ ወጣቶች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር በጊዜ ርዝመት የማይረሳ መሆኑን አስረድተው፥ የኢንዶኔዥያ ካቶሊክ ወጣቶች ኮሚሽን ወጣቶች ለኢንዶኔዥያ ያላቸውን የጋራ መልካምነትን እንዲያዳብሩ አበረታተዋል።
በዕለቱ ከቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ቀጥሎ በድርያርካራ የፍልስፍና ትምህርት ቤት መምህር እና በብሔራዊ የዘላቂ ልማት ግቦች ጽሕፈት ቤት የባለሙያዎች ቡድን አስተባባሪ በሆኑት ያኑዋር ኑግሮሆ የተመራው ውይይት የኢንዶኔዥያን የወደፊት ውጣ ውረዶች እና ምኞቶች በጥልቀት ተመልክቷል።
ኑግሮሆ በሀገሪቱ ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ላይ በተለይም በኢንዶኔዥያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ መካከለኛ ገቢ ወጥመድ ውስጥ ከገባች በኋላ ያጋጠማትን ኢኮኖሚያዊ መሰናክሎች አጉልተው አሳይተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት እንደ አውሮፓውያኑ በ2045 የበለጸገች ወርቃማ ኢንዶኔዥያን ለማየት የታቀደውን እቅድ ለማሳካት በዕድገት ላይ ያነጣጠረ የትብብር እና የዘላቂ ለውጥ ውጥን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
መምህር ኑግሮሆ በግል ባደረጉት አስተንትኖ ለሕዝብ አገልግሎት ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ወደ ኢንዶኔዢያ የተመለሱበትን ምክንያት ሲያጋሩ፥ ወደ ኢንዶኔዢያ ተመልሰው በኢንዶኔዥያ ለመሥራት መፈለጋቸውን እና የመንግሥት አካል ለመሆን ባያስቡም ኢንዶኔዢያን ማገልገል ይፈልጉ እንደ ነበር አስረድተው፥ በቅዱስ ኢግናቲየስ ሎዮላ መንፈሳዊ ልምምዶች በመነሳሳት ለሕዝብ አገልግሎት መሰጠቱ በመንፈሳዊነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
መምህር ኑግሮሆ የፐብሊክ ሴክተሩ ከቁሳዊ ትስስር የጸዳ ትህትና ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸው፥ አመለካከታችን ነጻ እና ምቹ መሆን እንዳለበት፣ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ሁሉንም መንገዶች መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። ለወጣት የመንግሥት ሠራተኞች ባደረጉት ንግግር፥ ከፍተኛ ጫና በሚፈጥሩ ሚናዎች ላይ የሚደርሰውን ድካም ለመቀነስ የአእምሮ ማገገም እና የድጋፍ መረቦች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ለረዥም ጊዜ ባድማ በመሆን የመከራ እና የሐዘን ስሜት ሰለባዎች መሆን አንችልም!” ያሉት መምህር ኑግሮሆ፥ ያላቸው ጊዜ እጅግ የተገደበ ወይም የሌለ መሆኑን ገልጸው፥ ብዙ ሥራ ቢኖርም ሞራልን እና ግልፅነትን ለማስቀጠል የአጋር ቡድን እና የመንፈሳዊ መሪ ጥቅምን አስረድተዋል።
መምህር ኑግሮሆ በተጨማሪም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2015 እስከ 2019 የኢንዶኔዥያ ፕሬዝደንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን የተከተሉትን የራሳቸውን የአመራር ስልት በመጥቀስ ወጣት የመንግሥት ሠራተኞች የቡድን ሥራን እና እኩልነትን እንዲያበረታቱ አሳስበዋል።
በአንድ ድርጅት ውስጥ የሥራ ሂደት እንዲቀል፣ የበለጠ ውጤታማ እና ግልጽ እንዲሆን ከተፈለገ የቡድን አባላት አንዳቸው የሌላውን ችሎታ በሚገባ ማወቅ እንዳለባቸው አሳስበው፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች ለመምህር ኑግሮሆ በርካታ ጥያቄዎችን በማቅረብ እና በተሳታፊዎች መካከል የልምድ ልውውጦችን በማድረግ ውይይቱ ተጠናቋል።