በሲንጋፖር መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ የነበሩ ካህን በስለት ተወጉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሲንጋፖር አፐር ቡኪት ቲማህ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህን ዘወትር ቅዳሜ ምሽት የሚደረገውን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ በነበረበት ወቅት በአንድ ግለሰብ የስለት ጥቃት የደረሰባቸው ቢሆንም በህይወት ለመትረፍ ችለዋል።
የ57 ዓመቱ አባ ክሪስቶፈር ሊ በስለት የተወጉት ለምዕመናኑ ቅዱስ ቁርባን በመስጠት ላይ በነበሩበት ወቅት ሲሆን፥ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ካህኑ ላይ ጥቃት ያደረሰው የ37 ዓመቱ የሲንጋፖር ተወላጅ የሆነው ሰው በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተዘግቧል።
የሲንጋፖር ፖሊስ እንደገለጸው ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ በፖሊስ አባላት ከመያዙ በፊት በስፍራው የነበሩ የጉባኤው አባላት የስለት መሳሪያውን ቀምተውት የነበረ ሲሆን፥ የሲንጋፖር ፖሊስ በመግለጫው ላይ አክሎ እንዳሳወቀው አጥቂው ከዚህን በፊት ከፍተኛ አደንዛዥ እጽ አላግባብ ይጠቀም እንደነበር እና በዚህም ከባድ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር በመግለጽ፥ ‘በተደረገው ቅድመ ምርመራ መሰረት ግለሰቡ ወንጀሉን የፈፀመው ብቻውን ነው ተብሎ የሚታመን ሲሆን፥ ፖሊስ ይሄንን ድርጊት የሽብር ተግባር ነው ብሎ እንደማይጠረጥር’ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ መግለጫው ‘ከዚህ ክስተት በስተጀርባ ያለውን ምክንያት ለማጣራት ምርመራ በመካሄድ ላይ በመሆኑ ህዝቡ ተረጋግቶ እንዲጠብቅ እና ከመላምት እንዲቆጠብ’ ፖሊስ አሳስቧል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና መንግስት ጥቃቱን አውግዘዋል
በሲንጋፖር የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ዊልያም ጎህ ጥቃቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ‘ተወዳጅ ከሆኑ ካህናት መሃል አንዱ ላይ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ ላይ በነበሩበት ወቅት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሲሰሙ በጣም እንደደነገጡ እና እጅግ እንዳዘኑ’ ገልጸዋል።
ብጹእነታቸው አክለውም ‘ይህ ክስተት በልጆቻችን እና ይህ ጥቃት ሲፈፀም ያዩ ሁሉ ላይ ስላሳደረው የስነ-ልቦና ተጽእኖ በጣም እንዳሳሰባቸው’ ገልጸው፥ ‘ምዕመናን ጉዳዩ እስከሚጣራ እና እውነቱ እስከሚወጣ መላ ምቶችን ከመገመት እና ፍርድ ከመስጠት እንዲቆጠቡ እና እንዲረጋጉ’ በማሳሰብ፥ “የአከባቢው ባለሥልጣናት ጉዳዩን በጥልቀት እንዲመረምሩ መፍቀድ አለብን” ሲሉ ብጹእ ካርዲናል ጎህ መክረዋል።
የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ በተመሳሳይ ሁኔታ ምዕመናን ከዚህ “አሰቃቂ ክስተት” ቶሎ እንደሚያገግሙ ያላቸውን ተስፋ ገልፀው፥ “ሲንጋፖር ውስጥ ለሁከት የሚሆን ቦታ የለም” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
የአምልኮ ቦታዎች ደህንነት እና ቅድስና መጠበቅ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዎንግ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባወጡት መልዕክት አክለውም እንደገለጹት ‘ከሁሉም በላይ ሰዎች ሰላምን፣ መፅናናትን እና ማህበራዊ ህይወትን ለማግኘት የሚሹባቸውን የአምልኮ ቦታዎቻችንን ደህንነት እና ቅድስና መጠበቅ አለብን’ ሲሉ ጽፈዋል።
“በመረጋጋት እና በአንድነት መቆም አለብን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “እኛን እንደ ሲንጋፖርውያን የሚገልጸን በስምምነት እና በጽናት መንፈስ እርስ በርሳችን መደጋገፍ አለብን” በማለትም መክረዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የሀገሪቱ የባህል፣ የማህበረሰብ እና የወጣቶች ሚኒስትር ኤድዊን ቶንግ ጥቃቱን በማውገዝ ለአባ ሊ መጸለያቸው ተነግሯል።