ፈልግ

እማሆይ ሐረገወይን ከብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ቡራኬ እና እውቅና ውስደው በሆለታ ገዳም መሥርተዋል እማሆይ ሐረገወይን ከብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ቡራኬ እና እውቅና ውስደው በሆለታ ገዳም መሥርተዋል 

እማሆይ ሐረገወይን በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ቅድስት ስላሴ የሴቶች ገዳም መሠረቱ

ካቶሊክ ካልሆኑ ቤተሰብ የተወለዱት እማሆይ ሐረገወይን ሰፋ ባለ ዕይታ እና በአገር ውስጥ ቋንቋ ለመጸለይ ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ጥሪያቸው ከግል የገዳም ሕይወት በላይ መሆኑን አምነዋል። እማሆይ ሐረገወይን አገልግሎታቸው በአካባቢው ወጎች ብቻ ሳይገደብ ድሆችን እና ችግረኞችን እንዲያገለግሉ የቀረበላትን ጥሪ ተቀብላ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያ ያደረጋትን የሴቶች ገዳም መሥርታለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ኢትዮጵያዊት ካቶሊካዊ መነኩሴ መሆን እፈልጋለሁ!” በማለት በድፍረት የተናገሩት እና በኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ የሆኑት እማሆይ ሐረገወይን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን የቅድስት ሥላሴ አቡነ ብሩክ ገዳምን መሥርተዋል።

ገዳማውያቱ “እማሆይ” የሚል ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን ይህ ማዕረግ “ሁሉም ሴቶች እናቶች ናቸው” የሚለውን እምነት የሚያንፀባርቅ እና ከገዳሙ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ወላጅ እናቶች እንደሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ገዳናውያት እህቶች በመሆን ለሁሉም ሰው መንፈሳዊ እናት ለመሆን ሕይወታቸውን የሰጡ ናቸው።

ከሥርዓተ አምልኮ ፍቅር ጋር ወደ ምንኩስና ሕይወት መሪነት
አዲስ አበባ የተወለዱት እማሆይ ሐረገወይን በሊሴ ገብረማርያም የፈረንሳይ ትምህርት ቤት ገብተው ከልዩ ልዩ ባሕሎች እና ቋንቋዎች ጋር የተላመዱ ሲሆንበ16 ዓመት ዕድሜአቸው ከአንዲት ካቶሊካዊ ጓደኛቸዋ ጋር ወደ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ካቶሊክ ቁምስና በመሄድ የመጀመሪያቸው የሆነውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከተካፈሉ በኋላ በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ስለተማረኩ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመገናኘት ያላቸው ፍላጎት ይበልጥ አድጓል።

የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ቢሆኑም ወደ ካቶሊካዊነት ይሳቡ ነበር። የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን በማዘውተር በኋላም ገዳማዊ እህት ለመሆን ያላቸው ፍላጎት ጨመረ። የቅዱስ ፍራንችስኮስን መንፈሳዊ ምስል ከተመለከቱ በኋላ እምነታቸው እየጠነከረ በመሄዱ ለጥሪያቸው ያላቸው ቁርጠኝነትም አድጓል።

እማሆይ ሐረገወይን በጸሎት እና በመንፈሳዊ ምክሮች እየተመሩ ፈተናዎችን አሸንፈው የኢየሱስ ታናናሽ እህቶች ማኅበር የተባለውን እና በቅዱስ ቻርለስ ደ ፉውኩ የተመሠረተውን የገዳማውያት ማኅበር ተቀላቀሉ። ለመንፈሳዊ ጥያቄዎቻቸው መልስ እየፈለጉ ስለነበር በናይጄሪያ፣ በኬንያ፣ በግብፅ፣ በፈረንሳይ እና በጣሊያን እንዲሁም ወደ ሌሎች የተለያዩ ሀገራት በመሄድ መንፈስዊ ትምህርቶችን ቀስመዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2007 በኢትዮጵያ ገዳማዊ ትውፊት ላይ በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ በመገኘት ሲፈልጉት የነበረውን መልስ እንዳገኙት ተሰማቸው። ይህ ቅጽበት የኢትዮጵያን ልዩ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ማንነት የሚያንፀባርቅ የካቶሊክ ገዳም የመመሥረት ተልዕኮአቸው የጀመረበት ወቅት ነበር።

እማሆይ ሐረገወይን
እማሆይ ሐረገወይን

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያውን የቅዱስ ብሩክ ካቶሊካዊ የሴቶች ገዳም መሠረቱ። በዚህም ገዳሙን ለመመሥረት የነበራቸው የረጅም ጊዜ ህልማቸው ተሳካ። በፈረንሣይ አገር ቆይታቸው በቅዱስ ብሩክ ገዳማዊ እህቶች ድጋፍ በትርፍ ጊዜያቸው የእጅ ሥራ ውጤቶችን ሽጠው ባገኙት ገንዘብ አዲስ አበባ ውስጥ አነስተኛ ቤት ገዙ።

በኋላም በፈረንሳይ በሚገኙ ገዳማዊ አህቶች ድጋፍ ከአዲስ አበባ በ40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኝ ሆለታ ውስጥ መሬት ተሰጣቸው። ቀጥሎም የአዲስ አበባ ሊቀ ጳጳስ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ከሆኑት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ቡራኬ እና እውቅና ተቀብለው ገዳም የማቋቋም ዕድል ተሰጣቸው። አዲሱን የገዳም ልብስ ለብሰው በአገር ቋንቋ ጸሎት ሲያቀርቡ በገዳም ሕይወት ጉዞ ውስጥ ለነበራቸው ክፍተቶች መልስ እንዳገኙ ተሰማቸው።

በሆለታ የሚገኝ የቅድስት ሥላሴ ገዳም
በሆለታ የሚገኝ የቅድስት ሥላሴ ገዳም

ከግብርና ሥራ ተነሳሽነት ጋር የተጣጣመ ተልዕኮ

እማሆይ ሐረገወይን እምነትን ከአካባቢው ባህል ጋር በማዋሃድ ገዳማቸው እራሱን እንዲችል ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ጀመሩ። ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ እንደ ዶሮ እና እንቁላል እንዲሁም የከብት እርባታ የመሳሰሉ የግብርና ሥራዎችን መሥራት ጀመሩ።

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአካባቢ እንክብካቤ ጥሪ በመነሳሳት በተፈጥሮ የእርሻ ዘዴ ለገዳሙም ሆነ ለማኅበረሰቡ የሚጠቅሙ ሥነ-ምህዳራዊ የግብርና አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ዕይታቸው ከገዳም ሕይወት ባሻገር የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚያገናኝ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት መርሃ ግብር ጀመሩ። እማሆይ ሐረገወይን በትምህርት ቤት አገልግሎታቸው እና በእርሻ ሥራቸው ከመንደሩ ነዋሪዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት መሠረቱ። በቤተሰብ ዕድገት እና በልማዳዊ የምግብ ዝግጅት ላይ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ።

ይህን እቅድ ወደ ፊት ለአካባቢው ነዋሪዎች ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት እንደሚያስችል እንደ መለኮታዊ ዕድል ይመለከቱታል። ለአካባቢው በራስ የመተማመን አስፈላጊነትን በማጉላት ማኅበረሰቦች በውጭ ድጋፍ ላይ ብቻ ከመተማመን ይልቅ እራሳቸውን ችለው የአርብቶ አደር ሥራዎችን እንዲያውቁ በማበረታታት ላይ ይገኛሉ።

የመዋዕለ ሕፃናት ት/ቤት የመጀመሪያ ተመራቂዎች
የመዋዕለ ሕፃናት ት/ቤት የመጀመሪያ ተመራቂዎች

የምንኩስና ሕይወት እና ወደ ቅድስና ጥሪ
እማሆይ ሐረገወይን ገዳሙን ሰላማዊ እና ቅዱስ ሥፍራ በማድረግ ምዕመናን ከገዳማውያቱ ጋር በጸሎት እና በሱባኤ እንዲገናኙ በማድረግ እንዲሁም በሚገባቸው የአከባቢው ቋንቋ መመካከር እንዲችሉ ለማድረግ አልመዋል። እምነት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ አብረው የሚያብቡበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርስ ጥልቅ ግንኙነት የሚፈጥሩበትን ቦታ ለማመቻቸት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ባለትዳሮች ልጅ እንዲወልዱ እና በጸሎት የሚተጉ ቤተሰቦችን እያበረታቱ በሌላ በኩል ደግሞ ጥሪያቸውን በሚገባ ያወቁትም ጊዜያቸው በጸሎት እንዲያሳልፉ በመርዳት እግዚአብሔር የሚያሳያቸው መንገድ የቱ እንደሆነ በሚገባ እንዲያውቁ በማበረታታት ላይ ይገኛሉ።

በብዙሃን መገናኛ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት በኩልም የገዳሙን ድረ-ገጽ በመዘርጋት የመንፈሳዊ ጥሪ መልዕክቶችን ለማሰራጨት ተስፋ አድርገዋል። እማሆይ ሐረገወይን ቅድስና ማለት በምንኩስና ሕይወት ብቻ የተገደበ ሳይሆን ለሁሉ ሰው የቀረበ ጥሪ መሆኑን በመግለጽ ቤተ ክርስቲያን ጸንታ የምትኖረው ምዕመናን ለኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው ፍቅር መስዋዕትን ለመክፈል ዝግጁዎች ሲሆኑ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።


 

05 November 2024, 17:08