ፈልግ

ኢየሱስ በክፉ መንፈስ የተያዘውን ሰው ፈወሰ ኢየሱስ በክፉ መንፈስ የተያዘውን ሰው ፈወሰ 

የኅዳር 15/2015 ዓ.ም ዘአስተምህሮ 2ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ቆላ.1:12-29

2.     1ጴጥ.1:13-20

3.     ሐዋ.19:21-40

4.     ዮሐ.5:16-27

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።  ኢየሱስ ግን አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።  እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። 

ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።  አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። 

ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።  የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

በቤተክርስትያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት የዛሬው ሰንበት ዘአስተምሕሮ 2ኛ በመባል ይታወቃል።በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባቦች አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።

የዛሬው ወንጌል ክርስቶስ ከአይሁዳውያን ጋር ያደረገውን ንግግር በመተረክ ስለ እግዚአብሔር ቀጣይ ምሕረት እንድናስተነትን ይጋብዘናል። ኢየሱስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ የታመመን አንድ ሰው በዓይናቸው ፊት ከፈወሰ በኋላ አይሁዳውያን ኢየሱስን ያሳድዱት ጀመር። ኢየሱስ ግን "አባቴ ሁልጊዜ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ" ሲል መለሰላቸው (5:17) ። ይህንን የኢየሱስ መልስ በሰሙ ጊዜ አይሁዳውያን ኢየሱስን ይገድሉ ዘንድ ይበልጥ ተነሣሡ። ምክንያቱም ይላል ወንጌል ሰንበትን በመሻሩ ብቻ ሳይሆን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" በማለቱ ነበር።

ሰው ለምን በእግዚአብሔር መልካም ሥራ አይደሰትም ብለን ብንጠይቅ ብዙ ምላሽ ይኖር ይሆናል፤ ግን ሰው የራሱ ሥራ ክፉ በሆነና እግዚአብሔርን እንደሚያሳዝን ባወቀ መጠን ሆኖም ግን ወደ ቀና መንገድ መዞር መምረጥን ካልፈለገ እግዚአብሔር ለሌሎች ሰዎች በሚያደርግላቸው መልካም ነገር ሁሉ ያዝናል። የሌሎቹ መልካምነት የርሱን ጎዶሎነት ያስታውሰዋልና መልካም ነገሮችን በይፋ መቃወም ይጀምራል። አባት፣ አባባ ብለን እንጠራው ዘንድ የተሰጠንን ጸጋ በመርሳት እግዚአብሔርን አባት ያለማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አባት መሆኑን እንቃወማለን። አይሁዳውያን ከነበራቸው የሃይማኖታቸው ግንዛቤ ባሻገር የመመጻደቅ ድርጊቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሥራ እንዳያዩ ጋርዷቸው ነበር።

የኛን ውስጣዊ የእግዚአብሔር ስዕል በመጠኑ እንይ። ክርስቶስ "አባታችን ሆይ!" ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ሲያዘንና "የሰማይ አባታችሁ" ብሎ ሲያስተምረን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" የሚለውን እወጃ ለኛም ሰጥቶናል። ክርስቶስ ከአባቱ ጋር ያለው ብቸኛ የልጅነት ደረጃን ባይሆንም የጸጋ ልጅነት ተሰጥቶናል፤ ታዲያ አፋችንን ሞልተን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ማለት እንችል ይሆን?

ይህን ማለት መቻል በሌላ አባባል እኔ የእግዚአብሔር ነኝ የሚል መልእክት ማስተላለፍ ማለት ነው። ዛሬ ዛሬ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ማለት በማኅበረሰባችን ውስጥ ብዙ ቅጽል ነገሮችን የሚያሰጥ ስለሆነ የዘመናዊነት ክፍል መሆን እፈልጋለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው የእግዚአብሔርን አባትነት በይፋ ሕይወቱ ማወጅ ብዙም አይዋጥለትም። ይህ አካሄድ ግን ድምዳሜው ላይ ሲደርስ መዘዙ ዘላለማዊንትን በዘመናዊነት መቀየር ይሆናል። ይህ በሕይወቴ ይታያል ወይ በማለት እናስተንትን።

እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለት ትልቅ ምስጢር ውስጥ ራስን ማስገባት ማለት ነው። ክርስቶስ ወንድሜ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም እናቴ፣ መላእክቶች ጠባቂዬ፣ ቅዱሳኖች አማላጆቼ ማለት ነው። የእሱን አባትነት ተቀብሎ ሌሎቹን ማስወገድ ያስቸግራል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ስፋት እኛ ከምንገምተው በላይ እርስ በርስ የተሳሰሩና ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚለው እጅና እግር አንዱ ለአንዱ እንደሚረዳ እንዲሁ የተጠማመረ ኅብረት ያለው ነው። እስቲ ይህን ምስጢር እናስበው፤ ደካማነታችን ዓይናችንን ጋርዶን ራሳችንን ብቻ በሚያሳየን ሰዓት የእንደዚህ ዓይነት ትልቅ ቤተሰብ አባል መሆናችን ትልቅ ጸጋ መሆኑን እናስታውስ። ተፈጥረን በዚች ፕላኔት ተውጠን እንድንቀር አይደለም የእግዚአብሔር ፈቃድ። የዚች ዓለም ውስንነት መልእክት ሁልጊዜ ከዚህም በላይ ሕይወት አለ የሚል ነው። የእርሱ ልጅ መሆናችን ገድበው ከያዙን ነገሮች ላቅ ያለ ዓላማና ውሳኔ እንዲኖረን ይጋብዘናል።

ጠንካራ የሚመስለው ሰው ሲወድቅ፣ ሀብታሙ ሀብቱን ትቶ ከምድር ሲሰናበት፤ ነገሮች ሁሉ ቁርጥራጭ ሆነው ሲታዩን ማንነታችንን ወደ ሕያው ከፍታ የሚያነሳው ብቸኛ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ መሆናቸን ነው። ይህ ባይሆን በርግጥ ምድር ከመልስ ይልቅ ጥያቄን የምታበዛ መቆያ ቦታ ብቻ ሆና ተስፋ ባሳጣችን ነበር። ነገር ግን ይህች ዓለም እናተርፍባት ዘንድ ተሰጥታናለች፤ ከርሷ የበለጠውን እናገኝ ዘንድ ወደርሷ መጥተናል እንጂ እርሷን አግኝንተን ከርስዋ የበለጠውን እንድናጣ አይደለም። ክርስቶስ "ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል" (ማቴ.16:26) እንዳለው ነው። "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ማለት የዚችን ምድር ነገር ለቀቅ ለቀቅ ማድረግ ማለት ነው። ቅዱስ አውጎስጢኖስ ዕድሜያችን ዘላለማዊነትን እናገኝበት ዘንድ ተሰጥቶናል እንጂ ምድራዊውን ኑሮ ብቻ እንኖር ዘንድ አይደለም፤ ለምድራዊ ኑሮ ብቻ የተፈጠርን ከሆንንማ ይህች ዕድሜያችን በጣም አጭር ናት ይላል።

ውሏችንን ስንጀምር "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ብለን እንውጣ፣ ስንውልም ሆነ ውሏችንን ስንደመድም "እግዚአብሔር አባቴ ነው" ብለን እናስብ። ምናልባትም ይህን በምናነብበት ሰዓት ራሱ አቋርጠን "እግዚአብሔር አባቴ ነው" እንበል......። ማን ያውቃል ይህን ማለት የሚከብደን ሁኔታ ውስጥ ልንሆን እንችላለን፤ እግዚአብሔር ግን ከሁኔታዎች በላይ ነውና አባትነቱ አይቀየርም። ስለዚህ ውስጣችን ቢዝል፣ ተስፋ ማድረግ ቢሳነን፣ ከኃጢአታችን ጋር ያለን ቁርኝት የበረታብን ቢመስለን፣ የኑሯችን ደባል ራሱ ብቸኝነት ሆኖ በሚሰማን ሰዓት.....ሁሉ ኢየሱስ ሊያጠምዱት በሚያሳድዱት ፊት የሰጠው መልስ በአንደበታችን ይሁን:- "እግዚአብሔር አባቴ ነው"።

ኢየሱስ ለአይሁዳውያን ሲመልስላቸው "አባቴ ሁልጊዜ ይሠራል" አላቸው። ይሄኮ ለሰው ሁሉ መልካም ብስራት መሆን የሚገባው ነገር ነው። ከመደሰት ይልቅ ሁሌ ይሠራል ስላላቸው ያሳድዱት ጀመር። እግዚአብሔር የማይሠራበት ጊዜ ቢኖር ምን ይውጠን ነበር። ኢየሱስን አይሁዳውያን ሰንበት ነውና ምንም አትሥራ ሲሉት፤ እሱ ግን "ሁልጊዜ" መሥራት እንዳለበት ያውቃልና እንደ አምላክነቱ ለሰው ልጅ በጎን ከማድረግ ምንም እንደማይገታው አስረዳቸው።

አንዳንዴ የሰው ልጅ እግዚአብሔር እንዳይሠራ የሚፈልግበት ጊዜ ሊኖር ይችላል ብለን ካሰብን ክፉን ስናደርግ ወይም ማድረግ ስንፈልግ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ግን እሱ ሁሌም ይሠራል። ክፋትን ስናደርግም ቢሆን እሱ ይሠራል፦ የእሱ ሥራ ምሕረት ነው። በምንፈልገውም በማንፈልገውም ጊዜና ቦታ፣ የዕድሜ ደረጃና የአናኗር ዘይቤያችን ሁሉ እሱ ሁልጊዜ ይሠራል፣ ሁልጊዜ ይቅር ይላል። ቤኔዲክቶስ 16ኛው "እግዚአብሔር ሲገባበት በረሃው ለምለም ይሆናል" እንዳሉት የደረቀና የጠወለገ መንፈሳዊነታችንን እሱ እንዲያለመልምልንና የእርሱ ልጅ የመሆናችንን ክብር ዳግም እንጎናጸፍ ዘንድ ከርሱ ሰፊ ቤተሰብ ጋር የቃሉና የማዕዱ ተካፋይ እንሁን፤ ሁልጊዜ የሚሠራ አባት ሊሆነን ስለፈቀደም የተመሰገነ ይሁን። ይህንን ለመፈፀም እንዲያስችለን የታዛዥነት ተምሳሌት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ይህንን ጸጋና በረከት ከልጇ ታማልደን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

 

 

 

23 November 2024, 10:27