ፈልግ

በስፔን በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ200 በላይ ሰዎች ሞተዋል በስፔን በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ200 በላይ ሰዎች ሞተዋል  (ANSA)

የቫሌንሽያ ሊቀ ጳጳስ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት በጎርፍ አደጋ የተጎዱትን ሰዎች እያስተናገዱ ነው አሉ

የቫሌንሽያ ሊቀ ጳጳስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በመላው ስፔን ከ 200 በላይ ሰዎችን የቀጠፈውን አሰቃቂውን የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በማስመልከት የሃገረ ስብከቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት የተቸገሩትን ሁሉ በደስታ እንዲቀበሉና እንዲረዷቸው ብሎም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት በምስራቃዊዋ ቫሌንሽያ ግዛት እና አካባቢው የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ድልድዮች የወደሙ ሲሆን፣ ከተሞች በጭቃ በመሸፈናቸው ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መብራት እና የሚመገቡት መቸገራቸው እንድዲሁም ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ደብዛቸው መጥፋቱ ተገልጿል።

በስፔን በ 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ተከስቶ የማይታወቅ እጅግ አስከፊ በሆነው ሞቃታማ አውሎ ነፋስ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፥ በቫሌንሽያ ብቻ ከመቶ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ፖሊስ ገልፆ፣ በአጠቃላይ በስፔን ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸው፣ ከዚህም በተጨማሪ በደርዘን የሚቆጠሩ የጠፉ ሰዎችን ፍለጋ እና የማዳን ስራ መቀጠሉ ተነግሯል።

በዚያች አገር ታሪክ በገዳይነቱ ከሁሉ የከፋው መሆኑ የተነገረለት የተፈጥሮ አደጋ ያስከተለው የውሃ ናዳ ከከመረው ጭቃ እና ፍርስራሽ የሚወጡት አሳዛኝ ዜናዎች አሁንም አላበቁም።

በሕይወት የተረፉ ካሉ በሚል ፍለጋው በቀጠለበት በዚህ ሰዓት የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል ተብሎም ተሰግቷል።

በስፔን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለዓመታት ታይቶ የማይታወቅ እጅግ አስከፊ በተባለው የጎርፍ አደጋ የጠፉ በርካታ ሰዎችን ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። እስካሁንም በጎርፍ አደጋው ከ200 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሞቱት በቫሌንሲያ ግዛት ነው ተብሏል።

ይህ በስፔን ምስራቃዊ ክፍል የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ በስፔን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ከታዩት እጅግ የከፋ የተፈጥሮ አደጋዎች አንዱ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በጣም ከተጎዱት ክልሎች ውስጥ የቫሌንሲያ ክልል ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘ እና በአንድ ዓመት ውስጥ ይዘንብ የነበረ ዝናብ በ8 ሰዓታት ብቻ እንደዘነበ ተገልጿል። በመኸር ወቅት ዝናብ የተለመደ ቢሆንም፣ በድንገት የጣለው ከባድ ዝናብ ግን በርካታ ውድመትን ማድረሱ ተነግሯል።

ከሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ከባርሴሎና በስተደቡብ በሚገኘው ቫሌንሲያ በደርዘን ከሚቆጠሩ መንደሮች እና የመኖሪያ አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች አንዳቸው በሌላው ላይ ተነባብረው፣ ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች እና የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ወዳድቀው፤ እንዲሁም የቤት እቃዎች ተከምረው ይታያሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በስፔን የቫላዶሊድ ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት ብጹእ አቡነ ሉዊስ ጃቪየር (አርጉዌሎ ጋርሺያ) በላኩት የቪዲዮ መልዕክት በአደጋው ለተጎዱት ሁሉ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

አደጋው የተከሰተው በስፔን ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ገለልተኛ እና አነስተኛ ግፊት ያለው የአየር ንብረት ስርዓትን ለሚገልጸው እና በምህፃረ ቃል “ዳና” ("DANA"-’Depresión Aislada en Niveles Altos’) በመባል በሚታወቀው፣ በጣም አልፎ አልፎ ብቻ በሚከሰተው የአውሎ ነፋስ ስርዓት አማካይነት እንደሆነ መረጃዎች እያሳዩ ይገኛሉ።

ይህ ያልተለመደ ክስተት በዋነኛነት በቫሌንሽያ ክልል ላይ ከባድ አደጋ ያደረሰ ሲሆን፥ የቫለንሽያ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ኤንሪኬ ቤናቬንት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “የአደጋው መጠን እና በፍጥነት የተከሰቱት ሁኔታዎች ለሁላችንም በእውነት አስደንጋጭ ተሞክሮ ነበር” ብለዋል።

ብጹእነታቸው በማከልም “በእርግጥም ማክሰኞ ምሽት ወደ ማረፊያ ቤታችን ስንሄድ ዋናው ‘ዳና’ እንደነበር አውቀን ነበር፥ ነገርግን የአደጋውን መጠን ይሄን ያክል ይሆናል ብለን አላሰብንም ነበር” ብለዋል።

ባለሥልጣናት ሰዎች ጉዳት የደረሰበት አካባቢ እንዳይሄዱ መክረዋል
ሊቀ ጳጳስ ቤናቬንት የጠፉትን ለመፈለግ እና የተጎዱትን ለመርዳት ቅድሚያ ስለሚሰጥ እስካሁን ድረስ በአደጋው ወደ ተጎዳው አካባቢ መድረስ አለመቻላቸውን አስረድተው፥ ነገር ግን በተቻለ ፍጥነት በአካባቢው የሚገኙትን አድባራትና ካህናትን እንደሚጎበኙ ያስታወቁ ሲሆን፥ ወደ አከባቢው ለመሄድ የባለስልጣናትን መመሪያ ጠይቀው እንደነበር፥ ሆኖም ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ በጥብቅ እንደመከሯቸው ገልጸዋል።

በአደጋው ምክንያት የፈራረሱ ድልድዮች ስላሉ እና የተጎዱ አካባቢዎችን መድረስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያትይ በጣም አስቸጋሪ እና ውስብስብ ስለሆነ ነዋሪዎቹ “በፍፁም ተስፋ ቆርጠዋል” ያሉት ብጹእነታቸው፥ የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ ስለሚያስችል እና ሁሉም ሥራውን በአግባቡ እንዲሰራ ስለሚያግዝ የባለሥልጣናት መመሪያዎችን መከተል አለብኝ ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ከቫቲካን ዜና ጋር ጥቅምት 20 ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት የስልክ መስመሮች ይቆራረጡ ስለነበር ለመግባባት አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበር ገልጸው “ምንም እንኳን የስልክ መስመሮቹ ትላንት ቀን ላይ በጥሩ ሁኔታ ባይሰሩም፣ ማታ ሁሉም ካህናት ደህና መሆናቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ፥ ይህም የተወሰነ የአእምሮ ሰላም ሰጥቶኛል” ብለዋል።

የቫሌንሲያው ሊቀ ጳጳስ በሰበካው የሚገኙ ተቋማትን ለጊዜያዊ መጠለያነት አቅርበዋል
የአደጋው መጠን አሁንም እየተገመገመ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ትክክለኛውን የሟቾች ቁጥር በእርግጠኝነት ለማወቅ አልተቻለም። ነገር ግን አደጋው በተከሰተባቸው ከተሞች በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች የስፔን መከላከያ እና የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች በሕይወት የተረፉትን በማፈላለግ እንዲሁም አደጋው ያደረሰውን ውድመት በማጽዳት ዘመቻ እየረዱ ሲሆን፥ የቫሌንሽያ ክልል ፕሬዝዳንት ካርሎስ ማዞን ተጨማሪ ወታደሮች እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

የስፔኑ ሊቀ ጳጳስ ከማድሪድ ለሚመጣው ወታደራዊ ክፍል የሚሆን ጊዜያዊ የመጠለያ ጥያቄ እንደቀረበ ገልጸው፥ ሃገረ ስብከቱ በተቻለ መጠን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ከዚህም በተጨማሪ “በአብሮነት የተቸገሩትን ለመርዳት የሚያስችሉ የእርዳታ ቁሳቁሶችን እና ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነው” በማለት አጽንዖት በመስጠት ከገለጹ በኋላ፥ “ለመቆያ እና ማረፊያነት እንዲያገለግሉ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን የሃገረ ስብከቱን ተቋማት አዘጋጅተናል” በማለት ሁሉም ክርስቲያኖች በአደጋው በጣም ከተጎዱት ጋር አንድ ሆነው እንዲተባበሩ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል። 

በመከራ ጊዜ የተላለፈ መልዕክት                                                                                                                                         ሊቀ ጳጳስ ቤናቬንት በመጨረሻም፣ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ሰው “እምነት እና ተስፋውን እንዲጠብቅ ብሎም ይህ መከራ ለመንፈሳዊ እድገት እድል እንደሚሆን በማሳሰብ፥ “በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በአምላክ በመታመን መኖር አስፈላጊ እንደሆነ፥ እንዲሁም ይህ ሁኔታ እንደ ወንድሞችና እህቶች አንድ እንድንሆን አጋጣሚውን ሊፈጥርልን ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

 

04 November 2024, 13:03