የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበርተኞች የቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊነት ለመቃኘት በሮም ተሰበሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“እሳቱ እየነደደ እንዲቆይ የሚያደርግ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር ሲኖዶሳዊነት በተግባር” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ዙር ስብሰባቸውን ሐሙስ ኅዳር 5/2017 ዓ. ም. በሮም የጀመሩት የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበርተኞች የማኅበራቸውን ዓላማ ታላቅነትን አክብረዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ ዝግጅት በቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል የቸርነት ተግባራት የሚመሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ማኅበራትን እና ግለሰቦችን እንደሚሰበስብ ታውቋል። ሮም ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቦታዎች ማለትም በካዛ ትራ ኖይ ሆቴል እና በጊዮን ቲያትር የሚካሄደው ዝግጅቱ እሑድ ህዳር 8/2017 በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲዚሊካ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚጠናቀቅም ታውቋል።
ለር. ሊ ጳ. ፍራንችስኮስ የሲኖዶሳዊነት ጥሪ ምላሽ መስጠት
ምልዓተ ጉባኤው እና ወርክሾፖቹ የሲኖዶሳዊነት ልምድን ለማዳበር፣ ተሳታፊዎቹ ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ፣ እርስ በርስ እንዲማማሩ እና ድሆችን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማደስ ያለመ እንደ ሆነ ታውቋል።
የጉባኤው ቁልፍ ርዕሦች የቅዱስ ቪንሴንት መንፈሳዊነት፣ የጨዋነት መግለጫዎች እና በማኅበረስቡ በተገለሉ ሰዎች ላይ ሲኖዶሳዊነት ያለው ተጽእኖ የሚሉት እንደሆኑ ታውቋል።
ለዝግጅቱ ድምቀት ከሰጡት መካከል አንዱ፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ ያደረጉት ንግግር እንደሆነ ተመልክቷል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግሮች፣ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች የቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር መንፈሳዊነት የሚያጠናክሩ አስተምህሮች እና ወቅታዊ ፈተናዎችን በእምነት እና በጎ አድራጎት ለመቋቋም የሚረዱ ዝግጅቶች መቅረባቸው ታውቋል።
ለወደፊት ትውልዶች የቅዱስ ቪንሴንት ዓላማ ቀጣይነት የሚያረጋግጡ በተለይ ወጣቶች ዝግጅቱን እንዲካፈሉ ተደርጓል።