ፈልግ

የሕግ ባለሙያ እህት ጆሲ ጆይ ኬረላ ውስጥ ከጎሳ አባላት ጋር ሆነው የሕግ ባለሙያ እህት ጆሲ ጆይ ኬረላ ውስጥ ከጎሳ አባላት ጋር ሆነው  

እህት ጆሲ ሕንድ ውስጥ በሰብዓዊ መብቶች ላይ እየሠራች እንደምትገኝ ተገለጸ

ማክሰኞ ኅዳር 1/2017 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1948 ዓ. ም ጀምሮ በየዓመቱ ኅዳር 1 ሲከበር መቆየታ ይታወቃል። ይህን ዕለት ምክንያት በማድረግ ሕንድ ውስጥ በማኅበረሰቡ ለተገለሉ ወገኖች ጠበቃ በመሆን በሥራ ላይ የምትገኝ ሕንዳዊ መነኩሴ እና የሕግ ባለሙያ እህት ጆሲ ጋር የቫቲካን ዜና አገልግሎት ቆይታ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፈው ዓመት የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ለሰብዓዊ መብት መከበር ያለው ቁርጠኝነት መቼም ቢሆን አያልቅም!” ካሉ በኋላ፥ “በጥበብ እና በትዕግስት በሰላም አብሮ ለመኖር የሰሩ ወንዶች እና ሴቶች ዓርዓያን ሁሉም ሰው እንዲከተል” በማለት መጋበዛቸው ይታወሳል።

ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ወስነው ከተነሱ ሰዎች መካከል ሕንዳዊ መነኩሴ እና የሕግ ባለሙያ እህት ጆሲ ጆይ አንዱ ናት። እህት ጆሲ ጆይ በሕንድ ኬረላ ግዛት በሚገኙ ጎሳዎች መካከል የሴቶችን፣ የሕጻናትን እና የአነስተኛ ገበሬዎችን ሕይወት ለመለወጥ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን፣ ነፃነታቸውን እና መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ በመሥራት ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።

ሕጋዊ አገልግሎት መስጠት
የእህት ጆሲ የሕግ ተሟጋችነት አገልግሎት፥ የፓኒያ ጎሳ አባል የነበረች ሴት በደረሰባት ድንገተኛ ሞት የካሳ ክፍያን በተመለከተ ፈታኝ ጉዳይ የተጀመረ ሲሆን፥ መንግሥት ለቤተሰቧ ከፍተኛ የካሳ ገንዘብ እንዲከፍል ማድረጓን በማስታወስ፥ ስኬቷ በሕግ ተሟጋችነት የመለወጥ ኃይል ላይ ያላትን እምነት ያጠናከረ መሆኑን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግራለች።

መንግሥት በኬራላ ግዛት ውስጥ እህት ጆሲን የሴቶች እና ሕፃናት መምሪያ የሕግ አማካሪ አድርጎ የሾማት በመሆኑ ይህ ሹመት የነበራትን ሚና የበለጠ እንዲሰፋ ማድረጉን ገልጻለች። በዚህ የሃላፊነት ሚናዋ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም፣ ነፃ የሕግ ውክልና ለመስጠት እና ለተጎጂዎች የሥነ-ልቦና ድጋፍ እንድትሰጥ ማስቻሉ ታውቋል። እህት ጆሲ በአምስት አካባቢያዊ አስተዳደሮች ላይ ስልጣን ያላት በመሆኑ በሕግ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የመግባት ስልጣንን የበለጠ እንዳጠናከረላት ገልጻለች።

እህት ጆሲ ቤተ ክርስቲያኗ ያቀረበችላትን የሲኖዶሳዊነት ጥሪ ተቀብላ ከሌሎች ጋር በመተባበር የበጎ ፈቃደኞች ቡድንን በመደገፍ ላይ እንደምትገኝ ታውቋል። ሁሉም በጋራ ሆነው ሕጋዊ እና ስሜታዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ በወረዳው ውስጥ የተገለሉትን በመርዳት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

እህት ጆሲ ለባለጉዳዮች የምክር አገልግሎት ስትሰጥ
እህት ጆሲ ለባለጉዳዮች የምክር አገልግሎት ስትሰጥ

የጥብቅና ዓመት
እህት ጆሲ ባለፈው ዓመት ብቻ 105 የቤት ውስጥ ጥቃቶችን፣ 30 የቤተሰብ ጉዳዮችን፣ 17 የመሬት ይዞታ ጉዳዮችን በመከታተል እና 117 የምክር አገልግሎት ስብሰባዎችን በንቃት መሳተፏ ታውቋል። “የናዝሬት በጎ አድራጎት ገዳማውያት ማኅበር” አባል የሆነችው እህት ጆሲ፥ በራሷ ቁርጠኝነት እና እምነት የበለጠ ፍትሃዊ ማኅበረሰብን ለመፍጠር በምትፈልገው የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ ላይ በመሥራት ላይ የምትገኝ መሆኗን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቆይታ አስረድታለች።


 

11 December 2024, 15:47