ክርስቶስ ሕያው ነው፤ ተስፋችን ነው! “የቆየ ቁርሾ”
ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ ችግር የሚገጥማቸው ከአባሎቻቸው አንዱ ካለፉት ልምዶች የተወረሱ ጠባሳዎች ሲኖሩት እንደ ሆነ ግልጽ ነው። ደስታ የራቀው የልጅነት ወይም የጉርምስና ጊዜ ትዳርን የሚጎዱ ግላዊ ቀውሶችን ሊያራባ ይችላል። ሁሉም ሰው በእውቀት የበሰለና ጤናማ ከሆነ፣ ቀውሶች አይደጋገሙም፣ ቢደጋገሙም አሳዛኝታቸው አናሳ ይሆናል። ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ሰዎች ከጉርምስና በኋላ መምጣት ወደ ነበረበት የብስለት ደረጃ የሚደርሱት በአርባዎቹ ዕድሜአቸው ብቻ ነው። አንዳንዶች የሚያሳዩት ፍቅር ራስን ብቻ ወዳድ፣ ለራስ አብዝቶ ተጨናቂና ራስን ማዕከል ያደረገ የልጅ ዐይነት ፍቅር ነው፤ የፈለገውን ሲያጣ የሚጮህ ወይም የሚያለቅስ እርካታ የሌለው የፍቅር ዐይነት ነው። ሌሎች ደግሞ የሚወዱት በጥላቻ፣ በምሬትና በትችት በተሞላና ሌሎችን መውቀስ በሚፈልግ የጉርምስና ፍቅር ነው፤ በራሳቸው ስሜቶችና አጉል ሕልሞች የተጠመዱ እነዚህን የመሰሉ ሰዎች ሌሎች ሰዎች ባዶነታቸውን እንዲሞሉላቸውና ማናቸውንም ምኞታቸውን እንዲያሳኩላቸው ይጠብቃሉ።
ብዙ ሰዎች ውለታን የማይጠብቅ ፍቅር ሳይኖራቸው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ይህም ሌሎችን የማመንና ለሌሎች ክፍት የመሆን ችሎታቸውን ይጎዳል። ከወላጆችና ከቤተሰብ አባላት ጋር ጥሩ ግንኙነት ካልተፈጠረና ችግሩ በወቅቱ ካልተፈታ፣ እንደገና ሊከሰትና ጋብቻን ሊጎዳ ይችላል። ስለዚህ መፍትሔ ያላገኙ ጉዳዮችን መፍታትና የማንጻት ሂደት ማካሄድ ያስፈልጋል። በትዳር ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ፣ ትልቅ ውሳኔዎችን ከመወሰን በፊት፣ እያንዳንዱ የትዳር አጋር የራሱን ወይም የራስዋን ታሪክ በሚገባ ማወቃቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህም የእርቅን፣ ይቅር ለማለትና ይቅር ለመባል የሚያስችል ጸጋ በጽናት የመለመንን፣ እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ የመሆንን እንዲሁም ተስፋ ሳይቆርጡ ጥረት የመቀጠልን አስፈላጊነት መገንዘብን ያካትታል። ራስን በሐቅ መገምገም የራስ ጉድለትና ብስለት ማጣት ምን ያህል ግንኙነትን እንደሚጎዳ ለመረዳት ያስችላል። በደለኛው ሌላ ሰው መሆኑ ግልጽ ቢመስል እንኳ፣ እርሱ ወይም እርስዋ እስኪለወጡ ድረስ በመጠበቅ ብቻ ቀውሱን ማስወገድ አይቻልም። ግጭቱ እንዲፈታ ከተፈለገ፣ እኛ ደግሞ በራሳችን ሕይወት ውስጥ ሊያድግ ወይም ሊታረቅ የሚገባው ነገር ምን እንደ ሆነ መጠየቅ አለብን።
ከትዳር መፍረስና ፍቺ በኋላ የሚደረግ ድጋፍ
በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ የራስን ክብርና የልጆችን ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል ልቅ ለሆኑ ፍላጎቶች አለመሸነፍን ወይም ከባድ በደልን፣ ሁከትን ወይም ሥር የሰደደ ጥቃትን ማስወገድ ይጠይቃል። እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ “መለያየት አይቀሬ ይሆናል። አንዳንዴ፣ በበደል ወይም በሁከት ምክንያት ከሚደርስባቸው ከባድ ጉዳት፣ ከውርደትና ከብዝበዛ እንዲሁም ከቸልተኝነትና ከግዴለሽነት ለመታደግ ሲባል ለጥቃት የተጋለጠ የትዳር አጋርን ወይም ጨቅላ ሕጻናትን ማራቅ ሲያስፈልግ፣ መለያየቱ ከግብረ ገብ አኳያ አስፈላጊም ሊሆን ይችላል”። ቢሆንም “መለያየት እንደ መጨረሻ አማራጭ የሚታሰበው፣ ሌሎች አሳማኝ የማስታረቅ ጥረቶች ሁሉ ከንቱ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ መሆን አለበት”። የሲኖዶስ አባቶች እንዳመለከቱት፣ “ለተለያዩ፣ ለተፋቱ ወይም ለተጣሉ ጥንዶች ሐዋርያዊ እንክብካቤ ለማድረግ ልዩ ግንዛቤ ማሳደር እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይ ያለ አግባብ መለያየት፣ መፋተት ወይም ብቸኝነት ላጋጠማቸው፣ ወይም ከባል ወይም ከሚስት በኩል በሚደርስባቸው በደል ምክንያት የጋራ ሕይወታቸውን ለማkረጥ ለተገደዱ ሰዎች ክብር መስጠት ያስፈልጋል። በዚህ በደል ምክንያት ስለደረሰው እንግልት ይቅር ማለት ቀላል ባይሆንም፣ የእግዚአብሔር ጸጋ ይህን ጉዞ እንዲቻል ያደርገዋል። ስለዚህ ሐዋርያዊ እንክብካቤ በሰበካዎች ውስጥ ልዩ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማዕከላትን በማከም የማስታረቅና የመሸምገል ጥረት ማድረግን ያካትታል”። (259) ከዚህ ሌላ፣ “ተፋተው ዳግመኛ ያላገቡና ብዙውን ጊዜ በጋብቻ የመተማመን ምሥክርነት ያላቸው ሰዎች አሁን ባሉበት ሁኔታ በሕይወት የሚያኖራቸውን ምግብ በቅዱስ ቁርባን እንዲያገኙ ሊበረታቱ ይገባል። በተለይ ልጆችን የሚያካትት ሁኔታ ሲኖር ወይም ከባድ የገንዘብ ችግር ሲያጋጥም፣ የአጥቢያ ማህበረ ሰብና ጳጳሳት እነዚህን ሰዎች መደገፍ ይኖርባቸዋል”። (260) የቤተሰብ መፍረስ በይበልጥ አስደንጋጭና አሳዛኝ የሚሆነው ድሆች ሲሆኑ ነው፣ ምክንያቱም እነርሱ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ያላቸው ሀብት አናሳ ነው። ድሃ ሰው ደግሞ አንዴ ከቤተሰብ ጉያ ከተፈናቀለ ለመገለልና ምናልባትም ለጉዳት በእጥፍ የተጋለጠ ይሆናል።
ተፋተው እንደ ገና ትዳር የመሠረቱ ሰዎችን የቤተክርስቲያን አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው። “እነርሱ ውጉዝ ስላልሆኑ” እንደ ተወገዙ ሊቆጠሩ አይገባም፣ አሁንም የቤተክርስቲያን ጉባኤ አካል ናቸው። (261) እነዚህ ሁኔታዎች “ማስተዋልንና በአክብሮት አብሮ መጓዝን ይጠይቃሉ። አድልዎ የተደረገባቸው የሚያስመስለውን ንግግር ወይም ምግባር ማስወገድና በማኅበረሰቡ ሕይወት እንዲሳተፉ ማበረታት ያስፈልጋል። ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለእነዚህ ሰዎች የሚያደርገው እንክብካቤ እምነቱንና ጋብቻ የማይፈርስ ስለ መሆኑ የሚሰጠውን ምሥክርነት ማርከሻ ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ ይልቁንም ይህን የመሰለ እንክብካቤ የክርስቲያን ማኅበረሰብ የፍቅሩ ልዩ መገለጫ ነው”።
በርካታ የሲኖዶስ አባቶችም “ከዚህ በፊት የተጋቡ የሚመስሉ ነገር ግን እውነተኛ ጋብቻ ያልሆኑትን ጋብቻ አልነበሩም የማለት ሂደት (nullity) በቤተክርስቲያን ለሁሉ ተደራሽና ጊዜ ቆጣቢ የማድረግንና ከተቻለም ሂደቱን ያለ ክፍያ የመፈጸምን አስፈላጊነት አበክረው ገልጸዋል”። የሂደቱ ዘገምተኛ መሆን ጉዳዩ በሚመለከታቸው ወገኖች ላይ ጭንቀትንና ውጥረትን ያስከትላል። እኔም ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቅርቡ ያወጣሁአቸው ሁለት ሰነዶች ጋብቻ አልነበረም (nullity) የማወጅ ሂደቶችን ቀላል አድርገውታል። በእነዚህ ሰነዶች አማካይነት “ጳጳሱ ራሱ፣ እረኛና መሪ ሆኖ በተሾመበት ቤተክርስቲያን ውስጥ አደራ በተሰጡት ምእመናን ጉዳይ ላይ መዳኘት እንደሚችል ግልጽ ለማድረግ ፈለግሁ” (265)። “ስለዚህ፣ እነዚህን ሰነዶች ተግባራዊ ማድረግ አንዳንድ ጉዳዮችን ራሳቸው እንዲመረምሩ፣ በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ፣ ምእመናን በቀላሉ ፍትህ ማግኘት መቻላቸውን እንዲያረጋግጡ በተጠሩ የሰበካ ባለሥልጣናት ላይ የተጣለ ትልቅ ኃላፊነት ነው። ይህም ኃላፊነት ከካህናትና ከምእመናን የተወጣጡና በዋናነት ለዚህ አገልግሎት የተወከሉ በቂ ሠራተኞች ማዘጋጀትን ያካትታል። ከቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጋር የተያያዙ መረጃዎች፣ ምክሮችና የሽምግልና አገልግሎቶች ለተለያዩ ግለሰቦች ወይም ችግር ለገጠማቸው ጥንዶችም ተደራሽ መሆን አለባቸው። እነዚህ አገልግሎቶች ስለ ተክሊል ሂደት ያለውን ሁኔታ አስቀድሞ ለማጣራት ከግለሰቦች ጋር መገናኘትንም ያካትታሉ (ንጽ. ሚቲስ እዩደክስ፣ አንቀጽ. 2-3)”።
የሲኖዶስ አባቶች “የባልና ሚስት መለያየት ወይም መፋታት የዚህ ሁኔታ ሰለባዎች በሆኑ ልጆች ላይ የሚያስከትላቸውንም ውጤቶች” አመልክተዋል። ስለዚህ፣ የልጆች ጥቅም ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንጂ በሌላ ውጫዊ ፍላጎት ወይም ዓላማ መደብዘዝ የለበትም። እኔም ለተፋቱ ወላጆች አደራ የምለው፥ “ልጃችሁን ከቶ መያዣ እንዳታደርጉት” ነው። እናንተ በብዙ ችግርና በብዙ ምክንያቶች ተለያይታችኋል። ሕይወት ይህን ፈተና ሰጥታችኋለች፣ ልጆቻችሁ ግን ይህ መለያያት የሚያስከትለውን ጫና መሸከም ወይም ሌላውን የትዳር አጋር ለማጥቃት መያዣ መሆን የለባቸውም። እናታቸው አብረው ባይኖሩ እንኳ ስለ አባታቸው በጎ ስትናገር፣ አባታቸውም ስለ እናታቸው በጎ ነገር ሲናገር እየሰሙ ማደግ አለባቸው”። (268) የልጅን ፍቅር ለማግኘት ወይም በበቀል ስሜት ወይም ራስን ንጹሕ አድርጎ ለማቅረብ ሲባል ሌላውን ወላጅ ማንኳሰስ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ይህን ማድረግ የልጁን ውስጣዊ ሰላምና ጸጥታ ያውካል፣ የማይሽር ቁስልም ይፈጥራል።
ቤተ ክርስቲያን፣ የትዳር አካል የሆኑ የግጭት ሁኔታዎችን ስለምትገነዘብ፣ ለችግር ይበልጥ በተጋለጡትና ብዙውን ጊዜ በጸጥታ በሚሰቃዩ ሕጻናት ስም መናገርዋን ማቆም አትችልም። ዛሬ፣ “የዳበረ ስሜትና የጠራ የሥነ ልቦና ትንተና ችሎታ ያለን ቢመስልም፣ የልጆችን ውስጣዊ ጉዳት በተመለከተ ዲዳዎች ሆነናል ወይ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ።… የቤተሰብ አባላት፣ የጋብቻ ትስስርንና መተማመንን እስከማፍረስ ድረስ እርስ በርስ በሚጎዳዱበት ቤተሰብ ውስጥ ሕጻናት የሚደርስባቸው ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ይሰማናል?” (269) እነዚህን የመሰሉ ጉዳትን የሚያመጡ ተሞክሮዎች ሕጻናት ቁርጥ ውሳኔን የሚጠይቅ እድገት እንዲኖራቸው ሊያደርጉ አይችሉም። ስለዚህ፣ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ትዳራቸውን አፍርሰው አዲስ ጋብቻ የመሠረቱ ወላጆችን ማግለል የለባቸውም። ይልቁንም ልጆቻቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ሊያሳትፉአቸውና ልደግፉአቸው ይገባል። “የተወገዙ ይመስል ከማኅበረሰቡ ሕይወት ካራቅናቸው እነዚያ ወላጆች ልጆቻቸውን በክርስቲያናዊ ሕይወት ለማሳደግ፣ የጽኑና ተጫባጭ እምነት ተምሳሌት ለመሆን የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ እንዴት ልናግዛቸው እንችላለን? በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ቀድሞም ቢሆን ባለባቸው ሸክም ላይ ሌላ ሸክም የሚጨምር ነገር ከማድረግ እንቆጠብ”። የወላጆችን ቁስል ማዳንና ለእነርሱም መንፈሳዊ ድጋፍ መስጠት ለሕጻናትም ይጠቅማል፤ ይህን አሳዛኝ ተሞክሮ እንዲያልፉ የምትረዳና የሚያውkት ቤተክርስቲያን ታስፈልጋቸዋለች። ፍቺ መጥፎ ነገር ነው፤ የፍቺዎች መብዛትም እጅግ አሳሳቢ ነው። ስለዚህ፣ ቤተ ሰቦችን በተመለከተ የእኛ ዋና ሐዋርያዊ ተግባር ፍቅራቸውን ማጠናከር፣ ቁስላቸውን ማዳንና በዘመናችን የሚታየው ይህ ድራማ እንዳይስፋፋ መሥራት ነው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 240-246 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
አዘጋጅ አባ ዳንኤል ኃይለ