የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ለ2017 ዓ.ም. የስብከተ ገና ወቅት ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት
ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ምዕመናን እና ወጣቶ
መላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ
በክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች፦
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት 57ኛውን መደበኛ ጉባኤያችንን ሞጆ በሚገኘው የኮንሶላታ ልዑካን የሱባኤ ማዕከል ከህዳር 30 እስከ ታህሣስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. አካሂደናል። በዚህ የጌታችን የየኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በልባችን ለመቀበል ዝጅግት በምናደርግበት በተቀደሰ ወቅት በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። ይህ የስብከተ ገና ወቅት፤ ግጭት፣ ስቃይና ተስፋ አጥነት ያጠላባት አለም ላይ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን ወሰን የሌለውን ፍቅር፣ ተስፋ እና የእርሱን ዘለዓለማዊውን የሰላም ቃልኪዳን ያስታውሰናል። ስለሆነም የአለም ብርሃን የሆነውን፣ ጨለማን ሊያስወግድ ቤዛ ሊሆነን የሚመጣውን መሲሕ ለመቀበል በጸሎት፣ በንስሀ እና በፍቅር ሥራ ልንዘጋጅ ይገባል። እኛ እረኞቻችሁ ለመላው ካቶሊካውያንና በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የተስፋ፣ የሰላም እና የዕርቅ የሆነውን የልደት መንፈስ በመላበስ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን እንድትጠባባቁ ጥሪ እናቀርባለን።
በአገራችን በጦርነት፣ በውስጥ ግጭቶች፣ በኢኮኖሚ የዋጋ ንረት ሳቢያ በህዝባችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ የመንፈስ ስብራትና ቁስለት እንገነዘባለን። ባሳለፍናቸው ዓመታት የተከሰቱ ጦርነቶችና አሁንም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ያለው ግጭትና የሰላም እጦት፣ ህዝባችን ከኖረበት ቀዬ የመፈናቀል እና የውድመት አሻራ ትተው እንዳለፉ፣ እያለፉም መሆኑን በጥልቅ እንገነዘባለን። በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች የብዙዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ቤተሰቦች ተበታትነዋል፣ መኖሪያ ቤቶች እና ንብረቶች ወድመዋል፣ እንዲሁም ማኀበረሰባችን ተከፋፍሏል። ከሁሉም በላይ ንጹኃን ዜጎች የግጭት እና የጥላቻ መንፈስ ሰለባ ሆነዋል።
በተለይም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታየው የሰላም እጦት የቤተክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ተልዕኮም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ አብዛኞቹ ቁምስናዎቻችን ተደራሽ አይደሉም፣ ብሎም አንዳንዶቹ በራቸውን ለመዝጋት ተገድደዋል። የሐዋርያዊ ሥራ፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማቶቻችን ወድመዋል። አገልጋዮቻችን እና ሰራተኞቻችን የጸጥታ ችግር ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተጋላጭ ሆነው ለመሥራት ተገደዋል፣ አንዳንዶቹም እየደረሰባቸው ባለው ዛቻና የሰላም ዕጦት ምክንያት ያሉበትን ቦታ ለመልቀቅ ተገደዋል። እኛ የእምነት አባቶቻችሁ እናንተ ካቶሊካውያንና በጎ ፍቃድ ያላቸውን ሁሉ ለነዚህ ሐዋርያዊ ድጋፍ ማግኘት ላልቻሉ እና በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለመኖር የተገደዱ ክርስቲያን ወንድም እህቶቻችን እና ወገኖቻችን ሁሉ እንድትጸልዩ ጥሪ እናቀርባለን።
በዚህ የስብከተ ገና ዝግጅት ወቅት በምናበራው የተስፋ፣ የሰላም፣ የደስታ እና የፍቅር ሻማ በአሁኑ ወቅት በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት፣ የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን ላጡት፣ ተስፋ ለቆረጡት እና በፍርሃት ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን እንጸልይላቸው፣ በልባችንም እናስባቸው። ይህ የስብከተ ገና መልእክት እነዚህን ከባድ እውነታዎች በታማኝነት እና በርኅራኄ እንድንጋፈጥ ያሳስበናል። የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ስቃይ፣ የተሰደዱት፣ የተፈናቀሉት እና የሚወዷቸውን ሕይወት ያጡ ወገኖች ጩኸት የኛም የሁላችንም ጩኸትና እምባ ነው። ህመማቸውን በርኅራኄ እና በፍቅር እንድንመልስ ይህ የዝግጅት ወቅት ይጋብዘናል።
አዳኛችን ክርስቶስ በዚህ ሀገራችን እያሳለፈች ባለው መከራ መካከል እርሱን ተስፋ እንድናደርግ ይጠራናል። የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የአዲስ ዘመን ጅማሬን የሚያመለክት፣ ፍቅር በጥላቻ ላይ ድል የሚነሳበት እና ብርሃን ጨለማን የሚያጠፋበት ታላቅ ወቅት ነውና ቤተክርስቲያናችን በነቢዩ ኢሳይያስ ላይ “ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፡ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ 9፡6) ተብሎ በተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል እንድናስተነትን ትጋብዘናለች።
የሰላም ንጉስ ክርስቶስ በተወለደበት በዚያ ሁከት በሞላበት ወቅት መላእክት የጌታን መምጣት በዝማሬ እንዲህ ብለው አወጁ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን።” (ሉቃስ 2፡14) ታድያ ይህ ሰላም ወዴት አለ? ክርስቶስ የገባልንን የሰላም ቃልኪዳን አሁን ካለንበት ስቃይ እና መከራ ጋር እንዴት ልናስታርቅ እንችላለን? የሰላም ንጉስ ክርስቶስ የጦርነት መሳሪያን፣ የጥፋት፣ የመከፋፈል እና የጥላቻ መንፈስን በማስወገድ የሰላም መሳሪያ እንድንሆን፣ ፍትህ እና አንድነት የምንሰብክ እንድንሆን ይጋብዘናል። በዚህ በስብከተ ገና ወቅት ክርስቶስ በልባችን እንዲወለድ የሰላም የዕርቅ እና የፍትህን መንፈስ ልንላበስ ይገባል። ከክርስቶስ ጋር ለሚኖረን ህብረት “እሺ” በማለት ለጥላቻ እና ለክፍፍል ግን “እምቢ” በማለት በተስፋ ለተሞላ የፍቅር ሥራ ልንነሳ ይገባል። ያለደስታ ተልዕኮ የለም፤ ያለደስታ ሰላም የለም! ያለ ፍትህ ሰላም የለም! ክርስቶስ እውነተኛ ደስታችን እና ሰላማችን ነው። “ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።” (አሞጽ 5፡24)
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለማክበር ልባችንን በምናዘጋጅበት ወቅት ሁላችንም በሕይወታችን የሰላም መሳሪያ ልንሆን ይገባል። ይህም የሚሆነው አሳታፊ የሆነ የውይይት ባህላችንን በማዳበር፣ የመነጋገርና የመግባባት እንዲሁም በተሰበረ ልብ ተሰሚነት አጥተው በየቦታው በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችን ድምጽ በመሆን ነው።
የሰላም ንጉስ ክርስቶስ በአለማችን በሰላም እጦት ለሚሰቃዩ ሁሉ እውነተኛ ሰላም እንዲያወርድልን እንጸልይ። ክርስቶስ በጦርነት የቆሰሉትን ያድንልን ዘንድ፣ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋ እንዲሆናቸው፣ እንዲሁም ምድራችን ሰላማዊ እና ፍትሕ የሰፈነባት እንድትሆን እና ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባት ያደርግልን ዘንድ እንጸልይ። በዚህም ወቅት የክርስቶስን ቅዱስ መንፈስ በመላበስ ከሚሰቃዩ እና ከተጨነቁ ነፍሳት ጋር በፍቅር እና በርኅራኄ እናሳልፍ።
በዚህ የስብከተ ገና ወቅት የአዳኛችንን ልደት ለማክበር መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ራሳችንን እውነተኛ የሰላም መሳሪያ ለመሆን እናዘጋጅ። ጥላቻ እና መከፋፈልን በክርስቶስ ፍቅር የሚያሸንፍ፣ ተስፋ የቆረጠውን በክርስቶስ እውነተኛ ተስፋ የሚሞላ ማህበረሰብ ይኖረን ዘንድ ሁላችንም ልባችንን ክፍት ልናደርግ ይገባል።
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የሀገራችንን መሪዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና መላው ማህበረሰብ ለውይይት፣ ለፍትህ እና ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ እንማጸናለን። እውነተኛ መሪነት በማዳመጥ፣ እውነትን በመፈለግ እና ለማህበረሰብ የጋራ ጥቅም በመሥራት ውስጥ ይገለጻል። በሀገራችን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የማህበረሰብ አካላት መካከል በተለይም በግጭት ውስጥ ካሉት ጋር የውይይት መድረክ ለመፍጠር የተለያዩ አካላት እየተጫወቱት ያለውን ጥረት እና ተስፋ ሰጪ ውጤታቸውን እናደንቃለን፤ እናበረታታለንም። ይህም ተነሳሽነት ዘላቂ መፍትሄ እና ለውጥ ያመጣ ዘንድ ሁሉም ዜጎቻችን በቤተሰቦቻቸው እና በማህበረሰባቸው ውስጥ ይቅርታን እና እርቅን የሕይወት ዘዬያቸው እንዲያደርጉ እና ለሌሎች ምሳሌ እንዲሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የክርስቶስ ብርሃን በሁላችን ላይ እንዲበራና እንዲመራን በተለይም ልባቸው የተሰበረባቸውን እና በስነልቦና የተጎዱ ወገኖቻችንን ልባቸውን እንዲጠግን እንጸልያለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የተስፋ፣የሰላምና የአንድነት ብርሃን የተሞላች ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር በቸርነቱ እና በጸጋው ይርዳን! አሜን