ብጹእ አቡነ ፋዶል የማሮናዊት ቤተ ክርስቲያን ለሲኖዶሳዊነት ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ማሮናይቶች መነሻቸው ‘ሌቫንት’ ተብለው ከሚጠሩ በመካከለኛው ምስራቅ ሜዲትራኒያን አከባቢ በሚገኙ ሃገራት ውስጥ ሲሆን፥ የክርስቲያን ሀይማኖት ቡድን የሚመደቡ በዋነኛነት ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ሙሉ ግንኙነት ካለው የምስራቅ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከሆነው ከማሮናይት ቤተክርስቲያን ጋር የተያያዙ ናቸው።
በአፍሪካ የማሮናዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ሲሞን ፋዶል ስለ ሲኖዶስ ለሲኖዶሳዊነት እና በአፍሪካ ውስጥ ያለው የማሮናዊት ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን የወደፊት አቅጣጫ ላይ ስላለው ተፅእኖ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የገለጹ ሲሆን፥ የሲኖዶሱ ሂደት በተለያዩ የአፍሪካ ባህላዊ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት እንደሚታይ እና እንደሚተገበር ያላቸውን ግንዛቤ አቅርበዋል።
በአፍሪካ ውስጥ የማሮናይት ቤተክርስቲያን መገኘት
በአፍሪካ የማሮናዊት ሃዋሪያዊ አህጉረ ስብከት የተመሰረተው የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ በሚገኙ 24 አገሮች ውስጥ የሚገኙ የማሮናዊት ምዕመናንን ለማገልገል እና ለመንከባከብ ብጹእ አቡነ ስምዖን ፋዱልን የመጀመሪያ ጳጳስ አድርጎ በመሾም ቢሆንም፥ ሃዋሪያዊ ተልዕኮው የጀመረው ግን ከአራት ዓመት ቀደም ብሎ በ2006 ዓ.ም. እንደሆነ ይታወቃል።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ ውስጥ የማሮናዊት ቤተክርስቲያን መገኘት በርካታ ዓመታትን ወደ ኋላ በመመለስ ከ 1867 ዓ.ም. አከባቢ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የብጹእ አቡነ ፋዶል መቀመጫ ናይጄሪያ ውስጥ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው ማሮናዊት ቤተክርስቲያን ከአፍሪካ ጋር ለዘመናት የዘለቀውን ትስስር በማስታወስ፥ በአከባቢው ከ150 ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውን ጠቁመው፥ “የማሮናዊት ቤተክርስቲያን በአፍሪካ ውስጥ መገኘት ሥር የሰደደ ነው” ሲሉ በአህጉሪቱ የቤተክርስቲያኑ እድገት ላይ ተጽእኖ ያላቸውን ጥልቅ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አብራርተዋል።
ሲኖዶስ ለዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ያለው ጠቀሜታ
ብጹእ አቡነ ፋዶል የሲኖዶሳዊ ፅንሰ-ሀሳቦች ምን ያህል ከአፍሪካ ባህል ጋር እንደሚስማሙ በመጥቀስ ሲኖዶሳዊነት ለአፍሪካውያን አዲስ ፅንሰ ሀሳብ እንዳልሆነ አስረድተዋል። በማሮናዊት ባህል፣ ሲኖዶሳዊነት ከጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ሲተገበር የነበረ ነው ያሉት ብጹእነታቸው፥ የማሮናዊት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊ መዋቅር ውስጥ ብጹአን ጳጳሳት በሚያደርጉት ውይይት እና ጉልህ በሆኑ ውሳኔዎች ላይ በሚያደርጉት ምክክር ይህንን ሲኖዶሳዊ ትውፊት አስቀጥለዋል ብለዋል።
በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ቀኖና እና በማሮኒት ቤተክርስቲያን ልዩ ህግ እንደተገለጸው የጳጳሳት ሲኖዶስ በማሮናዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ወሳኝ አስተዳደራዊ አካል ሲሆን፥ በእነዚህ ቀኖናዎች መሠረት የማሮናዊው ሲኖዶስ ትምህርታዊ፣ ሃዋሪያዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት በየጊዜው እንደሚሰበሰብ እና ይህም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ቅርሶችን እና የዛሬውን የማሮናዊ ማኅበረሰብ ልዩ ፍላጎቶችን የሚያንፀባርቅ የትብብር አካሄድን ያካትታል ብለዋል።
‘የሲኖዶሳዊ ሂደት ውበት የሚተላለፉት ውሳኔዎች ከበላይ አካል የማይመጡ መሆናቸው ብቻ ሳይሆኑ በውይይት፣ በመተባበር እና ምዕመናን ከሚሰጡት ግብዓቶች የተገኙ መሆናቸው ነው’ ያሉት ብጹእ አቡነ ፋዶል፥ “ከመጀመሪያው ጀምሮ በአህጉረ ስብከታችን ሥር በሚገኙ ሁሉም አደረጃጀቶች ማለትም ሃገረ ስብከቶችን፣ ጉባኤዎችን፣ ምዕመናንን፣ ገዳማዊያትን እና ገዳማዊያንን በማሳተፍ የቅዱስ ሲኖዶስ አንድ አካል ነን” በማለት ለማሮናውያን ሲኖዶሳዊነት ከባእድ የመጣ አዲስ ሀሳብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በሲኖዶስ ላይ የማሮናዊያን ድምጽ
ብጹእ አቡነ ፋዶል የማሮናዊት ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ ያላትን ጠቀሜታ እና ለሲኖዶሱ ሥራ የምታበረክተውን አስተዋፅዖ አበክረው በመግለጽ፥ “የዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን አካል እንደመሆናችን መጠን ሀሳባችንን የመግለጽ እና ልምዶቻችንን የማካፈል መብት አለን” ካሉ በኋላ በሲኖዶሱ ውስጥ ባለን ወኪሎቻችን አማካኝነት በሚደረጉ ሰፋፊ ውይይቶች ላይ ድምፃችንን በማሰማት አመለካከታችንን እናዋጣለን ብለዋል።
ብጹእነታቸው አህጉረ ስብከታቸው ከናይጄሪያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ የጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመሆን በሲኖዶሱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ስብሰባዎችን፣ ሴሚናሮችን እና ውይይቶችን በማዘጋጀት በቅርበት ይሰራ እንደነበር አስታውሰው፥ በተመሳሳይ ሁኔታ በሊባኖስ ከሚገኘው ማሮናዊት ቤተ ክርስቲያናችን መሪነት በማሮናዊት ሲኖዶስ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በመተባበር የሲኖዶስ ጉዞ አካል በመሆን መስራታቸውን ገልጸዋል።
በሂደቱ የተለያዩ ምዕራፎች ላይ ያዘጋጁትን ሪፖርቶች እንዳቀረቡ እና በእናት ቤተ ክርስቲያኗ በተዘጋጀው ሲኖዶሳዊ ሴሚናሮች እና ተግባራት ላይ እንደተሳተፉ፥ በዚህ መንገድ፣ የማሮናዊት ማህበረሰብ ድምፅ በሁለቱም ማለትም በአፍሪካ አህጉር እና በምስራቁ ክፍል ባለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‘ድምፆች’ እንደሚወከል አብራርተዋል።
ብጹእ አቡነ ፋዶል በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የማሮናውያን ድምጽ በአፍሪካ ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ እና ባህሎች የተቀረጹ እንደሆነ በመጥቀስ፥ ይህ ምሉዕነት የሲኖዶሱን ሂደት እንደሚያበለጽግ ገልጸው፥ “ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ሃሳቦች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች ስለሚያጋጥሟቸው ጉዳዮች የተሟላ እና የበለጸገ ግንዛቤ ይሰጣል” ብለዋል።
የምስራቁን ባህሎች ከአፍሪካ እውነታዎች ጋር ማመጣጠን
ጥንታዊ ትሁፊቶችን በሚሸፍነው የማሮናዊት ቤተ ክርስቲያንን እና በአፍሪካ ልዩ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ መካከል እንዴት ትክክለኛ ሚዛን ማምጣት እንደሚቻል ያነሱት ሊባኖሳዊው ጳጳስ፥ ይህ ሚዛን የሚመጣው ሁለቱንም ባህሎች “በማስማማት” ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ላሉ ማሮናዊት ቤተክርስቲያን አማኞች መልዕክት
በመጨረሻም ብጹእ አቡነ ፋዶል በአፍሪካ አህጉር ለሚገኙ የማሮናዊት አማኞች ባስተላለፉት መልዕክት ስለ ሲኖዶሱ ጠንካራ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ እና ለወደፊቷ ቤተክርስትያን እንዴት ሊያዘጋጃቸው እንደሚችል አሳስበው፥ “ሲኖዶሱ የጳጳሳት ወይም የነገረ መለኮት ሊቃውንት ሥራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ላይ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው” ብለዋል።
በማከልም እያንዳንዱ ክርስቲያን በእምነቱ እየተመራ እና እግዚአብሔር ማህበረሰቡን ወዴት እየመራ እንደሆነ በመገንዘብ፣ ሁሉም ሰው በቤተክርስቲያኑ ህልውና ላይ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ጭምር አሳስበው፥ በምዕመናን መካከል ተስፋ እና ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንዲሁም ሲኖዶሱ በአፍሪካ እና ከዚያ ባሻገር ላሉ ቤተክርስቲያናት አዲስ እውነታ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
'ገና በጉዞው መጀመሪያ ላይ ብንሆንም፥ ነገር ግን ወደ ተባበረች እና ደስተኛ ቤተክርስትያን እንዲሁም ይበልጥ ወደተዋሃደች ቤተክርስቲያን ለመድረስ ጥሩ መንገድ ላይ ነን ብዬ አስባለሁ’ ያሉት ብጹእ አቡነ ፋዶል በመጨረሻም፥
ቤተክርስቲያን በዕለት ተዕለት ህይወቷ ውስጥ ሲኖዶሳዊነትን ለመመስረት በምትጥርበት ወቅት፣ እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን በአፍሪካ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጋ ስትናገር አህጉሩን በሚመጥን እና ዓለም አቀፋዊው ቤተክርስቲያን በጥሞና ማዳመጥ በምትችልበት ልዩ ድምጽ እንድትናገር በመጋበዝ አጠናቀዋል።