ፈልግ

2021.11.26 Il Presepe nell'arte - libro di Rosa Giorigi 2021.11.26 Il Presepe nell'arte - libro di Rosa Giorigi 

የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ ‘ቤተክርስቲያን የተስፋ ምልክት እንድትሆን ተጠርታለች’ አሉ

ፍርሃት እና ጥርጣሬ በነገሰበት ዓለም ውስጥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በጣም ትልቅ የተስፋ ምልክት እና መልዕክት ነው የተባለ ሲሆን፥ የዘንድሮውን የብርሃነ ልደቱ በዓል እና ‘የተስፋ ነጋዲያን’ በሚል ርዕስ የሚከበረውን የኢዩቤልዩ ዓመት አስመልክቶ የቫቲካን ረዲዮ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች “በጦርነት በተመሰቃቀለው ዓለም ውስጥ ያለው የክርስቶስ ሰላም” በሚል መሪ ቃል አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል። በዚህም መሰረት የዛሬውን መልዕክት ያስተላለፉት የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ፕሬዝዳንት እና የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ታርቺስዮ ኢሳኦ ኪኩቺ ሲሆኑ መልዕክታቸው እንደሚከተለው ይቀርባል፦

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

                          የብፁዕ ካርዲናል ታርቺስዮ ኢሳኦ ኪኩቺ የገና መልዕክት

በጨለማው ውስጥ የሚያበራው ብርሃን መንገዳቸውን አጥተው በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተስፋ ቆርጠው ለሚንከራተቱ መንገደኞች የተስፋ ብርሃን ነው።

ይህ ብርሃን በጣም ትንሽ እና ኢምንት ብርሃን ብትሆንም እንኳን የተስፋ ምንጭ ይሆናል። ህይወታችን ጉዞ ነው፥ እኛ ተጓዦች ነን፥ እኛ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የምንጓዝ ተጓዦች ነን፣ በጨለማ ውስጥ የምንዞር፣ የእግዚአብሔርን መንገድ ለማግኘት የምንሞክር ተጓዦች ነን።

ለብቻ መጓዝ ቀላል አይደለም፥ ብቻችንን ብንጓዝ በፍርሃትና በጭንቀት እንዋጥ ነበር፣ ነገር ግን ከእኛ ጋር የሚጓዘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለን እናውቃለን።

በዚህ ጉዞ ከእኛ ጋር በጨለማ የሚራመደው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጨለማ ውስጥ የሚያበራ ብርሃን ነው። በክርስቶስ ልደት ትዕይንት ውስጥ አዲስ የተወለደው ሕፃን ‘በጨለማ ውስጥ የሚያበራ ብርሃን’ ተብሎ ተገልጿል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጨለማ እና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሕይወትን ተስፋ የሚያመጣ በጨለማ ውስጥ የሚያበራ ብርሃን ነው።

ዛሬ በዓለም ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች የብዙ ሰዎችን ሕይወትን እየነጠቁ ነው። በዓለም ላይ የዓመፃ አገዛዝ የበላይነቱን የያዘ ይመስላል። በማይናማር፣ በዩክሬን እና በቅድስት ምድር በተለይም በጋዛ ያሉ ሰዎችን እናስታውሳለን። በዓለም ላይ በሚነሱ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በግፍ ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን እናስታውሳለን።

እግዚአብሔር በስጦታ የሰጠንን ሕይወት ከመጀመሪያዋ እስከ ፍጻሜዋ ያለ ምንም ልዩነት መጠበቅ አለባት። በማንኛውም መልኩ ህይወትን የሚያሳጣ ግጭትን መታገስ ዬለብንም።

ሕይወትን መጠበቅ የተስፋ ብርሃን ምንጭ ነው። እኛ እንደ ቤተክርስቲያን የተጠራነው የተስፋ ምንጭ እንድንሆን እንጂ ተስፋ እንድንቆርጥ አይደለም።

በመጪው የኢዩቤልዩ ዓመት እኛ እንደ ቤተክርስቲያን በጨለማ ውስጥ ለሚንከራተቱ መንገደኞች መሸሸጊያ እና መጽናኛ ለመስጠት በራችንን በሰፊው መክፈት አለብን። እኛ ያንን የሚያበራውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ተሸካሚዎች መሆን አለብን።

እናም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር እንደሆነ እናውቃለን፣ ከእኛ ጋር አብሮን እየተጓዘ የተስፋ ብርሃን እንድናበራ ያበረታታናል።
 

25 December 2024, 11:51