በመላው ዓለም የሚገኙ የላቲን ሥርዓት ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች የኢዮቤልዩ ዓመት መግቢያን አከበሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዋዜማ ላይ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት የከፈቱት ሲሆን፥ በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ጳጳሳትም የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ዋና ጭብጥ በሆነው ተስፋ ላይ በማስተንተን የ2025 ኢዮቤልዩ ዓመት መግቢያን በየካቴድራሎቻቸው ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ታህሳስ 20/2017 ዓ. ም. አክብረዋል።
በቅድስት ሀገር የኢዮቤልዩ ዓመት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት
የቅድስት አገር ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ሀገረ ስብከታቸው በሆነው በናዝሬት በሚገኘው የብስራተ ገብርኤል ባዚሊካ ውስጥ በመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ አክብረዋል። የክብረ በዓሉ ሥነ-ሥርዓት የተጀመረው በጋራ መታደስ እና የተስፋ ጉዞን በሚያሳይ ኡደት እንደ ነበር ታውቋል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በዕለቱ ባሰሙት ስብከት፥ “በቅድስት ሀገር እየተፈጸመ ያለው ዓመፅ እና ስቃይ ሁሉንም ማኅበረሰቦች ስጋት ውስጥ በመክተት ሌሎችን በእምነት እና በተስፋ ለማየት ድፍረት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል” ብለዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ዋና ጭብጥ የሆነውን ተስፋ በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “በዙሪያችን ያሉ ነገሮች ሁሉ ስለ ጦርነት፣ ስለ ዓመፅ፣ ስለ ድህነት እና ስለ ችግር በሚነገርበት በዚህ ወቅት ስለ ተስፋ መናገር ከባድ እንደሚሆን ገልጸው፣ ተስፋ ትዕግስትን እንደሚጠይቅ እና ዘወትር ትዕግስት እንደሚያስፈልገው ቅዱስ ጳውሎስ ማስተማሩን አስታውሰው፥ ትዕግስ ያልታከለበት ተስፋ ሽንፈት እንደሆነ እና ያለ ትዕግስት ተስፋ ማድረግ ሌሎችን ማታለል ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።
የኢዮቤልዩ ዓመት እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን እና ልባችንን እንዲያድስ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው፥ ይህም ጉዟችንን በተስፋ እና በደስታ ወደፊት እንድንቀጥል የሚያስችለን መሆኑን ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ምእመናንን አስታውሰዋል።
በለንደን የኢዮቤልዩ ዓመት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት
ለንደን ውስጥ በዌስትሚኒስተር ካቴድራል የተፈጸመውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩት ብፁዕ ካርዲናል ቪንሰንት ኒኮልስ በስብከታቸው፥ “የመታደስ አንገብጋቢነት ባለበት ዓለማችን ውስጥ በሐዘን፣ በግጭት እና በጭካኔ መካከል ለሚገኙት የሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ ቀላል እና ምቹ አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።
የኢዩቤልዩ ዓመታ ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን ዳግም የምትጀምርባቸው አጋጣሚዎች እንደሆኑ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ቪንሰንት፥ “ይህ ቅዱስ ዓመት በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ተስፋ እንድናጠናክር እና እንድናድስ የሚገብዘን ነው” ብለዋል። በዕለቱ የተነበበውን የወንጌል ምንባብ መሠረት በማድረግ ሲናገሩ፥ ቅዱስ ቤተሰብ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው መንፈሳዊ ጉዞ፥ የሕይወት ጉዞአችንን የሚያነቃቃ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
በሰሜን አሜሪካ የኢዮቤልዩ ዓመት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት
የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ዋና ጭብጥ የሆነውን ተስፋን ያስቀደሙት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ካቶሊካዊ ጳጳሳት የኢዮቤልዩ ዓመትን በሀገረ ስብከቶቻቸው በደማቅ ሥነ-ሥር ዓት ከፍተዋል። በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ አንዳንድ ሀገረ ስብከቶች የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ምእመናን ለመስዋዕተ ቅዳሴ ወደ ካቴድራላቸው ወይም በካቴድራላቸው ውስጥ የኢዮቤልዩን መስቀል በመያዝ ባደረጉት ዑደት የተፈጸመው እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ይህ መስቀል ቁምስናዎች የኢዮቤልዩን ዓመት በልዩ ሥነ--ሥርዓት ለማክበር እንደሚጠቅማቸው ታውቋል።
በዩክሬን የኢዮቤልዩ ዓመት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት
ዩክሬን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያናት የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት መክፈቻን ያከበሩት የሩሲያን የቦምብ ጥቃቶች በመቃወም እንደ ነበር ታውቋል።
የግሪክ-ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ ብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ፥ በኪየቭ በሚገኘው የክርስቶስ ትንሳኤ ካቴድራል ውስጥ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል። የኪየቭ-ሃሊች ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ በቅዱስ ዓመት ዋዜማ ላይ ለምእመናኑ ባሰሙት ስብከት፥ “ዛሬ የዩክሬን ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ሲሉ አሳስበዋል።
ብጹዕነታቸው ለምዕመናኑ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “ሕዝባችን በጦርነት መካከል ተረጋግቶ ሳይሸነፍ ነፃነቱን ለመከላከል የቻለው በክርስቲያናዊ ተስፋ ነው” ስሊ ተናግረው፥ “ሕዝቡ ለልጆቹ ወደፊት የተሻለች ዓለምን ለመገንባት ዛሬ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል” ሲሉ አስረድተዋል።