ፈልግ

Cry my Beloved Country Cry my Beloved Country  (ANSA)

በ 2024 ብቻ 13 ሚስዮናውያን መገደላቸውን የፊደስ ጥናት አረጋገጠ

ዓመታዊው የፊደስ ጥናት እንዳረጋገጠው በ2024 ዓ.ም. ብቻ 13 የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሚስዮናውያን መሞታቸውን የዘገበ ሲሆን፥ ይህም አሃዝ በግጭት፣ በድህነት እና በሙስና በተጠቁ ክልሎች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች ጎላ አድርጎ ያሳያል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጳጳሳዊ ሚስዮናውያን ማኅበራት አገልግሎት የሆነው ፊደስ የዜና ማሰራጫ ተቋም በየዓመቱ በሚያደርገው ጥናት አማካይነት በዓለም ዙሪያ የተገደሉትን የሚሲዮናውያን እና ሃዋሪያዊ ሥራ ሠራተኞችን ታሪኮች ያቀርባል።

የጎረጎሳዊያኑ 2024 ዓ.ም. እየተገባደደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይፋ ያደረገው የዘንድሮው ሪፖርት የ13 የካቶሊክ ሚስዮናውያንን አሳዛኝ ሞት አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ስምንት ካህናት እና አምስት ምዕመናንን ጨምሮ ብዙውን ጊዜ ግጭት፣ ድህነት እና ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት በብዛት በሚታይባቸው ክልሎች የሚገኙ ህይወታቸው ለችግር የተጋለጡ ማህበረሰቦችን ለማገልገል የወሰኑ ወንዶች እና ሴቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።

ሪፖርቱ አሟሟታቸው የሰማዕትነት ጥብቅ መመዘኛዎችን ቢያሟላም ባያሟላም በሃዋሪያዊ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሁሉንም ካቶሊኮች በማካተት በእምነታቸው መሰረት ሲኖሩ የተገደሉትን “ሚስዮናውያን” በሚለው ቃል በስፋት ገልጿቸዋል።

ዓለም አቀፍ ጉዳይ
ለሚስዮናዊነት አገልግሎት በጣም አደገኛ የሆኑት ሁለቱ አህጉራት አፍሪካ እና ደቡብ አሜሪካ ሲሆኑ፥ በእያንዳንዳቸው አምስት ሞት ተመዝግቧል። በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሃገራት ውስጥ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሩን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል። በደቡብ አሜሪካ ደግሞ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ ሜክሲኮ እና ብራዚል ሚስዮናውያን ሠራተኞች የተገደሉባቸው አገሮች ነበሩ። ከእነዚህም ባሻገር ሪፖርቱ በአውሮፓ አህጉር ውስጥ በሚገኙት ፖላንድ እና ስፔን ሁለት ሚሲዮናዊያን እንደሞቱ የጠቀሰ ሲሆን፥ በሚስዮናውያን ላይ የሚፈጸመው ሰፋ ያለ የጂኦግራፊያዊ ጥቃት በአንፃራዊነት ሰላማዊ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ክልሎች ውስጥም ቢሆን በእምነት ላይ ለተመሰረተ ሥራ የሚተጉ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች አጉልቶ ያሳያል።

ለማህበራዊ ፍትህ እና ሙስናን ለማስቆም የሚደረግ ትግል
በሪፖርቱ ላይ ከታወሱት መካከል በሰሜን ኪቩ ክልል የታጣቂ ቡድኖችን ጥቃት ሲመረምር በጥይት ተመትቶ የተገደለው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጎማ ከተማ የራዲዮ ማሪያ ጋዜጠኛ እና አስተባባሪ ኤድመንድ ባሃቲ ሞንጃ አንዱ በመሆን የተጠቀሰ ሲሆን፥ የጋዜጠኛው ሞት በጦርነት በሚታመሱ ክልሎች ውስጥ ኢፍትሃዊነትን የሚቃወሙ ወገኖች እያጋጠሟቸው ካሉት በርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ የአንዱ ማሳያ ነው ተብሏል።

ከእነዚህም በተጨማሪ ከተገደሉት ውስጥ ሁዋን አንቶኒዮ ሎፔዝ የተባለ የሆንዱራስ ሃገር ሚስዮናዊ ሲሆን፥ በአካባቢ ባለስልጣናት እና በወንጀል ድርጅቶች መካከል እያደገ የመጣውን ግንኙነት በማጋለጡ እንዲሁም ሙስናን በማውገዙ ምክንያት እንደተገደለ ተመላክቷል።

“እግዚአብሔር በእነሱ በኩል ተአምራትን ያደርጋል”
እ.አ.አ. ከ 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ፊደስ በዓለም ዙሪያ 608 ሚስዮናውያን እና ሃዋሪያዊ ሥራ ሰራተኞች መገደላቸውን የመዘገበ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የእነዚህን ሰዎች መስዋዕትነት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ አስታውሰውናል። ከእነዚህም ውስጥ ብጹእነታቸው የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓልን በማስመልከት “የሞተ የሚመስለው የመሥዋዕትነታቸው ዘር በመብቀል ፍሬ አፍርቷል፥ እግዚአብሔር ልባችንን በመለወጥ እንዲሁም ወንዶችንና ሴቶችን በማዳን በእነሱ በኩል ተአምራት ማድረጉን ቀጥሏል” በማለት የሚሲዮናዊያኑን ሞት በከንቱ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
 

31 December 2024, 15:05